የናይጄሪያ መንግሥት የዩቲዩብ ቻናሎች እንዲታገዱለት ጠየቀ

የናይጄሪያ መንግሥት በአገሪቱ የታገዱ ቡድኖች በዩቲዩብ ላይ ምንም አይነት ስርጭት ማካሄድ እንዳይችሉ እንዲደረግ የማኅበራዊ ትስስር መድረኩ ባለቤት ጉግልን ጠየቀ።

የናይጄሪያ የማስታወቂያ ሚኒስትር ላይ ሞሐመድ ለጉግል ባቀረቡት ጥያቄ የዩቲዩብ ቻናሎቹ በአገሪቱ ላይ ሐሰተኛ ወሬዎችንና የጥላቻ ንግግሮችን እያስፋፉ ነው ብልዋል።

ሚኒስትሩ አቡጃ ውስጥ ከጉግል ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር በተነጋገሩበት ጊዜ “በሕገ ወጥነት የተፈረጁ ቡድኖችን እና የእነሱ ተባባሪዎችን ስያሜን የያዙ የዩቲዩብ ቻናሎች እና ኢሜይሎች በጉግል የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ሊፈቀድላቸው አይገባም” ሲሉ ጠይቀዋል።

የማስታወቂያ ሚኒስትሩ በውይይታቸው ወቅት የናይጄሪያ መንግሥት የባያፍራ ግዛትን በመገንጠል ነጻ አገር ለመመስረት የሚታገለው አይፖብ በመባል የሚታወቀው ቡድን በበይነ መረብ ላይ የሚያደርገው እንቅስቃሴ እንደሚያሳስበው ተናግረዋል።

ከናይጄሪያ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የወጣው መግለጫ “ማኅበራዊ ሚዲያን በኃላፊነት በመጠቀም በኩል መንግሥት እና ጉግል ተመሳሳይ ስጋት” አላቸው ብሏል።

የጉግል ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት የመንግሥት ጉዳዮች እና የሕዝብ ፖሊሲ ዳይሬክተር የሆኑት ቻርለስ ሙሪቶ “ተመሳሳይ ግብና አላማን ስለምንጋራ የማኅበራዊ መድረኮቻችን ለመጥፎ አላማ ጥቅም ላይ እንዲውሉ አንፈልግም” ማለታቸው ተገልጿል።

በዩቲዩብ በኩል የተለያዩ ይዘቶች የሚቀርቡ ሲሆን ሐሰተኛ ወሬዎች፣ የጥላቻ ንግግሮች እንዲሁም አሰቃቂ ምስሎች በመቅረባቸው ከመንግሥታት በኩል ተቃውሞ እየተሰማበት ነው።

በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ በሆነችው ናይጄሪያ ዩቲዩብ፣ ትዊተር፣ ፌስቡክ እና ቲክቶክ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ከፍተኛ ተጠቃሚዎች አሏቸው።

ዋነኛው የተንቀሳቃሽ ምስሎች [ቪዲዮ] ማቅረቢያ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ የሆነው ዩቲዩብ በወር 2.6 ቢሊዮን ተመልካቾች የተለያዩ ቪዲዮዎችን ይመለከታሉ።

የተለያዩ ወገኖችም ለትምህርት፣ ለመዝናኛ፣ ለፖለቲካ፣ ለሃይማኖት እና ለሌሎችም አላማዎች የሚውሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የቪዲዮ ይዘቶች በዓለም ዙሪያ በዩቲዩብ በኩል ይቀርባሉ።

በዚህም በየአንዳንዱ ደቂቃ 500 ሰዓታት የሚረዝሙ ቪዲዮዎች በዩቲዩብ ላይ ይጫናሉ።