ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከ6ሺህ በላይ የትክል ድንጋዮችን የያዘው እና በዩኔስኮ የተመዘገበው የጌዴኦ መልክዓ ምድር
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የጌዴኦ ባሕላዊ መልክዓ- ምድርን እንዲሁም የባሌ ተራሮችን በቅርስነት መዝግቧል።
ጌዴኦ ባሕላዊ ተፈጥሯዊ የእርሻና መልክዓ ምድር እንዲሁም የባሌ ተራሮች የዓለም ቅርስ በመባል በ45ኛ ዩኔስኮ ስብሰባ ላይ የተወሰነ ሲሆን፣ ይህም በኢትዮጵያ ስር የተመዘገቡ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶችን ወደ 15 አድርሶታል።
ጌዴኦ በአብዛኛው ተራራማና ወጣ ገባ፣ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ሜዳማ የሆነ መልክዓ ምድራዊ ገጽታ እንዳለው የዞኑ ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ አብርሃም መኩርያ ለቢቢሲ ገፀዋል።
በዚህ ተዳፋት በሚበዛበት መልክዓ ምድር ውስጥ ማኅበረሰቡ ለዘመናት የአፈር ደህንነቱን በጠበቀ መልኩ ጥምር እርሻ በማካሄድ ተፈጥሮን መንከባከቡን ይጠቅሳል።
አቶ ዳንኤል ከተማ፣ የጌዲኦ ዞን ባሕልና ቱሪዝም የፕሮሞሽን እና ኢንፎርሜሽን ባለሙያ ደግሞ ለጌዴኦ ቡና፣ እንሰት እና ደን ሲሉም ሕይወቱ ናቸው ይላሉ።
የጌዴኦ ባህላዊ አካባቢ ጥበቃ ባህላቸው ከዚህ ጋር የተያያዘው ለየት ያለ የእርሻ ልማዳቸው ፤ ጥንታዊ የቱቱ-ፈላ ትክል ድንጋዮች እና የድንጋይ ላይ ጥንታዊ ሥዕሎች ለዚህ ተመራጭ እንዳደረጓቸው የዩኔስኮ መረጃ ያሳያል።
የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ምዝገባ የኮንሶ መልክዓ ምድር ከተመዘገበ ከ12 ዓመት በኋላ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ነው።
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ደግሞ ከዚህ ቀደም በዩኔስኮ በጊዜያዊነት ተመዝግቦ የቆየ ሲሆን በቋሚነት ለማስመዝገብም 16 ዓመታት ያህል ፈጅቷል።
የጌዴኦ ባሕላዊ መልክዓ ምድሩ ምን ምን ይዟል?
የጌዴኦ ባሕላዊ መልክዓ ምድር፣ የመሬት አያያዝ፣ ታሪካዊ ቅርሶች፣ ትክል ድንጋዮች፣ የዋሻ ላይ ጽሑፍና በባሕላዊ መንገድ ብቻ የሚተዳደሩ ደኖች እንደሚገኙበት አቶ አብርሃም ይናገራሉ።
በአፍሪካ ከሚገኙ 10 ሺህ ትክል ድንጋዮች መካካል 60 በመቶው ወይም 6 ሺህ በላይ የሚሆኑ በጌዴኦ ዞን እንደሚገኙ የባህል እና ቱሪዝም ባለሙያው ያስረዳሉ።
እነዚህ የትክል ድንጋዮች በሦስት የተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ ሲሆን በአንዱ ስፍራ ብቻ ከ1ሺህ 500 በላይ የትክል ድንጋዮች እንደሚገኙ ባለሙያው አቶ ዳንኤል ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እነዚህ የትክል ድንጋዮች የሚገኙባቸው ሦስት ስፍራዎች ጨልባ ቱቲቲ የአርኪኦሎጂካል መካነ ቅርስ፣ ቱቱፈላ እንዲሁም በርካታ ሺህ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ እና የድንጋይ ላይ ጽሁፎችን ያያዘው ኦዶላ ገልማ መሆናቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዞኑ ኃላፊዎች ገልጸዋል።
የትክል ድንጋዮቹ በሰው ፊት ቅርጽ እና በወንድ ልጅ ብልት መልክ የተቀረፁ ናቸው።
ከትክል ድንጋዮቹ ስር በወቅቱ በአካበቢው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ቀብራቸው የተፈጸመ ሲሆን፣ በቀብር ስፍራው ሌሎች የመገልገያ መሳርያዎች በቁፋሮ ተገኝተዋል።
በይርጋ ጨፌ ወረዳ፥ ጨልባ ቱቲቲ የአርኪኦሎጂ መካነ ቅርስ ብቻ 1ሺህ 506 በወንድ ብልት ብቻ የተቀረፁ ትክል ድንጋዮች ቆመው ይገኛሉ።
በቱቱፈላ መካነ ቅርስ ደግሞ 525 የትክል ድንጋዮች ይገኛሉ።
የጌዴኦ ሕዝብ ደንን የመንከባከብ ባህሉ ከ5000 ዓመት በፊት መጀመሩን የባሕልና ቱሪዝም ባለሙያው ያስረዳሉ።
የጌዴኦ መልክዓ ምድር በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ካደረጉት ነገሮች መካከል አንዱ ይህ መሆኑን ባለሙያው ጠቅሰው፣ ጥብቅ ደኖች ሳይነኩ ጥምር እርሻ እንደሚካሄድ የዞኑ መረጃ ያስረዳል።
በጌዴኦ ባሕላዊ አስተዳደር ስርዓት የተነሳ ኅብረተሰቡ ዛፍን “እንደ ልጅ” የማየት ባህል ማዳበሩን ሁለቱም ኃላፊዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ባሌ የተሰኘው የጌዴኦ ዞን የሚተዳደርበት የገዳ ስርዓት፣ በየዓመቱ የዘመን መለወጫ በዓል ደራሮ ላይ፣ አባ ገዳዎች ለሁሉም የጌዴኦ ሕዝቦች ስለ አካባቢ ጥበቃ እና ደን እንክብካቤ የተለያዩ መልዕክቶች ያስተላልፋሉ።
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ምን ይዟል?
