የእስራኤልን የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ግንባታ ለዓለም ያጋለጠው ሞርዴካይ ማን ነው?

እስራኤል ከአስር ቀናት በፊት የከፈተችውን ያልተጠበቀ ጥቃት "የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር አከርካሪውን የመታ" በሚል ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የገለጹት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህም አገራቸው የከፈተችው ጥቃት ዒላማ ያደረገው የኢራን ኒውክሌር ይዞታዎችን እንደሆነ ለማሳየት ሞክረዋል።

ኢራን የኒውክሌር ማበልጸጊያ ፕሮግራሟ ለሰላማዊ አገልግሎት ነው ብትልም እስራኤል ግን በድብቅ የጦር መሳሪያ እያመረተች ነው በማለት ትወቅሳታለች።

የኢራን የኒውክሌር ማበልጸጊያ ጥያቄ በሆነበት በአሁኑ ወቅት እስራኤልን የተመለከተ ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም።

እስራኤል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ አላት የሚባለውን አታረጋግጥም ወይም አትክድም።

ሆኖም ዓለም እስራኤል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳላት በሰፊው ያምናል።

ለዚህም ምክንያቱ አንድ ሰው ነው።

ግለሰቡ ከአራት አስርታት በፊት እስራኤል በድብቅ ስታከናውነው የነበውን የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ግንባታ ለዓለም አጋልጧል።

ግለሰቡ ይህንን ሲያደርግ ያለ መስዋዕትነት አይደለም። ለሁለት አስርታት በእስር ማቅቋል።

ወቅቱ መስከረም 25/1979 ዓ.ም. የብሪታኒያው 'ዘ ሰንደይ ታይምስ ጋዜጣ "የእስራኤል የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ምሥጢር ሲጋለጥ" በሚል ርዕስ በርካቶችን ያስደመመ አንድ ዘገባ አተመ።

የዚህ ዘገባ ምንጭ እስራኤላዊው የኒውክሌር ቴክኒሻን ሞርዴካይ ቫኑኑ ነው።

ሞርዴካይ በርካቶች ይጠራጠሩ የነበረውን የእስራኤልን የኒውክሌር አቅም ከማረጋገጥ በተጨማሪም የአገሪቱ የኒውክሌር የጦር መሳሪያ መርሃ ግብር ከታሰበው በላይ ግዙፍ እና የላቀ መሆኑን አሳየ።

ቴክኒሻኑ ከእየሩሳሌም 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በኔጌቭ በረሃ ላይ በተቋቋመው፤ በከፍተኛ ደረጃ ምሥጢራዊ በሆነው የዲሞና የኒውክሌር የምርምር ማዕከል ውስጥ ሠርቷል።

ጋዜጣው እስራኤል በዓለም ላይ ስድስተኛዋ የኒውክሌር ኃይል ባለቤት ሆናለች አለ።

እንዲሁም እስከ 200 የሚደርሱ የአውቶሚክ የጦር ማስተኮሻ እንዳላትም ዘገበ።

"ውጥረት እና በከፍተኛ ድካም ውስጥ ነበርን። አብዛኞቹ እንዲህ ዓይነት ትልቅ ዘገባ ሠርተው አያውቁም" ሲል የጋዜጣው የምርመራ ዘጋቢ ፒተር ሁናም የነበረውን ሁኔታ ለቢቢሲ ገልጿል።

ዘ ሰንደይ ታይምስ ዘገባውን መስከረም 25/1979 ዓ.ም. ባተመበት በዚያችው ዕለት እስራኤላዊው የመረጃው ምንጭ ደብዛው ጠፋ።

እስራኤል በአገር ክህደት የከሰሰችው ሞርዴካይ

የሰንደይ ታይምስ ጋዜጠኛ ፒተር የኒውክሌር ቴክኒሻኑን ያገኘው ከዚያ ቀደም ብሎ በነሐሴ ወር ላይ ነበር። የተገናኙትም በአውስትራሊያዋ ከተማ ሲድኒ ነው።

ፒተር ሞርዴካይን ሲያየው አካላዊ ገጽታውም ሆነ ሁኔታው እንዳስገረመው አይደብቅም።

"ሞርዴካይን በአካል ሳየው አጭር፣ በጣም ትንሽ፣ ራሰ በራ፣ በራስ መተመማን የሌለው እና አልባሌ ልብስ የለበሰ ግለሰብ ነበር። በፍጹም የኒውክሌር ሳይንቲስትነት የተላበሰ ገጽታ አልነበረውም" ይላል ጋዜጠኛው።

ቴክኒሻኑ በዲሞና ስላየው ነገር ለዓለም ይፋ ለማድረግ በተነሳበት ውሳኔው ጸንቶም ዝርዝር መረጃዎችን አጋራ።

እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የምታደርሰውን በደል እንዲሁም የኒውክሌር የጦር መሳሪያ መገንባቷ ተስፋ ያስቆረጠው ሞርዴካይ ሥራውን ለመልቀቅ የወሰነው ከዚያ ቀደም ብሎ በነበረው ዓመት ነው።

