የ70 ዓመቱን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን የቀረጹ ሰባት ቁልፍ ጉዳዮች

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን 70ኛ ዓመት ልደታቸውን አርብ መስከረም 27/2015 ዓ.ም. አክብረዋል።

ከምዕራባውያኑ የተነጠሉት፣ በቅርቡ በዩክሬን ላይ ወረራ በማድረግ መነጋገሪያ የሆኑት፣ ኃያሉ እና አወዛጋቢው ፕሬዝዳንት ፑቲን ጉዟቸው ምን ይመስላል?

በሕይወታቸው ውስጥ ሰባት ወሳኝ ሁኔታዎች አስተሳሰባቸውን እንዴት እንደቀረጹ እና ከምዕራባውያን ጋር ያላቸው ልዩነት ለምን እንዲህ ሰፋ የሚለውን ያሳያሉ።

የጁዶ ሥልጠና- 1964

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የተወለዱት ሌኒንግራድ ውስጥ ነው።

ወቅቱ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሳቢያ በከተማዋ ላይ ተጥሎ የነበረው የ872 ቀናት ወታደራዊ ከበባ የጣለው ጠባሳ ያልሻረበት ነበር።

ትንሹ ቭላድሚር ፒቱን በትምህርት ቤት ቆይታው ፈጣን፣ ደፋር እና ጸበኛም ነበር። የትምህርት ቤት የልብ ጓደኛው ትንሹን ፑቲንን ሲገልጸው “ከማንም ጋር ይጣላ ነበር” ምክንያቱም “ምንም አይነት ፍርሃት አልፈጠረበትም” ይላል።

ሆኖም በጎዳና ወሮበሎች በተጨናነቀችው በዚያች ከተማ ቀልጠፋው፣ ሆኖም አነስ ያለው ፑቲን ገና በ12 ዓመቱ ነበር አካላዊ ገፅታውን ማዳበር እንዳለበት የተረዳው።

በመጀመሪያ የሩሲያ የማርሻል ጥበብ የሆነውን ሳምቦ በ12 ዓመቱ መማር ጀመረ ቀጥሎም የጁዶ ሥልጠናዎችን ወሰደ።

ቆራጥ እና የማይበገረው ፑቲን ገና በ18 ዓመቱ ከፍተኛ የሚባለውን የጁዶ ጥቁር ቀበቶ እንዲሁም በብሔራዊ የታዳጊዎች ውድድር ሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል።

በእርግጥ ከዚያም በኋላ ፕሬዝዳንት ፑቲን አካላዊ ግንባታቸውን ቀጥለዋል።

ገና በታዳጊነታቸው ጀምሮ ፑቲን የሚያምኑበት ጉዳይ ቢኖር በዚህች አደገኛ ዓለም ውስጥ በራስ የመተማመን ስሜትን አስፈላጊነት ነው።

እሳቸው እንደሚሉትም ጸብ ወይም ግጭት የማይቀር ከሆነ “መጀመሪያ ቀድመህ መምታት አለብህ፣ እናም ተፋላሚህ እንዳይነሳ አድርገህ በደንብ መምታት አለብህ” ይላሉ።

ቭላድሚር ፑቲን በጁዶ ስልጠና ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኬጂቢን ሥራ መጠየቅ - 1968

ብዙዎች ሌኒንግራድ ወደሚገኘው ቦልሾይ ዶም ወደተሰኘው የኬጂቢ ቢሮ መሄድን በሩቁ ይሉታል። በስታሊን አገዛዝ ዘመን ብዙዎች ጉላግ ወደሚባሉት የጉልበት ሥራ ካምፖች ሲወሰዱም በኬጂቢ የምርመራ ክፍሎች አልፈዋል።

ቦልሾይ ዶም በሌኒንግራድ ውስጥ ረጅሙ ህንፃ ነው ለዚህም በርካቶች መረር ያለ ቀልድ አላቸው፤ ይህም ከህንጻው ከምድር ቤት እንኳን ተሁኖ ሳይቤሪያን ማየት እንዲያስችል ተደርጎ የተሰራ ነው ይላሉ።

የ16 ዓመቱ ፑቲን ይህ ሁሉ አላስደነገጠውም። በቀይ ምንጣፍ በተሸፈነው መሰተንግዶ ክፍል ውስጥ በማለፍ ከጠረጴዛው በስተጀርባ ያለውን የተደነቀውን መኮንን እንዴት “ኬጂቢን መቀላቀል እችላለሁ?” ብሎ ጠየቀ።

የውትድርና ሥልጠና ወይም የዲግሪ ትምህርቱን ማጠናቀቅ እንዳለበት ተነገረው። እሱም አላረፈም፤ የትኛው ዲግሪ ይሻላል? ብሎ ጠየቀ።

