ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጥይት የተመቱት የስሎቫኪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሮበርት ፊኮ ሕይወታቸው አስጊ ሁኔታ ውስጥ አይደለም ተባለ
በጥይት የተመቱት የስሎቫኪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሮበርት ፊኮ ለሕይወታቸው የሚያሰጋ ሁኔታ አለመኖሩን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ቶማስ ታራባ፤ የፊኮ ቀዶ ሕክምና “በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን” እና “በመጨረሻም እንደሚተርፍ እገምታለሁ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፊኮ በሃንድሎቫ ከተማ በደረሰባቸው ጥቃት ከባድ ጉዳት ስላጋጠማቸው “በህይወት ለመቆየት እየታገሉ ነው” ሲሉ የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ቀደም ብለው ገልጸው ነበር።
አንድ ተጠርጣሪ ተኩስ በተከፈተበት ቦታ በቁጥጥር ስር ውሏል።
የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ማቱስ ሱታጅ ኢስቶካ ጥቃቱን ፖለቲካዊ የመግደል ሙከራ ሲሉ ገልጸውታል።
ጥቃቱን ተከትሎ ፊኮ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ተወስደው በቀዶ ሕክምና "በህይወት እንዲቆዩ ትግል መደረጉን” የመከላከያ ሚኒስትሩ ሮበርት ካሊናክ ረቡዕ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነበሩበት ሆስፒታል ደጃፍ ሆነው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
ከዚያን ወዲህ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሁኔታ በተመለከተ ምንም ዓይነት ይፋዊ መረጃ አልተሰጠም ነበር። በኋላም ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ፊኮ “በአሁኑ ሰዓት ለሕይወት አስጊ ሁኔታ ውስጥ አይደሉም” ሲሉ ለቢቢሲ ኒውስአወር ተናግረዋል።
ታራባ "እኔ እስከማውቀው ድረስ ቀዶ ጥገናው በጥሩ ሁኔታ ተከናውኗል። እንደሚተርፍም እገምታለሁ" ብለዋል።
ታራባ አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተተኮሰባቸው "ከቅርብ ርቀት ነው። አንደኛው ጥይት በሆዳቸው ውስጥ ሲገባ ሁለተኛው ጥይት ደግሞ መገጣጠሚያቸውን መቶታል" ብለዋል።
ፖሊስ እስካሁን የተጠርጣሪውን ማንነት አላሳወቀም። ያልተረጋገጡ የአገር ውስጥ ሚዲያ ዘገባዎች ግን ጥቃት አድራሹ የ71 ዓመት ጸሐፊ እና የፖለቲካ አክቲቪስት መሆናቸውን ዘግበዋል።
በስሎቫክ ሚዲያዎች ላይ በስፋት እየተሰራጩ ባሉ ቪዲዮዎችም ተጠርጣሪው ታይተዋል።
በቪዲዮው ላይ የሚታየው ግለሰብ ከመንግስት ፖሊሲ እና ከመንግስት ሚዲያ ጋር በአቋም እንደማይስማሙ ተናግሯል። ቢቢሲ በቪዲዮው ላይ ያለው ሰው በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪ ስለመሆኑም ሆነ ስለተቀረጸበት ሁኔታ ምንም ያወቀው ነገር የለም።
ጥቃቱ የተፈጸመው የስሎቫኪያን ብሮድካስት (አርቲቪኤስን) ለመዝጋት በቀረበው ሃሳብ ላይ የአገሪቱ ፓርላማ መወያየት በጀመረበት ቀን ነው።
በሺህ የሚቆጠሩ ስሎቫኮች ባለፉት ሳምንታት የአገሪቱ ፓርላማ የቀረበውን ማሻሻያ ተቃውመዋል። የጥቃቱ ዜና መውጣቱን ተከትሎ በተቃዋሚዎች ለረቡዕ ተጠርቶ የነበረው ሰልፍ ተሰርዟል።
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ታራባ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በስሎቫኪያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “የተሳሳቱ ታሪኮችን” ለጥቃቱ ተጠያቂ አድርገዋል።
ታራባ ከቢቢሲ ወርልድ ቱናይት ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ሌላ ቃለ ምልልስ ደግሞ “ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባለፈው ጊዜ ይህ ሊሆን ይችላል ብለው እንደሚሰጉ ደጋግመው ተናግረው ነበር” ብለዋል።
ፊኮ “መንግስት በውሸት ትርክቶች የተጠቃበት መንገድ ህዝቡን በማነሳሳት ወደ እንደዚህ ያለ ነገር ሊያመራ ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል ማለታቸውን ተናግረዋል።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት ፓርላማው ተሰብስቦ ነበር። እንደስሎቫኪያ ሚዲያ ዘገባ ከሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ ጥቃቱን አባብሰዋል በማለት አንድ የፊኮ ፓርቲ ባልደረባ መናገራቸወን ዘግበዋል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢስቶክ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ብዙዎቻችሁ ይህንን ጥላቻ የምትዘሩ ነበራችሁ” ሲሉ መገናኛ ብዙሃን ለ59 ዓመቱ ጠቅላይ ሚንስትር መጠቃት አስተዋጽኦ አድርገዋል ሲሉ ከሰዋል።
ኢስቶክ አክለውም “ይህ የግድያ [ሙከራ] ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው” ብለው እንደሚያምኑ ተናግሯል።
ተሰናባቹ የስሎቫኪያ ፕሬዝዳንት ዙዛና ካፑቶቫ በበኩላቸው “እስካሁን ልንገነዘበው እንኳን የማንችለው በጣም ከባድ ነገር ተከስቷል” ብለዋል።
አክለውም “በህብረተሰቡ ውስጥ የምናያቸው የጥላቻ ንግግሮች ወደ ጥላቻ ድርጊቶች ያመራሉ” ብለዋል።