የዓለማችን ለኑሮ ምቹ የሆኑ ምርጥ አስር ከተሞች

አንድ ከተማ ለኑሮ ምቹ ነው ሲባል ምን ዓይነት መስፈርቶችን ያካትታል?

አንድ ከተማስ ለኑሮ ተመችቶኛል ሲሉ ምን ሲሟላልዎት ነው?

የታዋቂው ኢኮኖሚስት ጋዜጣ አካል እና ምርምሮችን እንዲሁም ትንተናዎችን የሚያዘጋጀው ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት ‘ግሎባል ሊቨቢሊቲ ኢንዴክስ’ በየዓመቱ ለነዋሪዎች ምቹ የሆኑ ከተሞችን ደረጃ ያስቀምጣል።

ለዚህም የዓለማችን 173 ከተሞችን ገምግሞ ደረጃ የሚሰጥ ሲሆን፣ በዘንድሮው ግምገማውም የኦስትሪያዋ ዋና ከተማ ቪየና በአንደኛነት ስፍራ ተምጣለች።

በምቹነት በከፍተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የምዕራባውያኖቹ ከተሞች ናቸው።

ተቋሙ ከተሞቹን ሲመርጥ መስፈርት ያደረጋቸው መረጋጋት፣ የጤና ሥርዓት፣ ባህል እና ከባቢየዊ ሁኔታቸውን እንዲሁም የትምህርት እና የመሠረተ ልማት ሽፋንን በማጤን ነው።

የዓለም አቀፉ የዋጋ ግሽበት እንዲሁም በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የተከሰተው ጦርነት የእህል እና የምግብ ገበያን አለመረጋጋት ቢያስከትልም፣ የተመረጡት ከተሞች እነዚህን ችግሮች ተቋቁመው ለነዋሪዎቻቸው የተመቸ ኑሮን መቀየሳቸውን አመልክቷል።

በደረጃው በታችኛው ስፍራ ላይ የተቀመጡት አፍሪካዊዋ የሊቢያ ከተማ እና በጦርነት እየተናወጠች ያለቸው ሶሪያ ለነዋሪዎች እንዴት ፈታኝ እንደሆኑ በሪፖርቱ ተካቷል።

በዘንድሮው በዓለማችን ምቹ ከተማነት በአስሩ ውስጥ ከተካተቱ መካከል ቢቢሲ የስድስቱን ከተማ ነዋሪዎች በማነጋገር የከተሞቹን ምቹነት በነዋሪዎቹ ዐይን ቃኝቷል።

ቪየና፣ ኦስትሪያ

የኦስትሪያ መዲና ቪየና በዓለማችን ካሉ ምቹ ከተሞች በቁንጮነት ስፍራ ስትቀመጥ የመጀመሪያዋ አይደለም።

ከሁለት ዓመት በፊት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሙዚየሞቿ እና ሬስቶራንቶች ላይ ያስቀመጠችው ገደብ ተጽእኖ አድርሶባት የአንደኛነቱን ስፍራ ብታጣም፣ በተደጋጋሚ አንደኛነትን በመጨበጥ የምትታወቅ ናት።

ከተማዋ ከፍተኛ መረጋጋት ያለባት፣ የጤና፣ የትምህርት እና የመሠረተ ልማት አቅርቦቷ ፍጹም በሚባል ሁኔታ የተሟሉ እንደሆኑም ነዋሪዎቿ ይመሰክሩላታል።

“በአንድ ከተማ ውስጥ ሁሉን የሚያገኙበት፤ የተሟላ ኑሮ የሚኖሩባት ስፍራ ናት” ሲሉም ኮንስታንቲን ፊሊፖ የተሰኘው ታዋቂ ሬስቶራንት እና የወይን መጠጥ ቤትን ከምግብ አብሳይ ባለቤታቸው ጋር በጋራ የሚያስተዳድሩት ማኑኤላ ፊሊፖ ይናገራሉ።

የዘመናትን ታሪክ ጊዜ ሳይገድባቸው በሚነግሩት የኪነ ህንጻዎቿ፣ አስተማማኝ በሆነው የሕዝብ ትራንስፖርት ሥርዓቷ፣ ተመጣጣኝ የህጻናት እንክብካቤ አገልግሎት ለነዋሪዎቿ ሕይወትን ቀለል አድርገውላቸዋል።

