የተመድ ባልደረቦች በሐማስ ጥቃት ተሳትፈዋል ከተባለ በኋላ አሜሪካ ድጋፍ አቆመች

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፍልስጤም የእርዳታ ኤጀንሲ ባልደረቦች ከሐማስ ጋር በማበር በእስራኤል ላይ ድንገተኛውን ጥቃት ፈጽመዋል መባሉን ተከትሎ አሜሪካ ለተቋሙ ታደርግ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ አቋረጠች።

ተቋሙ ሠራተኞቹ በመስከረም 26ቱ ጥቃት ተሳትፈዋል መባሉን ተከትሎ በርካታ ሠራተኞቹን ማባረሩን እና ዝርዝር ምርመራ ለማድረግ ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውቋል።

የተመድ ሠራተኞች በጥቃቱ ተሳትፈዋል የሚለውን መረጃ ያወጣችው እስራኤል ነች። ሠራተኞቹ በዚህ ጥቃት ላይ የነበራቸው ሚና ምን እንደሆነ አልተገለጸም።

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጉዳዩ በጣም ማዘናቸውን ገልጸው ዝርዝር መርመራ ማዘዛቸውን ገልጸዋል።

ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 1200 ሰዎችን ገድሎ ከ250 ያላነሱ ሰዎች ከእስራኤል ወስዶ ማገቱ ይታወሳል።

እስራኤል ደግሞ በወሰደቻቸው የአጸፈ እርምጃዎች አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕጻናት የሆኑ ከ26 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን በጋዛ ተገድለዋል።

የአሜሪካ መንግሥት የተመድ ሠራተኞች በዚህ የሐማስ ጥቃት ተሳታፊ ናቸው መባሉ እጅግ የሚረብሽ ዜና ነው ካለ በኋላ ለተቋሙ ይሰጥ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ በጊዜያዊነት ማገዱን አስታውቋል።

የተመድ የፍልስጤም የእርዳታ ኤጀንሲ ዋና ኃላፊ ፊሊፔ ላዛሪኒ እስራኤል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞቻቸው በጥቃቱ ተሳታፊ መሆናቸውን የሚያመላክት መረጃ አቅርባለች ብለዋል።

ይህ ተከትሎም ተቋሙ በበርካታ ሠራተኞች ላይ ምርመራ መጀመሩን ገልጸዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር አማካሪ የሆኑት ማርክ ሬጌቭ በመከስረም 26 ጥቃት ተሳታፊ ከነበሩት መካከል በተመድ የፍልስጤም እርዳታ ኤጀንሲ ደሞዝ የሚከፈላቸው ይገኙበታል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አማካሪው ጨምረውም በተመድ የፍልስጤም እርዳታ ኤጀንሲ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ መምህራን በግልጽ የመስከረም 26ቱን ጥቃት በአደባባይ ሲያወደሱ ነበር ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከእስራኤል ታግታ የነበረች አንዲት ሴት ከአገታ ከተለቀቀች በኋላ ታግታ የቆየችው ለተመድ በምትሰራ ሴት መኖሪያ ቤት ውስጥ መሆኑን ተናግራለች ብለዋል።

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የፍልስጤም እርዳታ ኤጅንሲ ኃላፊ ላዛሪኒ ጉዳዩን በጥልቀት እና በፍጥነት እንዲመረምሩ ትዕዛዝ መስጠታቸውን አስታውቀዋል።

ዋና ጸሐፊው በመከስረም 26 የተሳተፉ ወይም የረዱ ሠራተኞችን ከሥራ ለማባረር እና በተጨማሪም በወንጀል ለመክሰስ ምርመራ መካሄድ አለበት ብለዋል።

ጉተሬዝ ፈጣን እና ጥልቅ የሆነ ምርመራ እንዲካሄድ መጠየቃቸውን አሜሪካ በአዎንታዊ መልክ እንምትወስደው አስታውቃለች።

የአውሮፓ ኅብረትም የሠራተኞቹን ተሳትፎ በሚመለከተው መረጃ እጅጉን ማዘኑን ገልጾ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ሲያገኝ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።

ለዚህ የተመድ ተቋም ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉ መካከል አሜሪካ፣ ጀርመን እና የአውሮፓ ኅብረት ተጠቃሽ ናቸው።

ይህ ኤጀንሲ በጋዛ፣ በዌስት ባንክ፣ ጆርዳን፣ ሶሪያ እና ሌባኖስ የሚገኙ ፍልስጤማውያንን የትምህርት፣ የጤና አገልግሎት እና የሰብዓዊ እርዳታ በማቅረብ ይረዳል።

**

ማስታወሻ፡ በዚህ ዜና ላይ የሟቾች ቁጥር ማስተካከያ ተደርጎበታል።