ኤርትራውያን ያስነሱት ሁከት “ቀይ መስመሩን ያለፈ ነው”- ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ

በእስራኤል መዲና ቴልአቪቭ ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች በጎራ ተከፋፍለው ያስነሱት ሁከት “ቀይ መስመሩን” ያለፈ እንደሆነ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተናገሩ።

በርካቶች ተጎድተውበታል እንዲሁም ከፍተኛ የንብረት መውደም ተከስቶበታል በተባለውም የቅዳሜ ነሐሴ 27/ 2015 ዓ.ም ግርግር ተሳትፈዋል የተባሉ ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎችን በአስቸኳይ ከአገር ማባረርን ጨምሮ ጠንከር ያለ እርምጃም ይወሰድባቸዋል ተብሏል።

በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል በተነሳው ግርግር እና ከፖሊስ ጋርም በተፈጠረው ግጭት ከ170 ሰዎች በላይ ቆስለዋል።

ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ዱላ፣ ድንጋይ እና ሌሎችም መሣሪያዎችን በመጠቀም እርስ በርስ የተወራወሩ ሲሆን ይህንንም ሁከት ኔታንያሁ “ቀይ መስመሩን ያለፈ” እና “ደም መቃባት የታየበት” ሲሉ ነው የገለጹት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሕገ ወጥ ሰርጎ ገቦች” ሲሉ የገለጿቸውን አፍሪካውያን ስደተኞችን ከአገር የማስወጣት አዲስ ዕቅድም እንዲዘጋጅ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

በሌሎች አገሮች የታየው በኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎች እና ደጋፊዎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች ከሰሞኑ በእስራኤል፣ ቴልአቪቭ ተከስቷል።

ለዚህም መነሻ የሆነው ተቃዋሚዎች በኤርትራ ኤምባሲ አዘጋጅነት የሚካሄደው ፌስቲቫል እንዲሰረዝ የእስራኤል ባለሥልጣናትን መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው።

ፌስቲቫሉ በተዘጋጀበት ስፍራ ዙሪያ የነበረውን የፖሊስ አጥር ሰባብረው በመግባት ከፍተኛ የሆነ ንብረት መውደሙ ተገልጿል።

በቴልአቪቭ የተከሰተውን አመጽ ለመቆጣጠር የእስራኤል ፖሊሶች ጥይት፣ አስለቃሽ ጭስ እና የፕላስቲክ ጥይቶችን የተኮሱ ሲሆን በፈረስ ላይ የተቀመጡ ፖሊሶችም ኤርትራውያኑን በመግፋት ለመበተን ሲሞክሩም ታይተዋል።

ፖሊስ በኤርትራውያን ላይ ጥይት መተኮሱን ተከትሎ ሕጋዊ አሰራር የተከተለ ስለመሆኑ ምርመራ ተከፍቷል ተብሏል።

በርካታ አባላቱ እንደቆሰሉበት ያስታወቀው የእስራኤል ፖሊስ በበኩሉ ሕይወታቸው አደጋ ላይ እንደወደቀ ተሰምቷቸዋል ብሏል።

ቅዳሜ የእስራኤል ጎዳናዎች የውጊያ ግንባር የመሰሉ ሲሆን በርካቶች እንጨት፣ ዱላ፣ ፌሮ ይዘው እርስ በርስ ሲደባደቡ ታይተዋል።

እርስ በርስ ከነበረው ድብድብም በተጨማሪ የሱቆች መስታዎችን እንዲሁም መኪናዎችን መሰባበራቸውም ተዘግቧል።

ኤርትራን በፈላጭ ቆራጭነት እየገዙ ባሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝ ላይ ከዚህ ቀደም በዳያስፖራው ተቃውሞች ቢሰሙም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ግን መልኩን እየቀየረና በደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች ደም መፋሰሶች እየታዩ ነው።

ቅዳሜ ዕለትም የማዕከላዊ ቴልአቪቭ ጎዳናዎች ለበርካታ ሰዓቶች የጦርነት ቀጣና መስሎ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ከጎዳናዎች ድብድብ በተጨማሪም የፖሊስ ሄሊኮፕተሮች በሰማይ ላይ እያንዣበቡ፣ ከፍተኛ የሳይረን ጩኸቶች እየተሰሙ እንደነበር ነው ነዋሪዎች የገለጹት።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተነሳው ሁከት ከዚህ ቀደም የእስራኤል ፖለቲከኞች መወዛገቢያ የሆነው የስደተኞች ጉዳይ ወደ አጀንዳው እንዲመለስ አድርጎታል።

የእስራኤል ፓርላማ የአገሪቱን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሥልጣን የሚገድብ አወዛጋቢ ሕግ ባጸደቀበት ማግስት ነው የአፍሪካውያን ስደተኞች ጉዳይ እንደገና መወያያ የሆነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እና ሌሎች በካቢኔያቸው የሚገኙ የምክር ቤት አባላት ስደተኞችን ከእስራኤል ለማስወጣት የተሞከረውን እርምጃ የከለከለውን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲወቅሱ ተሰምተዋል።

“በአሁኑ ወቅት በደቡብ ቴልአቪቭ እና በሌሎች ቦታዎች ሕገ ወጥ ሰርገቦች ከባድ ችግር እያስከተሉ ነው” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በእሑዱ ልዩ የመንግሥት ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።

“በሁከት አነሳሺዎቹ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወሰድ እንፈልጋለን። ተሳታፊዎቹን በአስቸኳይ ከአገር ማባረር ጀምሮ” ብለዋል።

ሚኒስትሮቻቸውም “ሁሉንም ሕገ ወጥ ሰርጎ ገቦች ለማስወገድ” ዕቅድ እንዲያቀርቡላቸውም ጠይቀዋል።

የቀኝ አክራሪው የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ጃቪር በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ የገቡ ስደተኞች በጅምላ ከአገር የሚባረሩበትን ሂደት ለማስጀመር እስራኤል በሰብዓዊ ክብር እና ነጻነት ያላትን መሰረታዊ ሕግን የሚሽር ረቂቅ ሕግ ለማዘጋጀትም አቅደዋል።

በእስራኤል ውስጥ ወደ 18 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች እንዳሉ ይገመታል።

በርካቶቹም ከዓመታት በፊት የግብጽን የሲናይ ባህረ ገብ መሬት አቋርጠው በህገወጥ መንገድ የገቡ ናቸው። ስደተኞቹ በአለማችን በጭቆና ከምትታወቀው ኤርትራ አስገዳጅ የሆነውን ብሔራዊ ውትድርና እና ጭቆናን አምልጠው እንደተሰደዱም ይናገራሉ።

ምንም እንኳን የኤርትራን አገዛዝ የሚደግፉ ኤርትራውያን ለስደተኞች የሚደረገው ዓለም አቀፍ ከለላ የሚያስፈልጋቸው ባይመስሉም የእስራኤል ባለሥልጣናት አገዛዙን ፈርተው ጥገኝነት በጠየቁት እና በደጋፊዎች መካከል ልዩነት ሲያደርጉ አልተሰሙም።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ነጻ የወጣችበትን 30 ዓመት ባከበረችበት ወቅት በተለያዩ አገራት የሚገኙ ዲያስፖራዎች ዕለቷን አክብረዋታል።

ነገር ግን በእስራኤል እንደተከሰተው በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካም በአንዳንድ ስፍራዎች ሁከቶች ተከስተዋል።

ባለፈው ወር በካናዳዋ ቶሮንቶ ለሦስት ቀናት የሚቆየው የኤርትራውያን የባህል ፌስቲቫል ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መጋጨታቸውን ተከትሎ ተሰርዟል።