ኢራን መንግሥትን የሚቃወሙ ታዋቂ ግለሰቦችን ‘ለመቅጣት’ ምስጢራዊ ኮሚቴ ማቋቋሟ ይፋ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, TARANEH ALIDOOSTI
ኢራን ጸረ መንግሥት የተቃውሞ ሰልፎችን የሚደግፉ ታዋቂ ግለሰቦችን ለመቅጣት ሚስጥራዊ ኮሚቴ ማቋቋሟ ሾልከው የወጡ ሰነዶች አጋለጡ።
ቢቢሲ የተመለከታቸው እነዚህ ሾልከው የወጡ ሰነዶች በኢራን ከተከሰተው አለመረጋጋት ከስድስት ቀናት በኋላ ኮሚቴው የ141 ታዋቂ ሰዎችን ስም ዝርዝር የያዘ ደብዳቤ መስከረም 22፣ 2015 ዓ.ም ጽፎ ለኢኮኖሚ ሚኒስቴር ልኳል።
ይህ ኮሚቴ “የታዋቂ ግለሰቦች ግብረ ኃይል” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ሊቀ መንበሩ የባህል እና እስላማዊ መመሪያ ሚኒስትሩ መሀመድ መህዲ እስማኢሊ ሲሆኑ በአውሮፓ ህብረትም ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ፈጽመዋል በሚል ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።
ኮሚቴው በደብዳቤው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የነዚህን ታዋቂ ግለሰቦች የግብር ተመላሽ አጣርቶ ያልተገለጸ እርምጃ እንዲወሰድባቸውም ጠይቋል።
በዝርዝር ውስጥ ታዋቂው የእግር ኳስ ተጫዋች አሊ ዴኢ እና ተዋቂዋ ተዋናይት ታራኔህ አሊዶስቲ ተካትተዋል።
እነዚህ ግለሰቦች ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ ተቃዋሚዎች ያነሷቸውን የነጻነት ጥያቄዎች መደገፋቸውን ተከትሎ የኢኮኖሚ ማዕቀብ፣ የጉዞ እገዳ ወይም እስር ካጋጠማቸው በደርዘን ከሚቆጠሩ አርቲስቶች፣ ስፖርተኞች እና የማህበራዊ ተጽእኖ ፈጣሪዎች መካከል ናቸው።
የራስ መሸፈኛዋን በአግባቡ አልለበሽም ተብላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር በነበረችበት ወቅት በደረሰባት ድብደባ የሞተችው ማህሳ አሚኒንም ሞት ተከትሎ ነው በኢራን ብሔራዊ ቁጣ የተቀሰቀሰው።
የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲሞቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ታስረዋል። ኢራን ህዝባዊ ተቃውሞው በውጭ ሃገራት የተቀሰቀሰ አመጽ አድርጋም እንደምታየው አስታውቃለች።
ቢቢሲ ፐርዢያ በመካከለኛው ምስራቅ ከሚገኝ የስለላ ምንጭ ሶስት ሰነዶችን አግኝቷል። በነዚህም ሰነዶች መሰረት መንግሥት ታዋቂ ሰዎች ለተቃውሞው ድጋፍ እንዳይሰጡ ለመከላከል በሚል ፈጣን እና የተቀናጀ እርምጃ እንዴት መውሰድ እንዳለበትም የሚዘረዝር ነው።
ኮሚቴው የኢራንን ሁከት በማቀጣጠል ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል የተባሉ 141 ታዋቂ ግለሰቦችን የግብር ምላሽ እንዲመረምርና በህጉ መሰረት የሚጠበቁ ገደቦች እንዲተገብር ለኢኮኖሚ ሚኒስቴር ትዕዛዝ ማስተላለፉ ተጠቅሷል።
ታህሳስ ወር ላይ አንድ ተቃዋሚ በመንግሥት መገደሉን በመቃወም አሊ ደኤሊ እና ታራነህ አሊዶስቲ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ከሁለት ሳምንት በኋላም በዋስ ተለቀዋል።
በዚህ ዝርዝር ውስጥ ከነዚህም በተጨማሪ ታዋቂዎቹ የፊልም ባለሙያዎች አስጋሪ ፋርሃዲ፣ ፔጋህ አሀንጋራኒ፣ ማኒጄህ ሄክማት፣ ባርዙ አርጆማንድ እና ሻሂን ሳማድፑር፣ እንዲሁም የቀድሞ የቴሌቪዥን አቅራቢ ኢህሳን ካራሚ ይገኙበታል።












