ፖሊስ በካናዳ አውሮፕላን ማረፊያ የተዘረፈውን 15 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ወርቅ እየመረመረ ነው

የካናዳ ፖሊስ በቶሮንቶ ፒርሰን አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተዘረፈውን 15 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ወርቅ እየመረመረ ነው።

አውሮፕላን ማረፊያው በኦንታሪዮ ግዛት ከሚገኘው የማዕድን ስፍራ የሚወጣውንም ወርቅ ለማጓጓዝ አገልግሎት ላይ ይውላል ተብሏል።

የካናዳ ባለስልጣናት 15 ሚሊዮን ዶላር ወይም 20 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር በላይ የሚያወጣ ወርቅና ሌሎች ንብረቶችም ሰኞ፣ ሚያዝያ 9/2015 ዓ.ም መዘረፉን አስታውቀዋል።

ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ንብረቶችን የያዘ የአውሮፕላን ጭነትም በተጠቀሰው እለት አውሮፕላን ማረፊያ ላይ መድረሱንንና ጭነቱም ተራግፎ ማከማቻ ውስጥ መግባቱ ተገልጿል።

ፖሊስ በዚህ ወቅት ዝርፊያው እንደተፈጸመም ያምናል።

በካናዳ ታሪክ ውስጥም ከተፈጸሙ ታላላቅ ዝርፊያዎች አንዱ ነውም ተብሏል።

ከዚህ ቀደም በኩውቤክ ከሚገኘው የማከማቻ ቦታ 3 ሺህ ቶን የሚገመትና 18.7 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ለዳቦና ለፓን ኬክ የሚውለው ጣፋጩ የሜፕል ሽሮፕ ተዘርፏል።

ይህም የተፈጸመው በአውሮፓውያኑ 2011 እና 2012 ነው።

የፔል ግዛት ፖሊስ ኢንስፔክተር እስጢፋኖስ ዱቬስቴይን እንደተናገሩት ቡድናቸው ይህ ሊፈጸም የቻለበትን ማንኛውንም መንገዶች እየመረመሩ እንደሆነ ነው። የሰኞውን ክስተትም “አጋጥሞ የማያውቅና እና ያልተለመደ” ሲሉም ገልጸውታል።

በአውሮፕላኑ ተጭኖ የነበረው ኮንቴይነር 5 ካሬ ጫማ ስፋት ያለው ቢሆንም ክብደቱ ምን ያህል እንደሆነ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

ጭነቱን ያጓጓዘው አየር መንገድ፣ ጭነቱ ከየት እንደመጣና መድረሻው የት እንደሆነም ባለስልጣናቱ ለመናገር ፈቃደኛ አልሆኑም።

የቶሮንቶ ሰን ጋዜጣ ፖሊስ ከዚህ ዝርፊያ ጀርባ የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች እጃቸው አለበት ብሎ እንደሚያስብ ዘግቧል። ኢንስፔክተር እስጢፋኖስ በበኩላቸው ይህንን ለመወሰን ጊዜው ገና ነው ብለዋል።

ቢቢሲ በበኩሉ የሮያል ካናዳ ፖሊሰን እና ፒርሰን አውሮፕላን ማረፊያ ለማነጋገር ያደረው ጥረት አልተሳካም።