የኤርትራው ፕሬዝዳንት ወደ ሳዑዲ ሲያቀኑ የሚያሳየው ምሥል 'ፎቶሾፕ' ተደርጓል?

የፎቶው ባለመብት, @hawelti
ለአራት ቀናት የሥራ ጉብኝት በሪያድ የሚገኙት የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሳዑዲ አረቢያው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋር በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተገልጿል።
የኤርትራ የልዑካን ቡድን ወደ ሪያድ ያቀናው ረቡዕ ታኅሣሥ 1/2018 ዓ. ም. ነው። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ወደ ሳዑዲ ያቀኑት በንጉሥ ሰልማን ቢን አብዱላዚዝ አል ሳዑድ ግብዣ እንደሆነም ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ሳዑዲ እንደተጓዙ የሚጠቁመው የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው ያጋሩት ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ ሆኗል። ስለ ምሥሉ ትክክለኛነት ጥያቄዎችም ተነስተዋል።
ከሁለት ቀናት በፊት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ያጋሩት የመጀመሪያ ምሥል ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኦስማን ሳላሕ በአሥመራ አውሮፕላን ማረፊያ ሳሉ ያሳያል። በምሥሉ ላይ ፕሬዝዳንቱ ከፊት ለፊት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደግሞ በቅርብ ርቀት ከኋላቸው ይታያሉ።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኦስማን በአሥመራ የአውሮፕላን ማረፊያ በተነጠፈ ቀይ ምንጣፍ ላይ ሲጓዙ ይታያል። የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ባጋሩት የኤክስ ልጥፍ ላይ የተያያዘው ሁለተኛ ምሥል ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አውሮፕላን ውስጥ ሲገቡ ያሳያል።
የአውሮፕላኑ መለያ 'ኪንግደም ኦፍ ሳዑዲ አረቢያ' ይላል። ምሥሎቹ በአንድ ዕይታ እምብዛም ጥያቄ ላያጭሩ ይችላሉ።
በትኩረት ሲታዩ ግን የተለያዩ የምሥሎቹ ክፍሎች አጠራጣሪ መሆናቸው ይስተዋላል። በተለይም አጠራጣሪ ሆኖ የሚታየው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኦስማን ምሥል ነው።
የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ ቢቢሲ ቬሪፋይ ምሥሉ ላይ ምርመራ አድርጓል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ምሥል ላይ ከወገባቸው በታች ያለው ጥላ ተፈጥሯዊ እንዳልሆነ ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል።

ምሥሉ ላይ አንዳች አርትኦት መደረጉን በዋነኛነት የሚጠቁመው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ምሥል ላይ የሚታየው ጥላ አቅጣጫው እና ቀዩ ምንጣፍ ላይ የሚታይበት ቦታ ከሰውነታቸው ተፈጥሯዊ አቋም ጋር የተመጣጠነ አለመሆኑ ነው።
የሰዎች ወይም የቁሳቁስ ምሥል ላይ ብርሃን ሲያርፍ የሚፈጠረው ጥላ ከሰዎቹ ወይም ከቁሳቁሱ አቀማመጥ ጋር የሚጣጣም መሆን አለበት።
ቢቢሲ ቬሪፋይ እንዳረጋገጠው፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና በፕሬዝዳንቱ መካከል ጥላ አይታይም።
በምሥሉ ላይ የሚታየው ጥላ መነሻው ከፕሬዝዳንቱ አንጻር ገዘፍ ብሎ ከሚታይ ሰው የተነሳ እንደሆነ ማወቅ ይቻላል። በፕሬዝዳንቱ እግሮች መካከል እና በምንጣፉ ላይ የሚታየው ጥላም ተፈጥሯዊ አይደለም።
የፕሬዝዳንቱ ቀኝ ትከሻ ከሚኒስትሩ ግራ ክንድ ጋር የሚገናኝበት ቦታ ላይ ቀይ መስመር ይታያል።
የሚኒስትሩ ምሥል ከበስተቀኛቸው ካለው ግለሰብ ጥላ ጋርም ይጣረሳል። ከቀኝ ያለው ግለሰብ ጥላ ቀዩ ምንጣፍ ላይ አርፎ ወደ ሚኒስትሩ ሲቃረብ ተፈጥሯዊ ባልሆነ መንገድ ደብዝዟል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጫማም እንግዳ የሆነ ገጽታ ተላብሷል። የሚኒስትሩ ጫማ ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ ሌሎች በምሥሉ ላይ ካሉ ሰዎች ጫማ ጋር ሲነጻጸር ልዩነት አለው። የሚኒስትሩ ጫማ ደብዘዝ ያለ ሲሆን፤ እንደ ሌሎቹ ሹል ሆኖ አይታይም።

