በሱዳን ጥቁር ገበያ የኤኬ-47 ክላሺንኮቭ መሳሪያ ዋጋ በግማሽ ቀነሰ

የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ በመዲናዋ ካርቱም በጦርነቶች ላይ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው ኤኬ-47 የተባለው ጦር መሳሪያ ዋጋ በግማሽ መቀነሱ ተገለጸ።

በተለምዶ ክላሽ ተብሎ የሚጠራው ጦር መሳሪያው የእርስ በእርስ ጦርነቱን ተከትሎ ገበያ ውስጥ በስፋት በመሰራጨቱ ዋጋው በ50 በመቶ ቀንሶ በጥቁር ገበያ በ830 ዶላር (48ሺህ ብር ገደማ) እየተሸጠ ነው።

በስልጣን ሹኩቻ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ እና የአገሪቱ ጦር አዛዥ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ከገባች ወራት ተቆጥረዋል።

ለመጀመሪያ ግዜ በሩሲያ የተፈበረከውን ጦር መሳሪያ በቋሚነት በመግዛት እና መልሶ በመሸጥ የሚተዳደር አንድ የጦር መሳሪያ ነገዴ ለቢቢሲ ሲናገር የክላሸ ዋነኛ አቅራቢዎች ጡረታ የወጡ የጦር ጀነራሎች መሆናቸውን ገልጾ አብዛኛዎቹ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪዎች የነበሩት ናቸው ይላል።

ስሜ አይጠቀስ ያለው ይህ የክላሽ ነጋዴ በተለይ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የባህሪ ጦርነት ተብሎ ከሚታወቀው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ከተደረገው ውጊያ በኋላ የክላሽ ዋጋ ቀንሷል ይላል።

የካርቱም ሰሜናዊ ክፍል በሆነችው ባህሪ በተደረገው ውጊያ በአገሪቱ ጦር ሠራዊት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶ የነበረ ሲሆን ካርቱም እና ኦምዱሩማን ጨምሮ የባህሪን አብዛኛውን ክፍል ተቆጣጥረው የሚገኙት የፈጥኖ ደራሽ ኃይል አባላት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የአገሪቱን ጦር ሠራዊት ከእነ መሳሪያቸው ማርከው ነበር።

“በጦርነቱ ብዙ ወታደሮች ተይዘዋል እንዲሁም ተማርከዋል። በዚህ ምክንያት (የክላሽ) አቅርቦት በከፍተኛ መጠን ጨመረ” ይላል ይህ የጦር መሳሪያ አካፋፋይ።

ነጋዴው ከዚህ ቀደም የክላሽ ንግዱን የሚያጧጡፈው ከጡረተኛ ጀነራሎች ጋር በመመሳጠር በሰሃራ በረሃ በኩል ጦር መሳሪያውን ከሊቢያ በማስገባት ነበር።

ሐምሌ መጀመሪያ ላይ በተደረገው ውጊያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ክላሽ በመማረኩ አቅርቦቱ ከፈላጊው በልጧል በማለት ተናግሯል።

ከዚህ ቀደም አብዛኛው ክላሽ ገዢ የነበሩት በሱዳን ባለው ግጭት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አማጺዎች እና የሚሊሻ አባላት እንደነበሩ የሚገልጸው ነጋዴው አሁን ላይ ግን ደንበኞቹ የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ስጋት ውስጥ የከተታቸው እና እራሳቸውን ከጥቃት መከላከል የሚፈልጉ በካርቱም እና በዙሪያዋ ያሉ ተራ ነዋሪዎች ናቸው ብሏል።

ጦር መሳሪያ ገዢዎች ስልክ ደውለው ፍላጎታቸውን ይገልጻሉ። ከዛም ኤኬ-47 ቤታቸው ድረስ ይላክላቸዋል። ነጋዴው እንደሚለው ገዢዎች ክላሹን እንዴት እንደሚጠቀሙ አጭር ማብራሪያ እንደሚሰጣቸው ይገልጻል።

