ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የርገን ክሎፕ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ሊቨርፑልን እንደሚሰናበቱ ገለጡ
የሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብ አሠልጣኝ የርገን ክሎፕ በያዝነው የውድድር ዘመን መጨረሻ ቡድኑን እንደሚሰናበቱ አሳወቁ።
አሠልጣኙ “አቅሜ እየተንጠፈጠፈ ነው” ሲሉ ለውሳኔቸው ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ተናግረዋል።
ክሎፕ የሊቨርፑል አሠልጣኝ ሆነው የተሾሙት በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2015 ነበር። ኮንትራታቸው የሚያበቃው ደግሞ 2026 ነበር።
ጀርመናዊው አሠልጣኝ በ2019 ሊቨርፑል የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን እንዲያነሳ አስችለዋል።
በ2019/20 የውድድር ዘመን ደግሞ ሊቨርፑል ከ30 ዓመታት በኋላ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ድልን ባለቤት እንዲሆን አድርገዋል።
የ56 ዓመቱ አሠልጣኝ ስለውሳኔያቸው “ባለፈው ኅዳር ለክለቡ አሳውቂያለሁ” ያሉ ሲሆን፣ ቡድናቸው ፕሪሚዬር ሊጉን እየመራ ሳለ ነው ውሳኔያቸውን ይፋ ያደረጉት።
“እርግጥ ነው ይህን ዜና ለመጀመሪያ ጊዜ ስትሰሙ ትደነግጡ ይሆናል። ግን ለማስረዳት እሞክራለሁ” ብለዋል በቪድዮ በሰጡት መግለጫ።
“ክለቡን እጅግ እወደዋለሁ። ከተማዋን እጅግ እወዳታለሁ። ደጋፊዎቻችን እወዳቸዋለሁ። የቡድኑን አባላት እወዳቸዋለሁ። እንዲህም ሆኖ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሴ አስፈላጊ ውሳኔ መሆኑን ያሳያል።”
ክሎፕ አክለው “አቅሜ እየተሟጠጠ ነው። እርግጥ ነው አሁን ምንም ችግር የለብኝም። ይህ ቀን እንደሚመጣ አውቀዋለሁ። ይህን ሥራ ደግሜ፣ ደጋግሜ መሥራት እንደማልችል ውስጤ ያውቀዋል” ብለዋል።
ጀርመናዊው አሠልጣኝ ወደ መርሲሳይድ ከመጡ በኋላ ሊቨርፑል ሁሉንም ዋንጫዎች አንስቷል።
በ2019 ስፔን ማድሪድ ላይ በተደረገው የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ቶተንሀምን በመርታት ሊቨርፑል ስድስተኛውን የአውሮፓ ዋንጫ እንዲያገኝ አግዘዋል።
በዚያው ዓመት የዩኤፋ ሱፐር ካፕ እና የፊፋ ክለቦች ዋንጫንም አሸንፈዋል።
ተከትሎ በነበረው የውድድር ዘመን ደግሞ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን ከሊቨርፑል ጋር አንስተዋል።
በ2021/22 የውድድር ዘመን በመጨረሻው ቀን በማንቸስተር ሲቲ ተቀምተው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን ሲያጡ፣ ፓሪስ በተካሄደው የፍፃሜ ጨዋታ ደግሞ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አጥተዋል።
ነገር ግን በተመሳሳይ ዓመት የኤፍ ኤ ዋንጫ እና የካራባዎ ዋንጫን ድልን ለመቀዳጀት ችለዋል።
ቀያዮቹ ባለፈው ዓመት ምንም ዓይነት ዋንጫ ባያገኙም በያዝነው የውድድር ዘመን በአራቱም ዋንጫዎች እየተፎካከሩ ይገኛሉ።
ባለፈው ረቡዕ ፉልሃምን በመርታት ለካራባዎ ዋንጫ ፍፃሜ ደርሰዋል።
የሊቨርፑል ረዳት አሠልጣኝ የሆኑት ፔፕይን ሊንደርስ እና ፒተር ክራዊትዝ እንዲሁም ቨቶር ማቶስ፤ ክሎፕን ተከትለው ቡድኑን ይለቃሉ።
ሊቨርፑል አሁን ፕሪሚዬር ሊጉን እየመራ ሲሆን፣ ለካራባዎ ዋንጫ ፍፃሜ ከመድረሱም በላይ በመጪው እሑድ በኤፍ ኤ ዋንጫ ከኖርዊች ሲቲ ይፋለማል። በአውሮፓ ሊግ ደግሞ ወደ ጥሎ ማለፉ መድረስ ችሏል።
ክሎፕ የማሸነፍ ዕድላቸው በመቶኛ ሲሰላ 60.7 በመቶ ሲሆን፣ ይህ ከቀድሞዎቹ የሊቨርፑል አሠልጣኞች ሁሉ ከፍ ያለ ነው።
አልፎም ኤፍ ኤ፣ ካራባዎ፣ ቻምፒዮንስ ሊግ አሊያም የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫን ከሊቨርፑል ጋር ያነሱ ብቸኛው አሠልጣኝ ናቸው።