በተጨማሪም በርካታ ዐይን የሚያስደምሙ ካፌዎች፣ ቲያትር ቤቶች እና በከተማ ዳርቻዎች ያሉ የወይን ፋብሪካዎች ሁልጊዜ የመዝናኛ ቦታ ላይ እንዳሉ እንዲሰማዎ ያደርጋሉ ይላሉ ማኑኤላ።

አክለውም “አንዳንድ ጊዜ ሥራ ላይ ስንጠመድ እና ለረጅም ጊዜ ወደሌሎች አካባቢዎች ሳንጓዝ ስንቀር ላናስተውላቸው እንችላለን። ነገር ግን ከተማዋን ቃኘት ስናደርግ ሁሉ ነገር በደጃችን መሆኑን እናያለን።”

ለሌላኛው ነዋሪ እና ዳስ ትግራ በተሰኘው ሆቴል የሽያጭ እና ግብይት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ሪቻርድ ቮስ ከተማዋ ለኑሮ ምቹ ናት የምትባልበት ዋነኛ ምክንያት በከተማዋ የበለጸገ ባህል፣ ታሪክ እንዲሁም በርካታ ትዕይንቶች መኖራቸው ነው።

“ቪየና የአስደናቂና ታሪካዊ የኪነ ህንጻ ባለቤት ናት። ከእነዚህም ውስጥ የሾንብሩን ቤተ መንግሥት፣ ሆፍበርግ እና የቪየና ማዘጋጃ ቤት አስደማሚ ከሆኑት መካከል ናቸው” ብለዋል።

“በተጨማሪም ከተማዋ በሙዚቃ ባህሏ ስመ ጥር ናት። በዓለም ላይ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጣቸው የሙዚቃ አቀናባሪዎቹ ሞዛርት፣ ቤትሆቨን እና ስትራውስን በዚህች ከተማ ነው ይኖሩ የነበሩት” ይላሉ።

ነዋሪዎቹ እነዚህን የባህል አሻራዎች በከተማዋ በሚገኙት በርካታ ሙዚየሞች፣ ቲያትር ቤቶች እና የኦፔራ ሙዚቃ ስፍራዎች ውስጥ በቀላሉ ያገኟቸዋል።

የቪየና የምግብ ባህሏም የበለጸገ መሆኑን የሚናገሩት እኚሁ ነዋሪ ለአዳዲስ ጎብኚዎችም እንደ ከጥጃ ሥጋ የሚሰራው ዊነር ሺኒትዝል፣ ሳቸርቶሬ የተሰኘው ጣፋጭ የቸኮሌት ኬክን መሞከር አይርሱ ይላሉ። በተጨማሪም በ16ኛው ክፍለ ዘመን እንደተመሠረተ የሚነገርለትን ናሽማርክት ገበያን እንዲጎበኙም ይመክራሉ።

ሜልበርን፣ አውስትራሊያ

የአውስትራሊያዎቹ ከተሞች ሜልበርን እና ሲድኒ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የጤና ሥርዓታቸው ከፍተኛ ጫና ውስጥ ገብቶ ነበር። ለረጅም ጊዜ ገደቦች በመጣላቸው ደረጃቸው አሽቆልቁሎ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት አንሰራርተው የምቹነት ስፍራቸውን መልሰው ይዘዋል።

በተለይም የሜልበርን ከተማ የአገሪቱ የባህል ማዕከል እንደሆነች ነዋሪዎች የሚመሰክሩላት ሲሆን፣ ዘንድሮም በሦስተኛ ስፍራ ተቀምጣለች።

“ሜልበርን አስደማሚ የምግብ ትዕይንት፣ ባህላዊ ጥበቦች፣ እግር የማያሳርፉ ዝግጅቶች እና መስህቦች አላት። እንደ አውስትራሊያ ፎርሙላ 1 እና ግራንድ ፕሪክስ ያሉ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮችንም በማስተናገድ ከዓመት እስከ ዓመት የደመቀች ያደርጋታል” ሲሉ የሚናገሩት ኬሪየር ሶሉሽንስ የተሰኘ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋች የሆኑት ጄን ሞሬል ናቸው።

በከተማዋ ውስጥም መዘዋወር ቀላል ነው። በመላዋ ከተማዋ፣ በየትኛውም ሰዓት በቀላሉ በባቡር ተሳፍሮ መንቀሳቀስ ይችላሉ። በዓለም ታዋቂ የሆኑ የባሕር ዳርቻዎች እና የወይን እርሻዎችም መዳረሻ ናት።

