በጀርመን ባንክ ላይ በአራት ሰዓት ውስጥ የ100 ሚሊዮን ዩሮ ዝርፊያ እንዴት ተፈጸመበት?

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

በጀርመን ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የባንክ ዘረፋ ተብሎ ተጠርቷል።

በገና በዓል በሳምንቱ ጀርመን ቀዝቀዝ ብላ ነበር። በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ጌልስኒክርቸን ከተማ ውስጥ ዘራፊዎች ተሰማሩ።

ሀይ ስትሪት የተባለ ባንክ ግድግዳውን ሰርስረው ገቡ። ሌቦቹ ከ3,000 በላይ ጥብቅ የንብረት ሳጥኖችን መዝብረዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዩሮ አግኝተዋል።

ዘረፋው አንድ ወር አልፎታል። ፖሊስ ግን ተጠርጣሪዎችን መያዝ አልቻለም።

የባንኩ ደንበኞች እንደተናገሩት ዕድሜ ዘመናቸውን ያጠራቀሙትን ሃብት እና ንብረት ተዘርፈዋል፤ በቤተሰቦች ውስጥ ተጠብቆ የቆየ ውድ ጌጣጌጥ አጥተዋል።

ብዙዎች ዘረፋው አስቆጥቷቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ ግራ ተጋብተዋል። አሁንም ድንጋጤው አልለቀቃቸውም። በባንኩ ላይ ያላቸው እምነት ተሸርሽሯል።

የኖርዝ ሪን ዌስትፊሊያ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ኸርበርት ሩል ስለ ዝርፊያው የሚነሱ ጥያቄዎችን ይዘረዝራሉ።

እንዴት ማንም ሰው ስርቆቱን አላስተዋለም? የባንኩ ሠራተኞች በምዝበራው እጃቸው አለበት? የባንኩ ግድግዳ ሲቦረቦር ማንም ሳይሰማ የቀረው እንዴት ነው?

ሌቦቹ ጥብቅ ቁሳቁስ የሚገኝባቸው ሳጥኖች የት እንዳሉ በትክክል ማወቅ የቻሉት በምን መንገድ ነው? የባንኩ የደኅንነት ጥበቃ ደካማ ነው?

የጌልስኒክርቸን ፖሊስ የዐይን እማኞች ካሉ መረጃ እንዲያቀብሉ ጥሪ አድርጓል።

መርማሪዎች እንደሚሉት፤ ሌቦቹ የባንኩን ግድግዳ ቦርቡረው የገቡት ከባንኩ አጠገብ በሚገኝ የመኪና ማቆሚያ በኩል ሊሆን ይችላል።

በተደራራቢ ሕንጻዎች ላይ ከሚገኘው የመኪና ማቆሚያ በኩል የባንኩን ግድግዳ መሰርሰር እንደቻሉ መላ ምት ያስቀመጡት መርማሪዎች፤ ሌቦቹ በመኪና ማቆሚያው በኩል የሚገኝ በርን አልፈው እንደገቡም ይገምታሉ።

ይህንን በር ከውጭ በኩል መክፈት አይቻልም። ሌቦቹ ግን በሩ በተለመደው ሁኔታ በአግባቡ እንዳይዘጋ አድርገው ወደ ውስጥ ዘልቀዋል።

በሩን ካለፉ በኋላ በመኪና ማቆሚያው እና በባንኩ መካከል ያለውን ግድግዳ መቦርቦራቸው ተገልጿል።

ዘራፊዎቹ በሩን ካለፉ በኋላ በርካታ የደኅንነት መጠበቂያ መሣሪያዎችን ጥሰው ማለፍ ነበረባቸው።

ባንኩ ውስጥ ከገቡ በኋላ በቀጥታ ያመሩት ጥብቅ ሳጥኖች ወደሚገኙበት የባንኩ ክፍል ነው። ይህ ጥብቅ ክፍል በባንኩ ከመሬት ሥር የተገነባ ነው።

የባንኩን ግድግዳ 40 ሴንቲሜትር ሰርስረው ወደ ጥብቅ ክፍሉ ማምራት ችለዋል። በዚህ ክፍል ውስጥ ውድ የሆኑ ሃብት ንብረቶች ይከማቻሉ።