በ1962 ዓ.ም የተመሰረተው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከአዲስ አበባ በ400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
የመሬት ሽፋኑ 215 ሺህ ሄክታር የሆነው ብሔራዊ ፓርኩ በውስጡ በርካታ ብርቅዬ አንእስሳትን ይዟል።
ከዚህ በፊት ቢቢሲ ያነጋረገርናቸው የፓርኩ ባለሙያዎች ፓርኩ በኦሮሚያ ውስጥ የሚገኙ ስድስት ወረዳዎች 29 ቀበሌዎችን እንደሚያዋስን ይገልጻሉ።
4377 ጫማ የሚረዝመው እና ከኢትዮጵያ በከፍታው ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የቱሊ ዲምቱ ተራራን ጨምሮ የአፍሮ አልፓይን ከፍተኛ ቦታዎች በዚህ ፓርክ ውስጥ ይገኛሉ።
የባሌ ተራሮች ከፍተኛ አካባቢ በተለያዩ መንገድ የተፈጠሩ ሀይቆች፤ እርጥበት አዘል መሬቶች፣ የእሳተ ጎሞራ ቅሪቶችን አቅፎ ይዟል፡፡
በባሌ ብሄራዊ ፓርክ 40 ያህል ወንዞች የሚፈሱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ዋቢ ሸበሌ፣ ዌብ፣ ዱማል፣ ያዶት እና ወልመል ይጠቀሳሉ።
በባሌ ብሔራዊ ፓርክ ከሚገኙ የዱር እንስሳት መካከል ቀይ ቀበሮ፣ ኒያላ ፣ አጋዘን እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።
ባሌን የተራሮች ለማስመዝገብ 16 ዓመታት መፍጀቱን የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነተር አቶ ነጋ ወዳጆ ተናግረዋል።
ኃላፊው ስለመመዝገቡ ጥቅም ሲያስረዱ ቱሪስቶች በብዛት አካባቢውን እንዲጎበኙ እንደሚያደርግ፣ በአካባቢ ያለውን ማህበረሰብም ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ጠቀሜታ ይዞ እንደሚመጣ አክለውም የዓለም አቀፍ እውቅና አንዲያገኝ እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት አስመዝግባለች።
ከእነዚህም መካከል የአክሱም ሀውልት፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት፣ የኮንሶ ባሕላዊ መልክዓ ምድር፣ የሲዳማ ፍቼ ጫምባላላ እና የኦሮሞ ገዳ ስርዓት ተጠቃሽ ናቸው።
የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ልዩ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል አንዱ በኢትዮጵያ ትልቁና ወደ 7 ሺሕ ኪሎ ሜትር ስኩዬር የሚሸፍነው ''የሐረና ደን'' በውስጡ በመገኘቱ ነው።
- ከዚህም በተጨማሪ ከ1ሺህ 600 በላይ የሚሆኑ ልዩ ልዩ ዓይነት ዕፅዋቶች
- 78 ዓይነት አጥቢ የዱር እንስሳት እና
- ወደ 200 የሚጠጉ አእዋፋት በፓርኩ ተጠልለው ይገኛሉ።
ከነዚህም መካከል 32 ዓይነት ዕፅዋቶች እና 17 የሚጠጉት ብርቅዬ የዱር እንስሳት በዚሁ ብሔራዊ ፓርክ ብቻ የሚገኙ ናቸው።
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርሶች መዝገብ ውስጥ የተካተቱ በርካታ የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች አሏት።ቅርሶቹ ከአክሱም ሐውልቶች እስከ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ድረስ የተዘረጉ ናቸው።
ከእነዚህም መካከል አስደናቂ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የአየር ንብረት፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ እንዲሁም የሰው ዘር መገኛ ስፍራዎች ተካተውበታል።
ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ለቱሪስት መዳረሻነት ከሚያበቋት ነገሮች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።
ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት 15 ቅርሶችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ አገር ናት።