ከካሊፎርኒያ የመጡት ጦማሪ ኪም ኮነር በኩላቸው ከሌሎች የአውስትራሊያ ከተሞች ሜልበርን ለምን የተመረጠች እንደሆነ ይናገራሉ።

“የሲድኒ ከተማ ገና ሲያዩዋት በከፍተኛ ሁኔታ ያስደምምዎታል። የባሕር ዳርቻዎቿ፣ ኪነ ህንጻዋ እንዲሁም የከተማዋ አጠቃላይ እይታ ቀልብን ለመሳብ ብዙ ጊዜ አይወስድም። ነገር ግን ሜልበርን ለየት ትላለች። ሜልበርን በዋነኝነት መልክዓ ምድሯ ሳይሆን ያላት ውብ ባህል ነው ከፍተኛ ፍቅር የሚያሳድረው” በማለት ‘አድቬንቸር ኤንድ ሰንሴትስ’ የተሰኘ ድረ ገጽ ላይ የሚጽፉት ኪም ያስረዳሉ።

አክለውም “በቀለማት ባሸበረቀ ጎዳና ላይ በምትገኝ ትንሽ ካፌ በሕህይወትዎ ቀምሰውት የማያውቁት ምርጥ ቡና ሲቀርብልዎት ነው የሜልበርንን የልብ ምት የሚያገኙት። በከተማዋ ዙሪያ ያሉ ምግብ ቤቶች የሚያቀርቡት ጣፋጭ ምግቦች እጅ ያስቆረጥማሉ። በከተማዋ ውስጥ ምስጢራዊ በሆኑ በሮች አልፈው የሚያገኟቸው የኮክቴል መጠጥ ቤቶች ደግሞ ሌላ ድምቀት ናቸው” ይላሉ።

ኪም ከሲድኒ ይልቅ የሜልበርን ነዋሪዎች እንግዳ ተቀባይ እና ሰላምተኛ ሆነውም አግኝተዋቸዋል።

“ሜልበርናውያን ሰላምተኛ፣ እንግዳ ወዳጅ እና ተግባባቢ ናቸው” የሚሉት ኪም፣ ለሰው መድኃኒቱ ሰው ነው የሚለው ብሂልም በሜልበርን ስላዩት ከተማዋን ለኑሮ ተመራጭ አድርጓታል ይላሉ።

ቫንኮቨር፣ ካናዳ

ሦስቱ የካናዳ ከተሞች ካልጋሪ፣ ቶሮንቶ እና ቫንኮቨር በዘንድሮው ምርጥ ለኑሮ ምቹ በሆኑ አስር ከተሞች ውስጥ ተካተዋል። ቫንኮቨር ከሌሎች ከተሞች በላቀ በአምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፣ ነዋሪዎችም ስለ ቫንኮቨር ሲያወሩ በፍቅር ነው።

“ቫንኮቨር በተፈጥሮ ሃብቷ የታደለች ናት። በዛፎች የተሞላች፣ ባሕር የሚሻገርባት ከተማ ናት” የሚለው የከተማዋ ነዋሪ እና አነስተኛ የንግድ ድርጅት ባለቤት የሆነው ቶኒ ሆ ነው።

የተለያዩ መልክዓ ምድሮችን የታደለችው ቫንኮቨር በመረጡት በአውቶብስ፣ በብስክሌት፣ በባቡር ወይም በጀልባ ሊንቀሳቀሱባት ይችላሉ።

ቫንኮቨር የበርካታ ባህል እና ሕዝቦች መገኛ መሆኗን የሚገለጸው በምግቧ ነው።

የኢትዮጵያውን እንጀራ በጥብስ ቢፈልጉ ወይም ወይም የቲቤት ሞሞስ የተሰኘውን ጣፋጭ ምግቦች ያገኛሉ።

የተለያዩ ምግቦች፣ ባህሎች እና ቋንቋዎችም ይነገሩባታል። ለህጻን ልጅ አባቱ ቶኒ ከተማዋ ያሏት በርካታ ፓርኮች እና የባሕር ዳርቻ መዝናኛዎች ከልጃቸው ጋር ሄደው ለመዝናናትም ተመራጭ ናት።