ዝርፊያው የተፈጸመው በታኅሣሥ ወር አጋማሽ ላይ በሚገኙ ቀናት ውስጥ እንደሚሆን ይታመናል።

ታኅሣሥ 27 የከተማዋ የእሳት አደጋ መከላከያ ተቋም እንዲሁም በግል የደኅንነት ጥበቃ የሚሰጥ ድርጅት ጥቆማ ደርሷቸዋል።

የደረሳቸው ጥቆማ ባንኩ ውስጥ እሳት እንደተነሳ የሚጠቁም ነው። ይህም በሌቦቹ እንቅስቃሴ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መርማሪዎች ገልጸዋል።

የአካባቢው ባለሥልጣናት እንዳሉት ዘራፊዎቹ ወደ ጥብቅ ክፍሉ ሳይገቡ በፊት ሊያዙ ቢችሉም ለጥቂት አምልጠዋል።

ለእሳት አደጋ መከላከያው 6፡00 ላይ ጥቆማ ከደረሰ በኋላ 6፡15 ላይ ፖሊስ እና 20 የእሳት አደጋ ሠራተኞች ወደ ባንኩ ደርሰዋል።

ፖሊስ እንዳለው ጉዳት መድረሱን የሚጠቁም አንዳችም ምልክት አልተገኘም።

የኖርዝ ሪን ዌስትፊሊያ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ኸርበርት ሩል እንደገለጹት፤ የእሳት አደጋ ደርሷል የሚለው ጥቆማ የደረሳቸው ከጥብቅ ክፍሉ ውስጥ ነበር።

ጥብቅ ክፍሉ ተቆልፎ ስለነበር የእሳት አደጋ ሠራተኞች መግባት አልቻሉም።

"ጭስ ወይም ሽታ አልነበረም። ጉዳት ደርሶም አላየንም። ስለዚህም የደረሰን ጥሪ የተሳሳተ ነው ብለን ደመደምን" ሲሉ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ፖሊሶች ጥሪው በደረሳቸው ሰዓት ላይ ባንኩን ያለ ፖሊስ ትዕዛዝ የመፈተሽ መብት እንዳልነበራቸው ለከተማዋ ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል።

ባንኩን መፈተሽ የሚችሉት የእሳት አደጋ ሠራተኞች ብቻ ነበሩ።

ዘራፊዎቹ ጥብቅ ክፍል ውስጥ ከገቡ በኋላ 3,250 ሳጥኖች ከፍተው ወርቅ፣ ገንዘብ እና ጌጣጌጦች ሰርቀዋል።

የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ የመጀመሪያው ሳጥን የተከፈተው ታኅሣሥ 17/2018 ዓ.ም. ቀን ረፋድ 4 ሰዓት ከ45 ላይ እንደሆነ የባንኩ የኮምፒውተር መረጃ ያሳያል።

የመጨረሻው ሳጥን የተከፈተው በዚያው ቀን ከሰዓት በኋላ 8 ሰዓት ከ44 ላይ ነው።

ስለዚህም በአራት ሰዓታት ውስጥ ሳጥኖቹን በአጠቃላይ ከፍተውት ይሁን አልያም የባንኩ ኮምፒውተር መረጃ መመዝገብ አቁሞ የሚለውን በትክክል ለማወቅ አልተቻለም።

የዐይን እማኞች ኋላ ላይ ለፖሊስ በሰጡት መረጃ መሠረት፤ ታኅሣሥ 18 ላይ በመኪና ማቆሚያው አካባቢ ብዙ ወንዶች ሲዘዋወሩ ተመልክተዋል።

በአጠቃላይ ምን ያህል ገንዘብ እንደተዘረፈ እንደማይታወቅ የአካባቢው ባለሥልጣናት ቢናገሩም፤ የጀርመን መገናኛ ብዙኃን እንዳሉት ወደ 100 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ሳይመዘበር አልቀረም።

በመኪና ማቆሚያው ውስጥ በሚገኙ የደኅንነት ካሜራዎች ላይ የተገኙ ፎቶግራፎች እና ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ይፋ ተደርገዋል።

ምሥሎቹ ላይ የሚታዩት ወንዶች የፊት መሸፈኛ ጭምብል አጥልቀዋል። ጥቁር አውዲ አርኤስ 6 እና ነጭ መርሴዲስ ሲታን ይታያሉ። ሁለቱም መኪኖች በሐሰተኛ ታርጋ ሲንቀሳቀሱ ነበር።

