የቀድሞ የኮንጎ ፕሬዚዳንት በጦር ወንጀሎች ሞት ተፈረደባቸው

የቀድሞው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ በሌሉበት በጦር ወንጀሎች እና አገር መክዳት ወንጀሎች ሞት ተፈረደባቸው።

ካቢላ ላይ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክልል ከፍተኛ ውድመት ያደረሱትን ኤም23 አማፂያን ይደግፋሉ የሚል ይገኝበታል።

አርብ ዕለት የአገሪቱ ወታደራዊ ፍርድ ቤት በአገር ክህደት፣በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸመ ወንጀል፣ እንዲሁም ግድያ፣ የወሲብ ጥቃት፣ ማሰቃየት እና ማመጽን ጨምሮ በተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች ጥፋተኛ ናቸው ብሏል።

ካቢላ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ቢናገሩም ችሎት ፊት ቀርበው ግን ራሳቸውን አልተከላከሉም።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ክሱን "በዘፈቀደ" የጠመሰረተ ያሉ ሲሆን ችሎቱን ደግሞ "ለጭቆና መሣሪያ ሆኗል" በማለት ውድቅ አድርገውታል።

ጆሴፍ ካቢላ አሁን የት እንዳሉ አይታወቅም።

የ54 ዓመቱ ካቢላ እአአ በ2001 በጥይት የተገደሉትን አባታቸው ላውረንት በመተካት ለ18 ዓመታት አገሪቱን አስተዳድረዋል።

ካቢላ እአአ በ2019 ለፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ ያስረከቡ ቢሆንም በኋላ ግን በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት እአአ በ2023 በፈቃዳቸው አገሪቱን ለቅቀው ተሰድደዋል።

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ የቀድሞው ፕሬዚዳንት በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ለሚካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት መፍትሄ ለማምጣት እንደሚፈልጉ የተናገሩ ሲሆን በቀጣዩ ወር በኤም23 አማጽያን በተያዘችው ጎማ ከተማ ደርሰዋል።

ይህንንም ተከትሎ ፕሬዚዳንት ቲሺሴኪዲ ከኤም23 ጥቃት ጀርባ ዋነኛ አንቀሳቃሹ ካቢላ ናቸው በሚል በመወንጀል እርሳቸው ላይ ክስ መመስረት እንዲያስችላቸው ሴናተሮች ያለመከሰስ መብታቸውን እንዲገፍፉ አድርገዋል።

ለበርካታ ዓመታት የቆየው የአማፂያኑ ትግል ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል በማዕድን የበለፀገውን አካባቢ የቡካቩ ከተማን እና ሁለት አየር መንገዶቿን በቁጥጥራቸው ስር ሲያውሉ ተባብሶ ቀጥሏል።

የመንግሥታቱ ድርጅት እና የምዕራባውያን አገራት አማፂያኑን በመደገፍ እንዲሁም በሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ወደ ኮንጎ በመላክ ጎረቤት ሩዋንዳን ይከስሳሉ።

ኪጋሊ እጄ የለበትም ብላ በመካድ ግጭቱ ግዛቷን አልፎ እንዳይስፋፋ የመከላከል ስራ እየሰራች መሆኑን ትናገራለች።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር በአማጺያኑ እና በመንግሥት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ቢፈረምም ግጭቱ ግን ቀጥሏል።