የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የ72 ሰዓት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደረሱ

 የተፈናቀሉ የሱዳን ዜጎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ለ72 ሰዓት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን አስታወቁ።

በተቀናቃኝ ጎራ ተሰልፈው እየተፋለሙ ያሉት የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የተኩስ አቁም ስምምነት ሰኞ እኩለ ሌሊት እንደተጀመረ ተገልጿል።

በሱዳን ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የአሁኑን ጨምሮ ቢያንስ ለሦስት ጊዜ ያህል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።እስካሁን የነበሩት የተኩስ አቁም ስምምነቶች ተፋርሰው ውጊያው ቀጥሎም ቆይቷል።

በመደበኛው ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ለ48 ሰዓታት ያህል ድርድር ከተደረገ በኋላም የአሁነኛው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መደረሱን ብሊንከን ገልጸዋል።

ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ በተናጠል አስታውቀዋል።

ጦርነቱ ሚያዝያ 7/ 2015 ዓ.ም ከተቀሰቀሰበት እለት ጀምሮ ቢያንስ የ400 ዜጎች ሕይወት ተቀጥፏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በሱዳን የተቀሰቀሰው ግጭት አገሪቱን ብቻ ሳይሆን መላውን ቀጠናውንም ሊያውክ የሚችል “አሰቃቂ ጦርነት” ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ግጭቱ ከተቀሰቀበት ጀምሮ የጦርነቱ ማዕከል የሆነችው የካርቱም ነዋሪዎች በቤት ውስጥ እንዲወሰኑ የተነገራቸው ሲሆን የምግብ እና የውሃ አቅርቦትም ተመናምኗል።

የቦምብ ጥቃቶችም ቁልፍ የሚባሉ መሰረተ ልማቶችን እንደ ውሃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ከጥቅም ውጭ በማድረጋቸው አንዳንዶች ከናይል ወንዝ ለመጠጣት ተገደዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሁን የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ ሲቪሎች መዲናዋን ካርቱምን ለቀው እንዲወጡ ያስችላቸዋል የሚልም ተስፋን ጭሯል። የውጭ አገር መንግሥታትም ዜጎቻቸውን ጨርሶ ለማስወጣት ያስችላልም ተብሏል።

ጦርነቱ በርካታ ሕዝብ በሚኖርባት መዲናዋ ካርቱም ላይ በማተኮሩ አገራት ዲፕሎማት እና ሲቪል ዜጎቻቸውን ለማስወጣት ከፍተኛ ፈተናም ሆኖባቸው ነበር።

ነዋሪዎችን ጭነው ወደ ውጭ ለማስወጣት የሞከሩ መኪኖችም ትናንት ሚያዝያ 16/2015 ዓ.ም እንደተዘረፉ ብሊንከን አስታውቀዋል።

የሚሊዮኖች ሕይወት ስጋት ውስጥ በገባበት በዚህ ግጭት መሃል የሱዳንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ሁለት ጄነራሎች እየተፋለሙ ይገኛሉ።

የሱዳን ጦር ኃይል መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ ተፋጠዋል።

ለዚህም ትርምስ ምክንያቱ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ከዋናው ጦር ጋር እንዴት መልሶ ማዋቀር ይችላል በሚለው ጉዳይ ላይ ከማተኮሩ ጋር የተያያዘ ነው።

ለሥስት አስርት ዓመታት ሱዳንን የገዟትን ፕሬዚዳንት አልበሽርን የገረሰሰውን አብዮት ተከትሎም በ2021 ከተከሰተው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ሱዳን በጄነራሎች ምክር ቤት ስትመራ ቆይታለች።

የሱዳንን ጦር ኃይል መሪ ጄነራል አል ቡርሃን የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት እንዲሁም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጄነራል ሄምቲም ምክትል ፕሬዚዳንትም ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ሁለቱ ተቀናቃኝ ጄነራሎች አገሪቱ እየተከተለችው ባለው አቅጣጫ እና ሱዳንንም ወደ ሲቪል አገዛዝ ለመመለስ በቀረበው ሃሳብም ላይ መስማማት አልቻሉም።

በተለይም 100 ሺህ የሚሆኑት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በምን መንገድ ወደ ጦር ሰራዊቱ ይካተቱ እንዲሁም አዲሱን ኃይል የሚመራው ማን ነው የሚለውም የግጭት መንስኤ ሆኗል።

ጄነራል ዳጋሎ የጀኔራል ቡርሃን መንግሥት “አክራሪ እስላማዊ ነው” በሚል ክስ የሚያቀርቡባቸው ሲሆን እሳቸው እና ጦራቸው የሱዳን ህዝብ ለረጅም ጊዜ ሲመኘው የነበረውን “ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ” ለማስፈን እየታገሉ እንደሆነ ይናገራሉ።

ሆኖም በዳርፉር የዘር ጭፍጨፋን ጨምሮ በሌሎች አረመኔያዊ ጥሰቶች የሚነሱት ጄነራል ዳጋሎን ንግግር ለማመን በርካቶች ይከብዳቸዋል።

ጄነራል ቡርሃን በበኩላቸው ሱዳን ወደ ሲቪል አገዛዝን መመለሷን እንደሚደግፉ፤ ነገር ግን ሥልጣናቸውን ለተመረጠ መንግሥት ብቻ እንደሚያስረክቡ አስታውቀዋል።