ካናዳ ባላት ክፍት የኢሚግሬሽን ፖሊሲዎችም ምክንያት በርካታ የውጭ አገራት የንግድ ባለቤቶችም መዳረሻቸው አድርገዋታል።

“እንደ ሥራ ፈጣሪ እና የክሮሺያ ስደተኛ የንግድ እድገትን የምታበረታታ እንዲሁም የውጭ አገር ዜጎችን ተቀባይ ከተማ እየፈለግኩ ነበር” የሚሉት ሮኬትፕላን የተሰኘው የሞባይል መተግበሪያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጆ ቶልዝማን ናቸው።

“የቫንኮቨር ከተማ ቢዝነስ ለመጀመር ፖሊሲዋ ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝቡም ቀናነት ተመራጭ ያደርጋታል። በእያንዳንዱ እርምጃዎች ድጋፍ ይሰጥዎታል። አገልግሎትም ያገኛሉ። የንግዱ ማኅበረሰብ በጣም አጋዥ እና ሁሉን አካታች ነው” በማለትም ያስረዳሉ።

ከንግድ ሥራው ባሻገር ጆ እንደሚሉት በውቅያኖስ እና በተራሮች የታጀበው የከተማዋ መልክዓ ምድር የአዕምሮ እረፍትን ይሰጣል።

ኦሳካ፣ ጃፓን

የጃፓኗ ከተማ ኦሳካ በ10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ብቸኛዋ የእስያ ከተማ ናት። ከተማዋ ባላት የተረጋጋ ሁኔታ፣ በጤና ሥርዓቷ እና በትምህርት ዘርፉ ለነዋሪዎቿ በምትሰጠው ሽፋንም የመረጃ ሰብሳቢውን 100 ነጥቦች አግኝታለች።

በበርካታ ከተሞች የዋጋ ግሽበት የዓለማችንን በርካታ ቤተሰቦች ኑሮን እየፈተነ ባለበት በዚህ ወቅት በከተማዋ የሚቀርቡ ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ መገኘታቸው ለነዋሪዎች ተመራጭ ከተማ አድርጓታል።

“በኦሳካ ውስጥ ያለው የቤት ኪራይ ከሌሎች የጃፓን እና የዓለም ከተሞች ጋር ሲወዳደር ውድ አይደለም” ሲሉም ከቫንኮቨር የመጡት እና በአሁኑ ወቅት የኦሳካ ነዋሪ የሆኑት ሸርሊ ዣንግ ይናገራሉ።

“ለቤቴ የምከፍለው የቤት ኪራይ በወር 700 ዶላር ገደማ ሲሆን ይህም የውሃ፣ ኢንተርኔት እና ሌሎች የጥገና ወጪዎችን ያጠቃልላል። የመኖሪያ ቤቴ አዲስ እና ንጹህ ነው። ቀድሞ በምኖርበት የቫንኮቨር ከተማ ውስጥ እንዲህ ያለ ቤት ለመከራየት ቢያንስ 1 ሺህ 200 ዶላር በወር መክፈል ያስፈልጋል” ይላሉ።

የኦሳካን ከተማ በነዋሪዎች የሚያስወድዳት ሌላኛው ነገር ወጣ ብለው በሬስቶራንቶች ቢመገቡ ኪስዎን አለመጉዳቱ ነው።

“በትውልድ ስፍራዬ ዩናይትድ ኪንግደም ሬስቶራንቶች እየወጣሁ ልመገብ ቢሉ ገቢዎን በእጅጉ ሊመናመን ይችላል። በኦሳካ ግን ጥራት ባላቸው እና በቅንጦት በተሞሉ ሬስቶራንቶች በተመጣጣኝ ዋጋ መገገብ ይችላሉ። እርስዎን አይሰልችዎት እንጂ ከፈለጉ በየቀኑ በሬስቶራንቶች ቢመገቡ ወጪው ይህን ያህል አይደለም” ሲሉም ጀምስ ሂልስ የተሰኙ ነዋሪ ያስረዳሉ።

ኦሳካ ከሌሎች ተመሳሳይ ትልልቅ ከተሞች በበለጠ ፀጥታ እና መረጋጋት የሰፈነባት በመሆኗ ሸርሊ ደኅንነት ይሰማኛል ይላሉ።

“በእኩለ ሌሊት እንኳን ብቻዬን መንገድ ላይ ብራመድ ምንም ስጋት አይሰማኝም። ቦርሳዬ ይሰረቃል ብሎ መጨነቅ የለም። ሰላም የተሞላባት ከተማ ናት” ይላሉ ሸርሊ።