ቀጣዩ ዕቅዱም ሻንጣውን ይዞ ወደ እስያን መዞር ነበር።

ሆኖም ሥራውን ከመልቀቁ በፊት ወደ ኒውክሌር ጣቢያው አምርቶ በሁለት ጥቅል ፊልሞች ፎቶዎችን አነሳ።

ይህም ብቻ አይደለም ለኒውክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታ የሚውሉ ራዲዮ አክቲቭ ቁሶችን ለማውጣት የሚያገለግል መሳሪያ እንዲሁም የኒውክሌር ቦምብ የላብራቶሪ ሞዴልን ወሰደ።

"ካሜራ እንዴት ደብቆ እንዳስገባ፣ ተመልሶ መጥቶ ፊልሞቹን በካልሲው ውስጥ እንደሸጎጣቸው እንዲሁም ፎቶዎቹን በድብቅ በሌሊት እንዲሁም በጥዋት እንዳነሳ አስገራሚ ታሪክ ነገረኝ" ይላል ጋዜጠኛው።

የሰንደይ ታይምስ አዘጋጆች የሞርዴካይን ታሪክ ለማጣራት ወደ ለንደን እንዲመጣ ጠየቁት።

ፍራቻ ቢያድርበትም ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለመብረር ተስማማ።

ጋዜጣውም ከለንደን ውጪ በሚገኝ ደበቅ ባለ ሆቴል አሳረፈው።

ሆኖም እረፍት አልባነት የተሰማው ቴክኒሻኑ ለንደን መጣ እና በአንድ ሆቴል አረፈ።

በዚህም ወቅት ነው ሁኔታዎች ግልብጥብጣቸው የወጣው።

"በጎዳናዎች ላይ ሲዘዋወር አንዲት ሴትን አገኘ። የተወሰነ ጊዜ አይቷት ስለነበር አብሯት ሲኒማ ሄደ። እናም ይህቺን ሴት ማንነቷን ታውቃለህ? እውነተኛ ናት ሲል መጠየቁን" ፒተር ያወሳል።

የሞርዴካይ የለንደን ቆይታ በከፍተኛ ሁኔታ ያሳስበው የነበረው ጋዜጠኛው በየጊዜው እየደወለ ይጠይቀው ነበር።

ፒተር ከሞርዴካይ ጋር የነበረውን የመጨረሻ ንግግር ያስታውሳል።

"'ወደ ሰሜን እንግሊዝ ለጥቂት ቀናት እሄዳለሁ። ምንም አልሆንም' አለኝ። እኔም ምንም ነገር ብታደርግ ደኅንነትህን እንዳውቅ በቀን ሁለት ጊዜ ደውልልኝ አልኩት" ይላል።

ሆኖም ከአንድ ወር በኋላ የእስራኤል መንግሥት ሞርዴካይ እንደታሰረ አስታወቀ።

ለንደን ላይ በተዋወቃት ሴት ነበር ወጥመድ ውስጥ የገባው። ራሱንም አስተው በጀልባ ነበር ወደ እስራኤል በድብቅ ያጓጓዙት።

ሞርዴካይ ወደ እስር ቤት እየሄደ ሳለ እንዴት ከለንደን ተጠልፎ እንደተወሰደ አንዳንድ ዝርዝሮችን በእጁ መዳፍ ላይ አሰፈረ።

ሲጠብቁት ለነበሩት ጋዜጠኞችም በመኪናው መስኮት በኩል መዳፉን ከፍ አድርጎ አሳየ።

ሞርዴካይ ሊያዝ የበቃው ለንደን ላይ ቱሪስት መስላ በቀረበችው ግለሰብ ነበር። በአሜሪካ የተወለደችው ቼሪል ቤንቶቭ ቱሪስት ሳትሆን የሞሳድ ወኪል ነበረች።

ግለሰቧ ሞርዴካይን አታልላ አብሯት ወደ ሮም እንዲመጣ መስከረም 20/1979 ጋበዘችው። ሮም ከሄደ በኋላ ታፍኖ እንዲደነዝዝ ተደረገ። ከዚያም በኋላ ነው ወደ እስራኤል የተወሰደው።

ሞርዴካይ መጋቢት 1981 በአገር ክህደት እና በስለላ ወንጀል 18 ዓመታት ተፈረደበት።

ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ጊዜም ብቻውን እንዲታሰር ተደርጓል።

"እየተከናወነ ያለውን ነገር ለዓለም ማሳወቅ ነው የፈለግኩት። ይህ የአገር ክህደት አይደለም። የእስራኤል ፖሊሲ ባይፈቅደውም ዓለምን አሳውቄያለሁ" ሲል ሞርዴካይ ከእስር ቤት ሆኖ በተቀረጸ ቃለ ምልልስ ተናግሯል።