የሕግ ትምህርት የተሻለ እንደሆነም ተነገረው። ኬጂቢን ለመቀላቀል ቁርጠኛ የነበረው ፕሬዝዳንት ፑቲን የሕግ ትምህርቱን አጠናቆ በመመረቅ ለኬጂቢ ተመለመለ።

ለፑቲን ኬጂቢ በከተማው ውስጥ ያሉ ወሮበሎችን ጸጥ የሚያሰኝ እንዲሁም የፓርቲ ግንኙነት ለሌላቸው እንኳን ደኅንነትን እና እድገትን ማረጋጫ መንገድ ነበር።

በተጨማሪም የኬጂቢ አባል መሆን አድራጊ እና ፈጣሪ መሆንንም ማሳያ ነበር፤ ፑቲን ራሳቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያሉ ስለተመለከቷቸው የስለላ ፊልሞች እንደተናገሩት “አንድ ሰላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እጣ ፈንታ ሊወስን ይችላል” ብለዋል።

በጀርመን ኬጂቢ የገጠመው ከበባ- 1989

ምንም እንኳን ፑቲን ትልልቅ ተስፋዎችን ቢሰንቁም በኬጂቢ የሥራ ዕድገት ሊያመጡ አልቻሉም። ጠንካራ ሠራተኛ ቢሆኑም ወደየትም ንቅንቅ አላሉም።

ከዚያም የጀርመንኛ ቋንቋን ተምረው በጀርመን ድሬዝደን ወደሚገኘው የኬጂቢ ቢሮ በአውሮፓውያኑ 1985 ተዘዋውረው ተሾሙ።

እዚያም በተመቻቸ ኑሮ ላይ ባሉበት ወቅት በአውሮፓውያኑ 1989 የምሥራቅ ጀርመን አገዛዝ በአስደንጋጭ ፍጥነት መንኮታኮት ጀመረ። በዚያው ዓመትም ታኅሣሥ ላይ በርካታ ሰዎች የድሬዝደን የኬጂቢ ህንፃን ከበቡት።

ፑቲንም በቅርበት ወደሚገኘው የሶቪየት ቀዩ ጦር እርዳታ እንዲሰጣቸው ደወሉ። ሆኖም የተሰጣቸው መልስ ከሞስኮ ትዕዛዝ ካልመጣ ምንም ማድረግ አንችልም የሚል ነበር።

የሞስኮ ምላሽ ዝምታ ነበር። ፑቲን የማዕካላዊው መንግሥት ሥስጣን ድንገተኛ መፍረክረክ ፍርሃት ፈጠረባቸው፤ እናም የሶቪየት ኅብረትረ መሪ ሚኻኤል ጎርባቾቭን ስህተት ያሉትን ላለመድገም ቆርጠውም ተነሱ።

ይህም ተቃውሞ ሲነሳ በፍጥነት እና በቁርጠኝነት ምላሽ መስጠት የሚለውን ነው።

‘ነዳጅን በምግብ የመለወጥ ፕሮግራም’ ደላላ - 1992

የሶቭየት ኅብረትን መፍረስን ተከትሎ ፑቲን ኬጂቢን ለቀቁ።

ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ ለአዲሱ እና ተሃድሶን ለሚያራምደው የሴንት ፒተርስበርግ ከንቲባ መስራት ጀመሩ። ጊዜው የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት የተንኮታኮተበት ወቅት ነበር።

ፑቲንም 100 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ነዳጅ ዘይት እና ብረትን በምግብ በመለወጥ የከተማውን ሕዝብ እንዲረዱ ኃላፊነት ተሰጣቸው።

ሆኖም ምግቡ ተደራሽ አልሆነም። በወቅቱ ተጀምሮ እንዲታፈን በተደረገው ምርመራ መሠረት ፑቲን፣ ከጓደኞቻቸው እና ከከተማ ወንበዴዎች ጋር በመሆን ገንዘቡን ወደኪሳቸው አስገቡ።

ፑቲን የተረዱት ጉዳይ የፖለቲካ ተጽእኖ በገንዘብ የሚተመን እንደሆነ እና ወሮበሎች (ወንበዴዎች) ጠቃሚ አጋሮች መሆን ይችላሉ የሚለውን ነው።

በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ኃላፊነታቸውን ሲጠቀሙበት እሳቸውስ ቢሆን ለምን አይጠቀሙበትም።

የጆርጂያ ወረራ - 2008

ፑቲን በአውሮፓውያኑ 2000 የሩሲያ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ ከምዕራቡ ዓለም ጋር መልካም ግንኙነት ለመመስረት ተስፋ አድርገው ነበር።

በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት አገራት ላይ ተጽእኖን ማሳረፍን ጨምሮ ባሰቡት መልክ ከምዕራባውያኑ ጋር ግንኙነትን እፈጥራለሁም አሉ።

ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ቅር የሚያሰኝ ነገር ገጠማቸው። ምዕራቡ ዓለም ሩሲያን ለማግለልና ለማዋረድ እየሞከረ ነው በሚልም መበሳጨት ጀመሩ።

የጆርጂያው ፕሬዝዳንት ሚካኤል ሳካሽቪሊ አገራቸው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) እንትድቀላል እሰራለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ይህ ሁኔታ ለፑቲን ማንቂያ ነበር።

ጆርጂያ በሩሲያ የሚደገፈውን ተገንጣዩን ደቡብ ኦሴትያን ለመቆጣጠር ያደረጉት ሙከራ ለሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻም ሰበብ ሆኖ ተገኘ።

በአምስት ቀናት ውስጥም ሩሲያ የጆርጂያን ጦር ሠራዊት ሰባብሮ ፕሬዝዳንት ሳካሽቪሊ በአሳፋሪ ሁኔታ ሰላም እንዲያውጁ ተገደዱ።

ይህም ሁኔታ ምዕራባውያንን በከፍተኛ ሁኔታ አስቆጣ። ነገር ግን በአንድ ዓመት ውስጥ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደገና ለማደስም ሞከሩ በዚህም ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2018 የተደረገውን የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫን እንድታዘጋጅ ተደረገ።

የጆርጂያ ወረራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሞስኮ የተደረጉ ተቃውሞዎች - 2011-13

በአውሮፓውያኑ 2011 የተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ መጠነ ሰፊ በሆነ ሁኔታ ተጭበርብሯል በሚል በርካቶች ተቃውሞ አስነሱ።

በተለይም ፕሬዝዳንት ፑቲን በአውሮፓውያኑ 2012 በድጋሚ ለመመረጥ ዕጩ መሆናቸውን ባወጁበት ወቅት ተቃውሞው በከፍተኛ ሁኔታ ተጋጋለ።

ሰልፈኞች የሞስኮን አደባባይ በማጥለቅለቅቃቸው “የቦሎትናያ ተቃውሞ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ይህም በፕሬዝዳንት ፑቲን ዘመን ከታዩ የሕዝብ ተቃውሞዎች መካከል ከፍተኛው ነው።

ፑቲን እነዚህ ሰልፎችም ሆኑ ተቃውሞዎች የተጀመሩት እና የሚደገፉት በዋሽንግተን ነው በማለት በተለይም በወቅቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት ሂላሪ ክሊንተንን በግል ይወቅሷቸው ነበር።

ለፑቲን ይህ ምዕራባውያን በቀጥታ እንደተነሱባቸውና ጦርነትም ውስጥ እንደሚገቡ ማሳያ ነበር።

በሞስኮ የተደረጉ ተቃውሞዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኮቪድ-19 ወቅት መገለል - 2020-21

በዓለም ላይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ባልተለመደ ሁኔታ ፕሬዝዳንት ፑቲን ራሳቸውን አገለሉ።

ማንም ሊያገኛቸው የፈለገ ሰው ቢሆን ለሁለት ሳምንት ያህል ራሱን ማግለል አለበት። በዚያም አያበቃም፤ ከዚያም ጀርሞችን በሚገድል አልትራቫዮሌት ጨረር በተሞላ እና በፀረ ተህዋስያን በተረጨ ኮሪደር ውስጥ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል።

በዚህም ምክንያት ፑቲንን በዚህ ወቅት ሊያገኟቸው የቻሉት በጣም ጥቂቶች ናቸው። እነሱም የቅርብ እና የሚሉትን ሁሉ የሚፈጽሙ ታማኞቻቸው ብቻ ነበሩ።

ምንም አይነት ከእሳቸው የተቃረኑ ሐሳቦችን የማያስተናግዱት እና አገራቸውንም እምብዛም ተዘዋውረው ያልተመለከቱት ፑቲን፣ የሚያስቡትና የሚገምቱት ሁሉ ትክክል መሆናቸውን በማሰብ ዩክሬንን የመውረር ሐሳብም በውስጣቸው እንዲጸነስ ምክንያት ሆኗል።

___

* የዚግ ጽሁፍ አዘጋጅ ፕሮፌሰር ማርክ ጋሌቲ፣ ምሁር እና ደራሲ ሲሆኑ ከመጽሐፋቸውም ውስጥ ‘ዊ ኒድ ቱ ቶክ አባውት ፑቲን ኤንድ ዘ ፎርዝካሚንግ ፑቲንስ ዋርስ’ ይገኝበታል።