የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ቪኤአር ይወገድ በሚለው ሐሳብ ላይ ድምፅ ሊሰጡ ነው

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች በሚቀጥለው ወር በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ቪኤአር ይቅር ወይስ ይቀጥል የሚለውን በድምፅ ይወስናሉ።

ዎልቭስ የተሰኘው ክለብ ለፕሪሚዬር ሊጉ ባስገባው የመፍትሔ ሐሳብ መሠረት ነው 20 ክለቦች በቪኤአር ዕጣ ፈንታ ላይ ድምፅ ለመስጠት በመጭው ሰኔ የሚሰየሙት።

ክለቡ እንዳለው ምንም እንኳ "ቪኤአር ለበጎ ሥራ" ቢሆንም ጥቅም ላይ የዋለው "ያልታሰባበቸው በርካታ አሉታዊ ጎኖቹ በደጋፊዎች እና በእግር ኳስ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠለሽ እያደረጉት ነው።"

ቪኤአር በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው በአውሮፓውያኑ 2019 ሲሆን ዓላማው በወሳኝ ውሳኔዎች ላይ ዳኞችን ማገዝ ቢሆንም በተለይ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በርካታ አከራካሪ ውሳኔዎች ተላልፈዋል።

የዎልቭስ መግለጫ አክሎ እንደሚለው "የውሳኔን ትክክለኛነት ትንሽ ከፍ ለማድረግ በሚል የጨዋታው መንፈስ እየተነካ ነው።"

ፕሪሚዬር ሊጉ ቪኤአርን በተመለከተ የሚነሱ ቅሬታዎችን "እንደሚቀበል" ቢገልጥም ቴክኖሎጂውን ግን "ሙለ በሙሉ እንደሚፈልገው" እና ከዳኞች ማሕበር ጋር በጋራ በመሥራት ለውጥ ለማምጣት እንደሚሞክር አሳውቋል።

በፕሪሚዬር ሊጉ ሕግ መሠረት ማንኛውም አዋጅ እንዲፀድቅ ሁለት ሶስተኛ ድምፅ ማግኘት አለበት። ይህ ማለት ከ20 ቡድኖች ቢያንስ 14 ቡድኖች ሊደግፉት ይገባል።

የሊጉ ክለቦች በሚቀጥለው የውድድር ዓመት [2024/25] 'ሰሚ አውቴሜትድ' የሆነ የኦፍሳይድ [ከጨዋታ ውጭ] ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እንዲደረግ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

በርካታ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አሠልጣኞች በአንዳንድ ቪኤአር ውሳኔ ደስተኛ እንዳልሆኑ የገለጡ ሲሆን የዎልቭሱ ጋሪ ኦኒል አንዱ ናቸው።

ባለፈው ሚያዚያ ዎልቭስ ከዌስትሀም በነበረው ፍልሚያ ቡድናቸው በመጨረሻው ደቂቃ አቻ የሚያደርግ ጎል አስቆጥሮ በቪኤአር የተሻረባቸው ኦኒል ወደ ዳኞች ክፍል ሄደው ንግግር በማሰማታቸው ተቀጥተው ነበር።

ኖቲንግሀም ፎረስት ከኤቨርተን ጋር በነበረው ፍልሚያ ሶስት የፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄዎችን ተከልክያለሁ በማለት በማሕበራዊ ሚድያ ገፁ መግለጫው ማውጣቱ አይዘነጋም።

ቶተንሀም ከሊቨርፑል በጥቅምት ወር ባደረጉት ጨዋታ ሉዊዝ ዲያዝ ያስቆጠራት ጎል ከጨዋታ ውጭ መባሏ እጅግ አከራካሪ ከነበሩ የቪኤአር ውሳኔዎች መካከል ነበሩ።

ባለፈው የካቲት የሊጉ ዋና የእግር ኳስ ኦፊሰር ቶኒ ስኮልስ ቪኤአር ዳኞች ይሠሩት የነበረውን ስህተት የቀነሰ ቢሆንም በጣም ረዥም ደቂቃ እየወሰደ ነው ብለው ነበር።

የዳኞች ማሕበር ኃላፊ ሀዋርድ ዌብ በአንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ በተደጋጋሚ እየቀረቡ አከራካሪ የሚባሉ ውሳኔዎችን የሚተነትኑ ሲሆን የሜዳ ላይ ዳኞች እና የቪኤአር ዳኞች ያደረጉትን ልውውጥም ለሕዝብ ይፋ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ።

ባለፈው ወር ስዊድን ቪኤአርን አልጠቀምም በማለት ከ30 አውሮፓ እግር ኳስ ማሕበር አባላት ብቸኛዋ ሀገር ሆናለች።