ደም በመለገስ የ2.4 ሚሊዮን ሕፃናትን ሕይወት የታደጉት አውስትራሊያዊ ሞቱ

ሃሪሰን ከልጅ ልጃቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Australian Red Cross Lifeblood

የምስሉ መግለጫ, ጀምስ ሃሪሰን ከልጅ ልጃቸው ትሬይ ጋር ቀደም ብሎ የተነሱት ፎቶ

በዓለማችን ከከፍተኛ ደም ለጋሾች አንዱ የሆኑት እና በደማቸው የሚገኘው ፕላዝማ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሕፃናትን የታደጉት አውስትራሊያዊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ጀምስ ሃሪሰን ሕይወታቸው ያለፈው በአውስትራሊያ፣ ኒው ሳውዝ ዌልስ በሚገኝ የእንክብካቤ ማዕከል በእንቅልፍ ላይ ሳሉ መሆኑን ቤተሰቦቻቸው አስታውቀዋል።

ሃሪሰን የ88 ዓመት አዛውንት ነበሩ።

'ባለ ወርቃማ ክንዱ' በሚል በአውስትራሊያ የሚታወቁት ሃሪሰን፣ ደማቸው ውስጥ የሚገኘው ፕላዝማ እምብዛም የማይገኘውንና በደም ውስጥ በሽታ የመከላከያ ሥርዓት የሚዘጋጅበትን [አንቲ ቦዲ]፣ አንቲ ዲን የያዘ ነበር። ይህ አንቲ ዲ የሚለገሰው የገዛ ራሳቸው ደም ፅንሳቸውን ለሚያጠቃባቸው ነፍሰ ጡር ሴቶች ነው።

ፕላዝማ የሰውነት የበሽታ መከላከያ ሥርዓት [አንቲ ቦዲ] የሚዘጋጅበት በደም ውስጥ የሚገኝ ፈሳሽ ክፍል ነው።

የአውስትራሊያ ቀይ መስቀል የደም አገልግሎት ለሃሪሰን በጻፈው መዘከሪያ ጽሑፉ እንዳለው ሃሪሰን ደም ለመለገስ ቃል የገቡት የ14 ዓመት ታዳጊ ሳሉ ቀዶ ሕክምና ሲያደርጉ ደም ከተለገሰላቸው በኋላ ነበር።

ከዚያም የ18 ዓመት ወጣት ሳሉ ጀምረው ፕላዝማ መለገስ የጀመሩ ሲሆን እስከ 81 ዓመታቸው ድረስ በየሁለት ሳምንቱ ደማቸውን ሲለግሱ ቆይተዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 ፕላዝማ በመለገስ የዓለምን ክብረ ወሰን ይዘው እስከ 2022 ቆይተዋል። ከዚያ ግን ይህንን ክብረ ወሰን በአሜሪካዊ ግለሰብ ተነጥቀዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሃሪሰን ሴት ልጅ ትሬሲይ ሜሎውሽፕ፣ አባቷ ያለምንም ክፍያ እና ህመም የበርካቶችን ሕይወት ስለታደገ ኩራት እንደሚሰማት ገልጻለች።

" ሁልጊዜም ይህን ማድረጉ ምንም እንደማይጎዳው እና 'የምትታደጊው ሕይወት ያንችም ሊሆን ይችላል' ይል" ነበር" ብላለች።

ሜሎውሽፕ እና የሃሪሰን ሁለት የልጅ ልጆች የአንቲ ዲ ተቀባይ ናቸው።

" ይህም ሃሪሰንን ልክ እንደኛ ሁሉ በርካታ ቤተሰቦች በእርሱ ደግነት መኖር በመቻላቸው ደስተኛ ያደርገው ነበር" ብላለች።

አንቲ ዲ ክትባት ያልተወለዱ ሕፃናትን፣ በፅንስ ጊዜ እንዲሁም ከተወለዱ በኋላ ከሚያጋጥመው ሄሞሊይቲክ ከተባለው የደም እክል ይጠብቃቸዋል።

ይህ የጤና እክል የሚከሰተው በእርግዝና ወቅት ሲሆን የእናቶች ቀይ የደም ህዋሶች ከፅንሱ ጋር ሳይጣጣም ሲቀር የሚከሰት ነው።

በዚህ ጊዜ የእናት በሽታ የመከላከል ሥርዓት የሕፃኑን የደም ህዋሶች እንደ ባዕድ ጠላት በመቁጠር እነሱን ለመከላከል በሽታ መከላከያ ያመነጫል። ይህም በሕፃኑ ላይ ከፍተኛ የደም ማነስ፣ የልብ መድከም ወይም ሞት ያስከትላል።

እንደ አውሮፓውያኑ 1960ዎቹ አንቲ ዲ መከላከያ ከመገኘቱ በፊት ከሁለት ሕጻናት አንዱ ኤችዲኤፍኤን በተባለው በሽታ ይጠቁ ነበር።

የሃሪሰን ደም በአንቲ ዲ ለምን የበለጸገ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ሆኖም አንዳንድ ሪፖርቶች የ14 ዓመት ታዳጊ ሳለ የተቀበለው ከፍተኛ ደም ጋር የሚገናኝ እንደሆነ ያመለክታሉ።

በአውስትራሊያ ከ200 ያነሱ አንቲ ዲ ደም ለጋሾች ናቸው ያሉት።

እንደ አገሪቷ ቀይ መስቀል የደም አገልግሎት ከሆነ እነዚህ ደም ለጋሾች በየዓመቱ 45 ሺህ የሚጠጉ እናቶችንና ልጆቻቸውን እንደሚረዱ ይገመታል።

የደም አገልግሎቱ፣ አንቲ ዲ የበሽታ መከላከያን ከሃሪሰን እና ከሌሎች ለጋሾች የተገኘውን ደም እና የበሽታ መከላከያ ህዋስ በማባዛት በቤተ ሙከራ እንዲበለጽግ ከአውስትራሊያው ዋልተር ኤንድ ኢሊዛ ሃል የሕክምና ምርምር ተቋም ጋር እየሰራ ነው።

በምርምሩ ላይ የተሳተፉ ተመራማሪዎችም በቤተ ሙከራ የሚሰራው አንቲ ዲ በዓለም ላይ ያሉ ነፍሰጡር ሴቶችን ለመርዳት ጥቅም ላይ እንደሚውል ተስፋ ሰንቀዋል።

የደም አገልግሎቱ የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ዴቪድ ኢርቪንግ፣ አዲስ የህክምና መንገድ መፍጠር ለረዥም ጊዜ በጉጉት ሲጠብቅ የነበረ ነው ብለዋል።

ዳይሬክተሩ ጨምረውም በበቂ ጥራት እና ብዛት አንቲ ቦዲ የሚያመነጩ በመደበኛነት የሚለግሱ የደም ለጋሾች እጥረት መኖሩንም ጠቁመዋል።