ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለማኅበራዊ ሚዲያ መክፈል ያዋጣል?
እውነቱን ልናገር፤ የኤሎን መስክን ኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) በክፍያ አባል ሆኛለሁ ትላለች የቢቢሲ ዘጋቢ ዞይ ክሌንማን።
"ለምንድነው ለዓለም ሀብታሙ ሰው ገንዘብህን የምትሰጠው?" ሲል ወዳጇ ጠየቃት።
ትክክለኛ ነጥብ ብታነሳም እኔ ግን ያደረኩት በሁለት ምክንያቶች ነው አለች።
የመጀመሪያው ጥቂት የውሸት አካውንቶቼ እንዲንቀሳቀሱ እንደሚረዳኝ ስለማውቅ እና መመዝገቤ ሰማያዊ ባጅ ስለሚያስገኝልኝ ነው።
ሁለተኛው ደግሞ የኤክስ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የሆነውን ግሮክን በቀላሉ ለማግኘት የሚረዳ መንገድ በመሆኑ ነው። ክፍያውን የፈጸምኩት ከራሴ ኪስ እንጂ ከቢቢሲ ሒሳብ አልነበረም ብላለች።
ኤክስ ላይ በደንበኝነት መመዝገብ የተደበላለቀ ጥቅም ነው ያለው። ከተመዘገቡ በኋላ ከስምዎ ትይዩ የሚታየውን "ሰማያዊ ምልክት" ለመደበቅ አማራጭ ይሰጣል ስትልም ታክላለች።
በአንዳንድ ተጠቃሚዎች መካከል “ተቀባይነትን ስለመግዛት" የሚኬድበት መንገድ ጥልቅ የሆነ የጥላቻ ስሜት ፈጥሯል። ቁም ነገሮችን በመለጠፍ የበለጠ ትኩረትን ከማግኘት በክፍያ መሆኑ ነው ቅሬታው።
ዞይ ከራሷ ልምድ አንጻር ስትገልጸው፣ "ይህን በማድረጌ ብዙ ለውጥ ይመጣል ብዬ አልጠበኩም ነበር። ግን የተሻሻሉ ነገሮች አሉ" ትላለች።
ረዣዥም ጽሑፎችን መለጠፍ እና ካስፈለገም ማረም መቻሉ አንደኛው ነው።
የማስታወቂያዎችን ቁጥር መቀነሱንም አደንቃለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ለአገልግሎቱን ገንዘብ እየከፈልኩ አይፈለጌ እና ማሽን ሠራሽ መረጃዎችን የበለጠ በማግኘቴ ተናድጃለሁ ትላች።
በአይሪሽ የሲቪል ነፃነቶች ምክር ቤት ከፍተኛ ባልደረባ የሆነው የቀድሞ የማስታወቂያ ሥራ አስፈጻሚው ጆኒ ሪያን በአንዳንድ ሁኔታዎች ከተመዘገቡ ደንበኞች ይልቅ አስተዋዋቂዎችን ለማስደሰት ቀላል ነው ብሏል።
"በአጠቃላይ ከታየ ማስታወቂያ አስነጋሪው ስለይዘቱ ምንነት ምንም ደንታ የለውም" ብለዋል።
"ለምርቱ ካልከፈሉ እርስዎ ምርቱ ነዎት" የሚል የቆየ አባባል አለ።
ይህ ማለትም አንድን ነገር በነጻ እየተጠቀሙ ከሆነ የኩባንያው ባለቤት እርስዎን ከማስከፈል ያስቀመጡትን መረጃ እየወሰደ ድርጅቶች ከፍለው እንዲያስተዋውቁበት ያደርጋል።
የተለመደ እና ትርፋማ የንግድ ሞዴል ነው። "ዳታ አዲሱ ነዳጅ ነው!" የሚለውን ትልቅ አባባል ከጥቂት ዓመታት በፊት በቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ውስጥ ነበር የሰማሁት።
ይህ የነዳጅ መጠባበቂያ ክምችት ላይ ትንሽ እያሽቆለቆለ ይመስላል። ምክንያቱም የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የደንበኝነት ምዝገባዎችን እንደ አማራጭ እያዩ መጥተዋል።
ከስድስት ወራት በፊት ሜታ በአውሮፓ ለሚገኙ የፌስቡክ እና የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች ከማስታወቂያ ነጻ የደንበኝነት ምዝገባ ሞዴል አስተዋውቋል።
በሞባይሎች በወር 14 ዶላር ያስከፍላል። ይህም ለበይነ መረብ አገልግሎት አማካይ የሚባል ክፍያ ነው።