የክላሽ ጥይት ለብቻ እንደሚሸጥ የሚናገረው ይህ ነጋዴ፤ ኦማዱሩማን መሃል ገበያ ላይ ሌሎች ሸቀጦችን ይሸጡ የነበሩ ነጋዴዎች አሁን ላይ ወደ የክላሽ ጥይት ሻጭነት መቀየራቸውን ይህ ነጋዴ ጨምሮ የንግድ ሰንደለቱን ያብራራል።

ነጋዴው በቅርቡ ክላሽ ከሸጠላቸው ሰዎች መካከል አንዱ የስድስት ልጆች አባት የ55 ዓመት ጎልማስ መሆኑን ይናገረል።

“ወንጀል በመጨመሩ እና በሌሎች ጥቃት እንዳይደርስበት እራሱን ለመጠበቅ ነው የገዛው። የትኛውም ሰው በማታውቀውም ምክንያት ድንገት ሊያጠቃህ ይችላል። ይህ ጦርነት ወደ ብሔር ግጭት ሊቀየር ይችላል። ያ ነው ትልቁ ስጋታችን” በማለት ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ነጋዴ ይናገራል።

ሱዳንን በጋራ ሲሟሯት የነበሩት የአገሪቱ ጦር መሪ ጀነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጀነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ አገሪቱ ወደለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ገብታ ከፍተኛ ኪሳራ እያስተናገደች ነው።

በአሁኑ ወቅት በሱዳን ስላለው ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ንግድ ምን እንደሚመስል ለቢቢሲ ማብራሪያ የሰጠው የጦር መሳሪያ ነጋዴ ከክላሽ ይልቅ ብዙ ፈላጊ ያለው ሽጉጥ ነው ይላል።

ነጋዴው እንደሚለው ብዙዎች ለአጠቃቀም ቀላል እና ለመያዝ አመቺ የሆነውን ሽጉጥ ለመግዛት ፍላጎት አላቸው።

በጦርነቱ ምክንያት በአገሪቱ መንግሥት አለ ማለት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። የፖሊስ ኃይል ተበትኗል። እስር ቤቶች ተሰብረዋል እንዲሁም ፍርድ ቤቶcእ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም።

በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ በካርቱም ያለው ትልቁ እስር ቤት ተሰብሮ አደገኛ ወንጀለኞች ከእስር ቤት በጅምላ አምልጠው በካርቱም ጎዳናዎች ላይ እንደልባቸው እየተንቀሳቀሱ ነው።

ቀጣሪ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን በመበተናቸው የሚበሉትን ያጡ ቀማኛ ሆነዋል ይላል ነጋዴው። በእነዚህ ምክንያቶች ገንዘብ ያጠረው ሁሉ ጦር መሳሪያ መግዛትን ቀዳሚ አድርጎ እየታጠቀ ነው።

ይህ የጦር መሳሪያ ነጋዴ ለሽጉጥ ይከፈል የነበረው 1ሺህ 330 ዶላር በአራት እጥፍ ቀንሶ አሁን ላይ 350 ዶላር ገደማ እየተሸጠ ነው ይላል።

“ድሮ ሽጉጥን ውድ ያደርገው የነበረው ፍቃድ ማውጣቱ ነበር። አሁን ፍቃድ ማውጣት ስለማይጠበቅብህ ገዝቶ መጠቀም ብቻ ነው።”

በሱዳን ሰላማዊ ሰዎች ደኅንነታቸው አደጋ ላይ መሆኑን የሚያሳየው የ24 ዓመቱ ወጣት ገጠመኝ ነው። ይህ በቅርቡ ትዳር መስርቶ የአንድ ልጅ አባት የሆነው ወጣት መሠረታዊ ሸቀጦችን ለመግዛት ወደ ኦምዱሩማን ገበያ እያቀና ሳለ በታጠቁ አደገኛ ቦዘኔዎች በጥይት ተመትቶ ይዞት የነበረውን ገንዘብ ተዘርፏል።

የአከርካሪ አጥንቱን የተመታው ወጣት አደገኛ የሆነው የ200 ኪሎ ሜትሮች ጉዞ አድርጎ ሪቨር ናይል ግዛት ወዳለ ሆስፒታል ተወስዶ ጥይቱ ከሰውነቱ እንዲወጣ ቢደረግም የደረሰበት ጉዳት እድሜ ልኩን መንቀሳቀስ እንዳይችል አድርጎታል።