ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ በ30 ሺህ ብር ዋስ ከእስር ተፈቱ

ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ በ30 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲለቀቁ በዛሬው ዕለት አርብ ሰኔ 03/2014 ዓ.ም. ፍርድ ቤት መወሰኑን ተከትሎ መፈታታቸውን ጠበቃቸው በሙሉ ታደሰ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ውሳኔውን ያስተላለፈው በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ከሰዓት በኋላ 9 ሰዓት ላይ ነው።

የዕለቱ ችሎት ሐሙስ ዕለት የተጠየቀውን የዋስትና ክርክር ሂደትን ላይ መርምሮ ብይን ለመስጠትም ነበር የተቀጠረው።

በዚህም መሰረት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል በ30 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስተላልፏል።

ትናንት ሐሙስ ሰኔ 02/2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ላይ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ በሽብርና በሌሎች ተደራራቢ ወንጀሎች ስለተጠረጠሩ ዐቃቤ ሕግ ክስ የመመስረቻ ጊዜ አስራ አምስት ቀን ይሰጠኝ ሲል ጠይቆ ነበር።

ጠበቃቸውም የሽብር ወንጀሉ በተለየ ሁኔታ ዋስትና የሚከለክል ስላልሆነ በዋስ እንዲፈቱ የመከራከሪያ ሃሳብ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቱም የመከራከሪያ ሃሳቦቹን ከሰማ በኋላ በሽብር አዋጁ 1176/ 2012 መሰረት ዋስትና በተለየ ሁኔታ የሚከልክል ባለመሆኑ በ30 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ውሳኔ ላይ ደርሷል።

ጠበቃቸው ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዛሬ ከሰዓትም በኋላ ጄኔራሉ ከማረሚያ ቤት ወጥተዋል።

ከሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ መሰወራቸው የተነገረው ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ሞክረዋል በሚል ተጠርጥረው እንደተያዙ ፖሊስ መናገሩን መዘገቡ ይታወሳል።

ከአዲስ አበባ በደኅንነት ኃይሎች በአስገዳጅ ሁኔታ ታፍነው በሄሊኮፕተር ወደ ባሕር ዳር ከተማ መወሰዳቸው የተነገረ ሲሆን፣ በወቅቱም ድብደባ እንደደረሰባቸው ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ጄነራል ተፈራ ተፈራ ማሞ ባለትዳር እና የአራት ልጆች አባት ናቸው።

ከሚኖሩበት ባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ የመጡት በእግራቸው ውስጥ የሚገኙትን ጥይቶች በተመለከተ የሕክምና ክትትል ለማድረግ እንደነበረም ባለቤታቸው ወ/ሮ መነን ኃይሌ ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ለዓመታት በከፍተኛ መኮንንነት ያገለገሉት ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ከአስር ዓመት በፊት መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ አሲረዋል በሚል ከሌሎች ወታደራዊ አመራሮች ጋር ተከሰው ለዓመታት በእስር ላይ ቆይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎም ከእስር ተለቀው በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።

በቅርቡም የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች ጦርነት ባነሱበት ወቅት የክልሉን ልዩ ኃይል በበላይነት ሲመሩ የነበሩ ሲሆን፣ ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ ከዚሁ ኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጋቸው ይታወሳል።