በከተማዋ ለመንቀሳቀስም ሆነ ከከተማዋ ወጥተው እንደ ኪዮቶ፣ ናራ እና ኮቤን ለመጎብኘት ከፈለጉ የባቡር አገለግሎቱ ነገሮችን ቀለል ያደርግልዎታል።

ኦክላንድ፣ ኒውዚላንድ

ከኦሳካ ጋር በ10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው የኒውዚላንዷ አክላንድ ከተማ ካለፈው ዓመት 25 ደረጃዎችን ተሻግራ ነው በዚህ ስፍራ የደረሰችው።

ከተማዋም ሆነ አገሪቷ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እገዳዎች እና መመሪያዎችም ጋር በተያያዘ ነበር ደረጃዋ አሽቆልቁሎ የነበረው።

ምርጥ የተባለ የትምህርት ሥርዓትን ዘርግታለች የተባለችው ይህች ከተማ፣ ያላት ባህል እንዲሁም ውብ ተፈጥሯዊ መልክዓ ምድር ነዋሪዎች እንዲወዷት አድርጓታል።

“የሚያምሩ እና የተከለሉ የባሕር ዳርቻዎችን ለማግኘት የኦክላንድ ነዋሪዎች ብዙ ርቀት መሄድ አይጠበቅባቸውም። በየደጃፋችን አስደናቂ የሆኑ የውሃ ውስጥ መጫወቻዎች አሉን። ከተማዋ ለነዋሪዎቿ በርካታ የሚደሰቱበትን መንገዶች ቀይሳለች። በተፈጥሮ ልምላሜ የታደለች በመሆኗም ከተማ ውስጥ ያሉ ሳይመስልዎት የየዕለቱን ሁኔታ ዘና ባለ መልኩ እንዲያሳልፉ ያደርግዎታል” ይላሉ ሜጋን ላውረንስ የተሰኙ ፀሐፊ።

የኒውዚላንድ ትልቋ ከተማ አክላንድ በቅርቡ የተጠናቀቀውን የ2023 የሴቶች የዓለም ዋንጫን ጨምሮ የዓለም አቀፍ ዝግጅቶች መዳረሻም ናት።

“ምርጥ የሚባሉ ኮንሰርቶች፣ ትርዒቶች እና ስፖርታዊ ውድድሮችን እንታደማለን። ግብፅ በፈርኦኖች ጊዜ የነበራትን ታላቅነት ለማየትም ወደ ኦክላንድ ሙዚየም እሄዳለሁ” ሲሉም የጉዞ ኩባንያ የሆነው ኤኤቲ ኪንግስ ባልደረባ ግሬግ ማሬት ያስረዳሉ።

በተጨማሪም የከተማዋ ወደብ አስደናቂ ውበት የሚሰጧት ሲሆን፣ የተንቆጠቆጡ ጀልባዎችም “የአሳሾች ከተማ” የሚል ቅጽል ስም አሰጥቷታል። ከተማዋን ለሚጎበኙም የባሕር ታሪኳን ለመረዳት የኦክላንድ የባሕር ሙዚየምን እንዲጎበኙ ይመክራሉ።

ኒውዚላንድ የተለያዩ አገራት ዜጎች መኖሪያ እንደመሆኗ በርካታ ዓይነት ምግቦችን ያገኛሉ። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የአገሬው ተወላጅ የሆኑት ኪዊዎች ሰው ወዳጅነት ልብዎ ላይ ይቀራል።

“ኪዊዎች ደግ ናቸው። ሰዎችን ለመርዳት አይሰለቹም። ጎዳናዎችን ሲያቋርጡ ቢያውቁዎትም ባያውቁዎትም ፈገግ ብለው ሰላም ይሉዎታል። በፈገግታቸውም እንደተቀበሉዎት ያሳይዎታል” ይላሉ።

የዓለማችን ለኑሮ ምቹ የሆኑ ምርጥ አስር ከተሞች በደረጃ

  • ቪየና፣ ኦስትሪያ
  • ኮፐንሃገን፣ ዴንማርክ
  • ሜልቦርን፣ አውስትራሊያ
  • ሲድኒ፣ አውስትራሊያ
  • ቫንኮቨር፣ ካናዳ
  • ዙሪክ፣ ስዊዘርላንድ
  • ካልጋሪ፣ ካናዳ
  • ጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ
  • ቶሮንቶ፣ ካናዳ
  • ኦሳካ፣ ጃፓን / ኦክላንድ፣ ኒውዚላንድ