ታኅሣሥ 19 በድጋሚ የእሳት አደጋ ጥቆማ ሲደርስ ነው ዝርፊያ መፈጸሙ የተደረሰበት።

የእሳት አደጋ ሠራተኞች ወደ ባንኩ ሲደርሱ "ምስቅልቅሉ ወጥቶ" እንደነበር ተገልጿል።

የአገር ውስጥ ሚኒስትሩም ከ500 ሺህ በላይ ቁሳቁሶች እዚህም እዚያም ወዳድቀው እንደነበር ተናግረዋል።

ሌቦቹ ጌጣጌጦች እና ገንዘብ ከሰረቁ በኋላ ጥለዋቸው የሄዱት ጥብቅ ሳጥኖች ተገኝተዋል። ዘራፊዎቹ ውሃ እና ኬሚካል የደፉባቸው ቁሳቁሶች እንደተጎዱ የፖሊስ መረጃ ያሳያል።

የትኛው ንብረት የማን እንደሆነ ለመለየት እየተሞከረ ይገኛል። ዝርፊያ መፈጸሙ ይፋ ከሆነ በኋላ ከ200 በላይ የባንኩ ደንበኞች በሥፍራው ተገኝተዋል።

የ63 ዓመቱ ጆቹም አልፍሬድ ዋግነር አሥር ሺህ ዩሮ የሚያወጣ ወርቅ መሰረቃቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም የአባታቸው እና አያታቸው ጌጣጌጦች ተዘርፈዋል።

ጆቹም መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደጋጋሚ ሌቦች ሲገቡ ወደ ባንክ ሄደው ጥብቅ ሳጥን ተከራይተዋል።

ሃብት ንብረታቸው መዘረፉን ሲሰሙ "በንዴት እንዳለቀሱ" ተናግረዋል።

ባንኩ እንዳለው ጥብቅ ሳጥኖች እያንዳንዳቸው 10,300 ዩሮ የመድኅን ዋስትና አላቸው።

ባንኩን ከከሰሱ ደንበኞች መካከል ጆቹም ይገኙበታል። ጠበቃቸው ዳንኤል ኩህልማን እንዳሉት ባንኩ ተገቢውን ጥበቃ አላደረገም።

ሌላ የባንኩ ደንበኛ ጡረታ ለመውጣት በሚል የቆጠቡትን 400 ሺህ ዩሮ ተዘርፈዋል።

ባንኩ የወንጀል ዒላማ ቢደረግም እንኳ "በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንደሚጠበቅ" ገልጿል።

ከባንኩ ደንበኞች የተወሰኑት በጥብቅ ሳጥን ውስጥ ያስቀመጡት ንብረት ይፋዊ ዝርዝር አላቸው።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ የባንኩ ደንበኞች ላይ የደረሰው ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸው "ልናግዛቸው ይገባል" ብለዋል።

"ብዙዎቹ ያጡት ንብረታቸውን ብቻ አይደለም። በባንኩ ላይ ያላቸው እምነት ተሸርሽሯል" ሲሉም አክለዋል።

የፖሊስ ኃላፊው ቲም ፍሮምየር በበኩላቸው "በኖርዝ ሪን ዌስትፊሊያ ውስጥ ከተፈጸሙ ዝርፊያዎች ትልቁ ነው" ብለዋል።

"ይሄ ጉዳይ እንዴት ከባድ እንደሆነ የፖሊስ ክፍላችን እና ሠራተኞቹ ይገነዘባሉ። የደረሰው የገንዘብ ጉዳት ግዙፍ ነው። ጥርጣሬ እና ቁጣም ተፈጥሯል" በማለትም ተናግረዋል።

ዝርፊያው መፈጸሙ ይፋ ከተደረገ በኋላ የጀርመን ቀኝ ዘመም ፓርቲ ኤኤፍዲ በባንኩ በራፍ ላይ ተቃውሞ አካሂዷል። ብዙዎች ተቃውሞውን ሁከት ከማስነሳት ጋር አያይዘውታል።

'ደር ስፒገል' የተባለው የጀርመን ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ ስርቆቱ የፖለቲካ አጀንዳ መሆኑን ጠቁሟል።

"ተቋማት ደኅንነት ማስጠበቅ አልቻሉም እንዲሁም ማንም አካል ተጠያቂ አልተደረገም" የሚል ሐተታም አስነብቧል።