ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኔታኒያሁ በሁከት የተሳተፉ ኤርትራውያን እንዲባረሩ እና አፍሪካውያን ስደተኞችን ለማስወጣት ዕቅድ እንዲወጣ አዘዙ
ትናንት ቅዳሜ ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም. ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች በቴል አቪቭ ከባድ ሁከት ፈጥረው በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አፍሪካውያን ስደተኞች በሙሉ ‘በአስቸኳይ’ ከእስራኤል ለማባረር እቅድ እንዲወጣ አዘዙ።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ትናንት በቴል አልቪቭ ሁከት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ኤርትራውያን በአስቸኳይ ከአገር እንዲባረሩ እፈልጋለሁ ካሉ በኋላ በአገሪቱ ያሉ አፍሪካውያን ስደተኞችን በሙሉ ከአገር ለማባረር ዕቅድ እንዲወጣ ትዕዛዝ መስጠታቸውን አሶሲዬትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ትናንት ቅዳሜ በእስራኤል አገር የኤርትራ ባሕር ፌስቲቫል ዝግጅት ጋር በተያያዘ የኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች በፈጠሩት ሁከት ከአገሪቱ ፖሊስ ጋር ተጋጭተው ጉዳት ደርሷል።
ሁከቱ የተፈጠረው በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች የተዘጋጀ ነው የተባለውን ዝግጅት ለማወክ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎች ፌስቲቫሉ ወደሚዘጋጅበት ቦታ በኃይል ከገቡ በኋላ ነው።
በእስራኤል መዲና የተከሰተውን ሁከት ለመቆጣጠር የእስራኤል ፖሊስ ጥይት፣ አስለቃሽ ጭስ እና የፕላስቲክ ጥይቶችን በመቶዎች በሚቆጠሩ ኤርትራውያን ላይ ለመተኮስ ተገዷል።
ቀደም ሲል የጠቅላይ ሚንስትር ኔታኒያሁ ጽ/ቤት ትናንት ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም. ምሽት ላይ በሁከቱ የተሳተፉ ኤርትራውያንን ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ ሚንስትሮችን በአባልነት የሚያቅፍ ግብረ ኃይል ይቋቋማል ብሎ ነበር።
ጠቅላይ ሚንስትር ኔታኒያሁ ሁከቱን በተመለከት ውይይት ለማድረግ በጠሩት ልዩ የሚንስትሮች ስብሰባ ላይ በሁከቱ “ተሳታፊ የነበሩትን ወደ አገራቸው መመለስን ጨምሮ በአመጸኞቹ ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ እንፈልጋለን” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ “ሕገ-ወጥ ሰርጎ ገብ የሆኑ ሁሉንም ስደተኞች” ከእስራኤል ማስወጣት ስለሚቻልበት ሁኔታ ሚንስትሮቹ ሕጋዊ አማራጮችን እንዲያቀርቡላቸው አሳስበዋል።
በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት አንድ ስደተኛ ወደ ትውልድ አገሩ ቢመለስ ሕይወቱ ወይም ነጻነቱን የሚያጣ ከሆነ እስራኤል በኃይል ወደ ትውልድ አገሩ መመለስ አትችልም።
ኔታኒያሁ የኤርትራ መንግሥት ደጋፊ የሆኑትን ወደ ትውልድ አገራቸው መመለስ በአስተዳደራቸው ላይ ሕጋዊ ተጠያቂነት ሊያስከትል እንደማይችል ያምናሉ ይላል የኤፒ ዘገባ።
በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ ኤርትራውያን እና ሱዳናውያን የሆኑ ከ25ሺህ የማያንሱ አፍሪካውያን ስደተኞች በእስራኤል ይኖራሉ።
እስራኤል ከእነዚህ መካከል ለጥቂቱ ብቻ የስደተኛነት እውቅና የሰጠች ሲሆን የተቀሩት ግን የኢኮኖሚ ጥገኛ ናቸው በማለት እነሱን ተቀብሎ የማኖር ሕጋዊ ግዴታ እንደሌላት ታምናለች።
በሮቿን ለስደተኞች ክፍት አታደርግም ተብላ የምትወቀሰው እስራኤል ከዚህ ቀደም ስደተኞችን ከእስራኤል ለማስወጣት የተለያዩ ስልቶችን ስትጠቀም ቆይታለች።
አንዳንድ ሕገ-ወጥ ስደተኞችን እርቀው ወደሚገኙ እስር ቤቶች የምትልክ ሲሆን ሌሎችን ደግሞ በጥቅማ ጥቅም በመደለል አፍሪካ ውስጥ ወዳለ ሦስተኛ አገር እንዲዘዋወሩ ስታደርግ ቆይታለች።
የስደተኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ግን የእስራኤል መንግሥት ስደተኞች አገሪቱን ጥለው እንዲወጡ አስጨናቂ እርምጃዎችን ይወስዳል ሲሉ ይተቻሉ።
የመብት ተቆርቋሪዎቹ በስደተኛ አይሁዶች የተመሠረተችው አገር ጥገኝነትን የሚጠይቁ ስደተኞች የምትቀበል አገር መሆን አለባት ይላሉ።
ትናንት የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚ ናቸው የተባሉ ከመንግሥት ደጋፊዎች ጋር ተጋጭተው የእስራኤል ፖሊስ አባላትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በንብረት ላይም ውድመት ደርሷል።
ከሁከቱ በኋላ 30 የፖሊስ አባላትን ጨምሮ 114 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው የሕክምና አገልግሎት እንደተሰጣቸው ከአገሪቱ ጤና ተቋም የወጣ መረጃ አመላክቷል።
ከእነዚህ መካከል 8 በጸና የተጎዱ ሲሆኑ 13 ደግሞ ለሕይወት አስጊ ባይሆንም ቀላል የማይባል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የኤርትራ የባሕል ፌስቲቫል ዝግጅትን ምክንያት በማድረግ በኤርትራውያን መካከል በአውሮፓ እና አሜሪካ ከተሞች ግጭት ሲፈጠረ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በዚህ ዓመት ብቻ በጀርመን ጊሰን ከተማ፣ በስዊድን፣ በኖርዌይ እና በካናዳ ቶሮንቶ ብዙዎችን ለጉዳት የዳረገ ግጭት ተከስቷል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንደሚያሳዩት በቀለም የተለያየ ካናቴራ የለበሱ ኤርትራውያን በሁለት ጎራ ተከፍለው በዱላ ሲደባደቡ እና በድንጋይ ሲፈነካከቱ ታይተዋል።
ፖሊስ ጥይት እየተኮሰ ከላይ ደግሞ በሄሊኮፍተር ቅኝት ሲያደርግ የነበረ ሲሆን የቴል አቪቭ ከተማ ነዋሪዎች ክስተቱ መኖሪያ አካባቢያችንን 'የጦር ቀጠና' አስመስሎት ነበር ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።