የፎቶው ባለመብት, @hawelti
ቢቢሲ ቬሪፋይ ባደረገው ማጣሪያ መሠረት ምሥሉ ላይ አርትኦት መደረጉን የሚጠቁመው ሌላ ማሳያ የሚኒስትሩ ትከሻ እና ጭንቅላት ነው። ምሥሉ የተቆረጠ ወይም ከሌላ ምሥል የተወሰደ መሆኑን ይጠቁማል። አልያም ከመካከላቸው የነበረ ሰው ምሥል ተቆርጦ ወጥቶ ሊሆን ይችላል።
የሚኒስትሩ ትከሻ ከፕሬዝዳንቱ ምሥል ጋር በሚገናኝበት ቦታ ያለው ቀለም ምሥሉን ለማመሳሰል ሙከራ መደረጉን ያሳያል።
ፕሬዝዳንቱ እና ሚኒስትሩ በሪያድ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ሲደረግላቸው እንዲሁም ከሳዑዲ መሪዎች ጋር ውይይት ሲያደርጉ የሚያሳዩ ምሥሎችን የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ በኤክስ ገጻቸው አጋርተዋል።
እነዚህ ምሥሎች የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ በሳዑዲው የሥራ ጉብኝት ላይ መገኘታቸውን የሚያረጋግጡ ሆነው ሳለ በአሥመራ አውሮፕላን ማረፊያ ሳሉ የሚያሳየው ምሥል ላይ ቅንብር ወይም አርትኦት ማድረግ ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
"ምናልባትም ለፕሮቶኮል ሲባል ወይም ምሥሉን ለማሳመር" ተብሎ የተደረገ ሊሆን እንደሚችል የቢቢሲ ቬሪፋይ ባልደረባ ግምቱን ያስቀምጣል።
ሌላኛው ግምት፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ምሥሉ ሲነሳ ራቅ ብለው ከሆነ ለማቅረብ የተደረ ሙከራ ሊሆን ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, @hawelti
የኤርትራው ፕሬዝዳንት በጉብኝታቸው ወቅት ሳዑዲ አረቢያ እንደ ናይል ተፋሰስ እና ቀይ ባሕር ባሉ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ያላትን ተሳትፎ እንድታሳድግ እንዲሁም ለቀጣናው ሰላም "ከፍተኛ አስተዋጽኦ" እንድታደርግ ጠይቀዋል።
ሳዑዲ አረቢያም በእነዚህ "በወሳኝ ቀጣናዊ ጉዳዮች" ላይ ምክክር ለማድረግ ወደ ኤርትራ ልዑክ እንደምትልክ መግለጿ ተዘግቧል።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ያጋሩት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ኢሳያስ በአል-ያማማህ ቤተ መንግሥት ከሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋር "ሰፊ ንግግር" አድርገዋል።
የሁለቱ መሪዎች ንግግር "በሁለትዮሽ ግንኙነቶች እንዲሁም ለሁለቱ አገራት ወሳኝ ጥቅም ባላቸው ሌሎች ጉዳዮች" ላይ ያተኮረ እንደነበር አመልክተዋል።
"ሞቅ ያለ" እንደነበር የተገለጸው የሁለቱ መሪዎችን ውይይት፤ አገራቱ ያላቸው "ታሪካዊ እና ወንድማማቻዊ ግንኙነት" የተነሳበት እንደነበረም ጠቅሰዋል።
ሁለቱ አገራት "ኢኮኖሚያዊ ትብብሮች ላይ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማስፋት ያላቸው ተስፋ እና ዕድል" ላይ ያተኮረም እንደነበርም ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቀጣናዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያደረጉት ውይይት "ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ ምልከታ መለዋወጥ ላይ" ያጠነጠነ እንደነበረ የማነ በኤክስ ልጥፋቸው አስረድተዋል።
ቀጣናዊ ጉዳዮች ተብለው የተጠቀሱት "የአባይ ተፋሰስ፣ የአፍሪካ ቀንድ፣ ቀይ ባሕር እና የአረቢያን ባሕረ ሰላጤ" ናቸው።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከጥቅምት 21 አንስቶ አስከ ኅዳር 30 ድረስ ባለው የሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ሦስት አገራት ተጉዘዋል። ፕሬዝዳንቱ የቀይ ባሕር ዋነኛ ተጎራባች አገራት ወደሆኑት ግብፅ፣ ሱዳን እና ሳዑዲ አረቢያ ተጉዘው ረዘም ላሉ ቀናት ቆይተዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር እየተካሰሱ ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዙሪያቸው ካሉ አገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ የተደጋጋሚ ጉብኝታቸው መዳረሻ ከነበረችው ኢትዮጵያ ጋር ሆድና ጀርባ የሆኑት ኢሳያስ በተለይም ከቀይ ባሕር ጋር በተያያዘ ውጥረት መንገሡን ተከትሎ ፊታቸውን ወደ ሌሎች አገራት አዙረዋል።















