በሁለቱ ታዋቂ የኦሮምኛ ዘፋኞች መካከል የተፈጠረው ምንድን ነው?

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አካባቢ በኦሮሞ ማኅብረሰብ ዘንድ እውቅ በሆኑት ሁለት አርቲስቶች መካከል የተፈጠረው ክስተት የማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ በአንድ የምሽት መዝናኛ ስፍራ ባጋጠመው ክስተት አርቲስት ጫላ ቡልቱሜ ወጣቱ ድምጻዊን አንዱዓለም ጎሳን በጥይት ስለመምታቱ ተገልጿል።

ከክስተቱ በኋላ አርቲስት አንዱዓለም ከጫላ ቡልቱሜ በበተኮሰበት ጥይት መመታቱን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በለቀቀው ቪዲዮ የተናገረ ሲሆን፤ ጫላ ቡልትሜ ደግሞ አርብ ጠዋት ላይ በፌስቡክ ገጹ ባጋራው ጽሑፍ የግድያ ሙከራ ተፈጽሞብኛል ብሏል።

ቢቢሲ ስለክስተቱ ሁለቱንም አርቲስቶች አግኝቶ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

ፖሊስም በቦሌ ክፍለ ከተማ ስላጋጠመው ክስተት ምርመራ ጀምሮ እንደሆነ ዓርብ ዕለት ያቀረብነው ጥያቄ መልስ አላገኘም።

ዓርብ ነሐሴ 26/2015 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባይ መረጃው የለኝም ያሉ ሲሆን: ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 29/2015 ዓ.ም. መረጃ ለመጠየቅ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

ዓርብ ንጋት ላይ የሆነው ምን ነበር?

አርቲስት አንዱዓለም በቲክቶክ ገጹ ለሥራ በሄድኩበት የምሽት መዝናኛ ክበብ ውስጥ ለመዝናናት በመጣው ጫላ ቡልቱሜ በጥይት ተመትቻለሁ ያለ ሲሆን፤ ጫላ ቡልቱሜ ደግሞ በፌስቡክ ገጹ “በፋኖ ቡድን የግድያ ሙከራ” ተፈጽሞብኝ እንዲሁም የግል ተሸከርካሪዬንም ሰብረዋል ብሏል።

ቢቢሲ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ምንጮች አነጋግሮ እንደተረዳው ከጫላ ቡልቱሜ በተተኮሰ ጥይት ከአንዱዓለም በተጨማሪ ሌላ አንድ ግለሰብ በጥይት ተመትቶ ክፉኛ ተጎድቷል።

በጥይት የተመታው ግለሰብ አሁን ያለበትን ሁኔታ ማወቅ ባይቻለንም እግሩን የተመታው አርቲስት አንዱዓለም ግን የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ከተደረገለት በኋላ ወደ ቤቱ ተመልሷል።

አንዱዓለም በቲክቶክ ገጹ በኦሮምኛ ዓርብ ምሽት ቦሌ ቀነኒሳ ሆቴል ውስጥ በሚገኝ የምሽት መዝናኛ ስፍራ ለሥራ መሄዱን ይናገራል።

“የዚያን ቀን በቀነኒሳ ሆቴል ሥራ ነበረኝ። ጫላ ደግሞ ለመዝናናት መጣ” የሚለው አንዱዓለም፤ አርቲስት ጫላ ወደ መዝናኛ ስፍራው ሲመጣ ጦር መሳሪያ ይዞ እንደነበረ ተናግሯል።

ጫላ ይዞት ከመጣው መሳሪያ ጋር በተገናኛ በምሸት መዝናኛው ካሉ ጠባቂዎች ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብቶ እንደነበረ ይገልጻል።

“መሳሪያውን ተቀብለውት ነበር። ወደ ውጪ ይዘውት ወጡ። መሳሪያው ሊመለስልኝ ይገባል ሲለኝ እኔም መልሱለት ብዬ አስመለስኩለት። በዚህ መሃል ከሌላ ቦታ ከመጡ ሰዎች ጋር ተጋጨ። አንዱን በጥይት መትቶ ጣለው። ተመትቶ ከወደቀ በኋላ ጥይት ሲተኮስ ነበር። አትግደለኝ ሲለው (ተመትቶ የወደቀው) እኔ አላስቻለኝም መሃል ገብቼ ተው አልኩት” በማለት አንዱዓለም ዓርብ ምሽት የነበረውን ሁኔታ ያስረዳል።