ሞርዴካይ ሚያዝያ 13/1996 ዓ.ም. ከእስር ቢፈታም ከእስራኤል እንዲወጣ አልተፈቀደለትም።

ነገር ግን የኒውክሌር ሳይንቲስቱ ሞርዴካይ ከእስር የተለቀቀበትን የይቅርታ ሁኔታውን በመተላለፍ በተደጋጋሚ ለእስር ተደርጓል።

በ2001 ከመታሰሩ በፊትም "ባሰራችሁኝ 18 ዓመታት ውስጥ ምንም አላገኛችሁብኝም። በሦስት ወር ምንም አታገኙም። እስራኤል ሆይ እፈሪ" በማለት ሲጮህ ተሰምቷል።

የእስራኤል የኒውክሌር ግንባታ ምሥጢራዊ ስምምነት

የእስራኤልን የኒውክሌር አቅም በተመለከተ ቴክኒሻኑ እስኪያጋልጥ ድረስ የቅርብ አጋሮቿ እንኳን ብዙም የሚያውቁት ጉዳይ አልነበረም።

እስራኤል የኒውክሌር መርሃ ግብሯን የጀመረችው በአውሮፓውያኑ 1948 እንደ አገር በተመሠረተች ማግስት ወዲያውኑ መሆኑ ይታሰባል።

በጠላቶች እንደተከበቡ ያመኑት የእስራኤል የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ቤን ጉሪዮን የኒውክሌር መከላከያ መገንባትን ከፍተኛ ቦታ ሰጡት።

ነገር ግን ግጭት በማያጣው ቀጣና የኒውክሌር መሳሪያዎችን በማምረት ወዳጆቻቸውን ማበሳጨት አልፈለጉም።

እስራኤል የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ለማምረት የሚያስችላትን የዲሞና የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያን ለመገንባት ከፈረንሳይ ጋር በአውሮፓውያኑ 1960 ምሥጢራዊ ስምምነት ላይ ደረሰች።

ለዓመታት ያህል ይህ ጣቢያ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ እንደሆነ እስራኤል ስትናገር ቆይታለች።

የአሜሪካ ባለሙያዎች ስፍራውን በ1960ዎቹ በተደጋጋሚ ጎብኝተው ነበር።

ሆኖም ጣቢያው የነበረበትን ከመሬት በታች ያለውን ግንባታ አልተረዱት።

እስራኤል በአሁኑ ወቅት ወደ 90 የሚጠጉ የኒውክሌር አረሮች እንዳሏት ይገመታል ሲል የጦር መሳሪያ ቁጥጥርን የሚከተታተለው 'ሴንተር ፎር አርምስ ኮንትሮል ኤንድ ነን ፕሮሊፈሬሸን' አስታውቋል።

ሆኖም እስራኤል በኒውክሌር አቅሟ ዙሪያ ግልጽ ያለ መረጃ አትሰጥም።

ከዚህ ቀደም የአገሪቱ መሪዎች "እስራኤል የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን በመካከለኛው ምሥራቅ ለማስተዋወቅ የመጀመሪያዋ አገር አትሆንም" ሲሉ በተደጋጋሚ ሲደመጡ ይሰማል።

ከአውሮፓውያኑ 1970 ጀምሮ 191 አገራት የኒውክሌር የጦር መሳሪያዎች ሥርጭት እና መስፋፋትን ለመከላከል ያለመውን 'ትሪቲ ኦን ዘ ነን ፕሮሊፈሬሽን ኦፍ ኒውክሌር ዌፐንስ' የተሰኘውን ስምምነት ፈርመዋል።

አምስት አገራት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ቻይና የኒውክሌር የጦር መሳሪያ እንዲኖራቸው ተፈቅዶላቸዋል።

ለዚህም ምክንያቱ ስምምነቱ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ገንብተው ሙከራ አድርገው በማጠናቀቃቸው ነው።

እስራኤል የስምምነቱ ፈራሚ አባል አገር አይደለችም።

የእስራኤልን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለዓለም ያጋለጠው ሞርዴካይ በእስራኤል የአገር ክህደት እንደፈጸመ ተደርጎ ነው የሚቆጠረው።

ነገር ግን ደጋፊዎቹ በበኩላቸው በ1996 ዓ.ም. ከእስር ሲፈታ "የሰላም ጀግና" በሚል አክብረውታል።

ከእስር ከተለቀቀ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ "ምንም የሚጸጽተኝ ጉዳይ የለም" ብሏል።

"እኔ በምሥጢር እየተከናወነ የነበረውን ነገር ለዓለም ነው ያሳወቅኩት። እስራኤልን እናጥፋ፣ ዲሞና ይውደም አላልኩም። ይሄን እየሠሩ ነው እና እዩና ፍረዱ ነው ያልኩት" ብሏል።