በአውስትራሊያ የአራት ዓመቱ ህጻን የአምቡላንስ ጥሪ የእናቱን ሕይወት አተረፈ

በአውስትራሊያ የአራት አመቱ ህፃን ለድንገተኛ ህክምና አምቡላንስ በመደወል የእናቱን ህይወት አተረፈ።

እናቱ ለድንገተኛ ህክምና እንዴት እንደሚደውል ካስተማረችው ከአንድ ቀን በኋላም ነው ስልክ የደወለው ተብሏል።

ሞንቲ ኮከር ብሔራዊ የአደጋ ቁጥር የሆነውን 000 በመደወል ለሰራተኞች “እማዬ ወድቃለች” ሲል ተናግሯል።

“የሰጠን አድራሻ ላይ ስንደርስ በመስኮት በኩል ቆሞ እያውለበልን ነበር” በማለት ማርክ ስሞል የተሰኘ የአምቡላንስ ሰራተኛ ተናግሯል።

በቤት ውስጥም ሞንቲ በእርጋታ የአምቡላንስ ሰራተኞቹንም ሲረዳ ነበር።

በፍጥነት ስልክ መደወሉ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል ሲል ማርክ ያስረዳል “ አንድ ሰው ሲወድቅ ጭንቅላቱን ከተመታ ወይም እንደሷ ረዘም ያለ መንቀጥቀጥ ካጋጠመው ለህይወቱ አስከፊ ሊሆን ይችላል”

የአስቸኳይ ጊዜ ሰራተኞች ለሞንቲ የምስጋና የምስክር ወረቀት ለማቅረብ ማክሰኞ በላንስስተን፣ ታዝማኒያ ወደሚገኘው ቤት ተመልሰዋል።

ነርሰ የሆነችው እናቱ ኮከር ለጋዜጠኞች ሞንቲ ጥሩ ነገር እንደሰራ ቢያውቅም ሚናው ግን ቀንሶ እንደሚናገር አስረድታለች። ለትምህርት ቤት ጓደኞቹም “ቀላል ነው” ሲል መናገሩን ገልጻለች።

“አያቱ መጥታ የጀግኖች ሁሉ ቁንጮ የት አለ ብላ ስትናገር አይ እኔ ጀግና ብቻ ነኝ” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ክስተቱ ከመፈጠሩ በፊት ኮከር ወደ አምቡላንስ እንዴት እንደሚደውል ለሞንቲ ያስረዳችው ሲሆን የተማረውን እንዲህ በአጭር ጊዜ በተግባር ላይ ያውለዋል ብላ ግን አልጠበቀችም።

ህመም ተሰምቷት ባሏን ለመጥራት ብትሞከርም እንዳልቻለች ተናግራለች።

“ስነቃ አምቡላንሱ አጠገቤ ነበር። በጣም ነው የኮራሁበት። እውነት ነው ህይወቴን አድኖታል” ብላለች።

“ለ13 ዓመታት ያህል የአምቡላንስ ሰራተኛ ሆኜ አገልግያለሁ ትልልቅ ልጆች አምቡላንስ ሲጠሩ አይቻለሁ ነገር ግን በፍጹም የአራት አመት ልጅ ይደውላል ብዬ አልጠብቅም” ብሏል።