በመቀጠልም “አንተም ብትሆን ዞር በል ብሎ ወደ እኔ ሽጉጡን አዙሮት ተኮሰብኝ. . . በዚያ ቅጽበት የሰው ሕይወት ሊያልፍ ይችል ነበር። በጥይት የተመታው ከባድ ጉዳት ደርሶበታል። እኔን ግን ፈጣሪ አትርፎኛል” ብሏል።

አንዱዓለም ሁለት ጥይት ተተኩሶበት አንዱ ሰውነቱን ሳያገኘው የለበሰውን ሱሪ በስቶ ማለፉን እና ሁለተኛው ግን የታችኛው የእግሩን ክፍል እንደመታው ተናግሯል።

“ሁለቴ ነው የተኮሰብኝ። አንዱ በሱሪዬ መሃል ነው ያለፈው። አንዱ እግሩን አግኝቶታል” ብሏል።

ከክስተቱ በኋላ አንዱዓለም ጎሳን እግሩ በፋሻ ተጠቅልሎ እንደሚገኝ እና የደረሰበት ጉዳት ቀላል የሚባል እንደሆነ በቤቱ ሄደው ከጠየቁት አርቲስቶች መካከል አንዱ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ጫላ ቡልቱሜ በበኩሉ ከክስተቱ በጥቂት ሰዓታት ልዩነት በፋኖ ቡድን አባላት የግድያ ሙከራ ተፈጸመብኝ ብሎ በፌስቡክ ካጋራው ጽሑፍ ውጪ እስካሁን ያለው ነበር የለም።

ጫላ ቡልቱሜ በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ “በፋኖ ቡድን አባላት ከተሞከረብኝ የግድያ ሙከራ ተርፊያለሁ” ያለ ሲሆን መኖሪያ ቤቱ እስኪደርስ ድረስ “ተከታትለውኝ መኪናዬን ሰባብረዋል” ያለ ሲሆን ከመኪና ውስጥ የግል ንብረት መወሰዱን ገልጿል።

አርቲስት ጫላ በቅርቡ በርካታ የግድያ ሙከራዎች እንደተፈጸሙበት የገለጸ ሲሆን: በዚህ የፌስቡክ ገጹ ጽሑፍ ላይ ከአርቲስት አንዱዓለም ጋር ስለገባው ግጭት ያለው ነገር የለም።

ጫላ ቡልቱሜ ከሐሙስ ለአርብ አጥቢያ ባጋጠመው ክስተት ተጎድቷል ያለውን የተሸከርካሪ ምስል አጋርቷል። ይሁን እንጂ ማንነታችን አይገለጽ ያሉ እና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች: በመኪናው ላይ ያለው ጉዳት ከዚህ ቀደም ባጋጠመ አደጋ የተጎዳ እንጂ ዓርብ ዕለት ከነበረው ክስተት ጋር የሚያገናኘው የለም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ስለ ሁለቱ አርቲስቶች በአጭሩ

አርሰቲስት ጫለ ቡልቱሜ ከአምስት ዓመት በፊት በኦሮሚያ በኢህአዴግ አስተዳደር ላይ የተነሳውን ተቃውሞ ባቀጣጠሉ የተቃውሞ ሙዚቃዎቹ ትልቅ ዝናን አግኝቷል።

አርቲስቱ በስደት ሆኖ የተቃውሞ መነሻ የነበረውን የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላንን በተመለከተ ያዜማቸው ዜናማዎች ብዙዎች ጋር ደርሰው ነበር።

አርቲስት ጫላ ኬንያ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ በስደት ከኖረ በኋላ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ወደ አገር ተመልሷል።

አርቲስቱን በቅርብ እናውቀዋለን የሚሉ ምንጮች እንደሚሉት ጫላ ወደ አገር ከተመለሰ በኋላ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር ቅርብ የሆነ ወዳጅነት በመመሥረት በንግድ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ንብረት ማፍራት መቻሉን ይገልጻሉ።

አርቲስት አንዱዓለም ጎሳ ደግሞ በቅርቡ ብቅ ካሉ እና ትልቅ ተቀባይነት ካገኙ ወጣት የኦሮሞ ድምጻውያን መካከል አንዱ ነው። አንዱዓለም ከኦሮሞ አርቲስቶች በመድረክ ሥራዎቹ ትልቅ ስም ያለው ወጣት አቀንቃኝ ነው።

አንዱዓለም ዩቲዩብ ላይ የተለቀቁ ነጠላ ዜማ የሙዚቃ ክሊፖቹ በሚሊዮኞች የሚታዩለት አቀንቃኝ ነው።