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ እስካሁን ምን ያህል ሰዎች እንደተመዘገቡ ሊነግረኝ አልፈቀደም።
ይህ የሸማቾች ምርጫን በተመለከተ ከአዲሱ የአውሮፓ ህብረት ህግ ጋር ለመስማማት የወጣ ይመስላል።
ሆኖም ግን አልተሳካም። የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ገንዘብን ወይም መረጃን የማስረከብ ሁለትዮሽ ውሳኔ በቂ ላይሆን ይችላል በሚል ሜታ ላይ ምርመራ ጀምሯል።
ከማስታወቂያ ነጻ የሆነ አማራጭን ጨምሮ ይፋ የሆነው ስናፕቻት ፕላስ በ2022 በተጀመረ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ተመዝጋቢዎችን አፍርቷል።
በ2023 የዩቲዩብ የፕሪሚየም ከማስታወቂያ ነፃ 100 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን አፍርቷል።
“ 'ማስታወቂያዎች መቼ ይመጣሉ' የሚል ፍራቻ ሳይኖር በቀላሉ መደሰት መቻል በህይወቴ የሚያስፈልገኝ ነገር ነው" ይላል የሶሻሊ ፓወርፉል መስራች እና የዩቲዩብ የረዥም ጊዜ ተመዝጋቢው ጀምስ ሃኪንግ።
ኔትፍሊክስ በበኩሉ ማስታወቂያዎችን ያካተተ ርካሽ የደንበኝነት ምዝገባ የጀመረ ሲሆን አማዞን ፕራይም ደግሞ ማስታወቂያዎችን በቪዲዮ ገጹ ላይ ከማስተዋወቅ ባለፈ ተጠቃሚዎቹ (ተመዝጋቢ የሆኑትን ጨምሮ) ማስታወቂያውን ለማስወገድ ተጨማሪ ክፍያ እየጠየቀ ነው።
ጆኒ ሪያን ይህ ድብልቅ ሞዴል ከሁሉም ሁሉ የከፋውን ይወክላል በማለት ይከራከራሉ። ማስታወቂያዎችን ማየትም ሆነ ክፍያ መክፈል “የሚገርም ነገር ነው” ብለዋል።
በአጠቃላይ የደንበኝነት ምዝገባዎች "ከአዲስ ገበያ ወጥተው ወደተበላበት ገበያ የሚያድገው ሂደት አካል ናቸው" ሲሉ የኤክሰፕሽን ቪው ጋዜጣ መስራች አዜም አዝሃር ተናግረዋል።
"አዳዲስ ደንበኞችን ማግኘት ስለማይቻል እንዴት ገቢዎን እንደሚጨምሩ ማወቅ ያስፈልግዎታል” ብለዋል።
"በፍጥነት ለመሳፈር ለመክፈል ፈቃደኛ የሆኑ የአየር መንገድ ተጠቃሚዎች እንዳለ ሁሉ ለመክፈል ፈቃደኛ የሆኑ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችም አሉ።”
ማህበራዊ አውታረ መረቦች በጥንቃቄ መሄድ እንዳለባቸው ግን ያስጠነቅቃሉ።
"ሁሉም ሰው መክፈል ካለበት የሚጠቀሙበት ሰዎች በጣም ጥቂት ብቻ ይሆናሉ። ስለዚህ ተሳትፎ ይቀንሳል፤ ብዙም የማይፈለግ ይሆናል። እንዲያጋሩ እና ይዘት የሚፈጥሩ ነጻ ተጠቃሚዎችን እና ትንሽ ሻል ያለ አገልግሎት ለማግኘት መክፈል በሚፈልጉ ሰዎች መካከል ሚዛን አለ" ሲሉ አክለዋል።
ምናልባት ኤክስ ይህን ተምሮታል። የደንበኝነት ምዝገባ ሞዴሉን በጀመረ በቀናት ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ላሏቸው ሁሉም አካውንቶች ነጻ የፕሪሚየም መለያ ሰጥቷል።
በቅርቡ ደግሞ ይህንን ከሁለት ሺህ 500 በላይ ፕሪሚየም ተከታዮች ላላቸውም ክፍት አድርጓል።
ይህ የሚመጣው ብዙ መድረኮች በተሳካ ሁኔታ የደንበኝነት ምዝገባ ገንዘብ ለማግኘት በመሞከራቸው ነው።
ከከፋይ ደንበኞች ጀርባ በምቾት የተቀመጡት በርካቶች ናቸው።
በስካንዲኔቪያ ደግሞ ውጤታማ ሆኗል። ባለፈው አመት የሮይተርስ ኢንስቲትዩት እንደዘገበው 33 በመቶ ስዊድናውያን ለበይነ መረብ ዜና ክፍያ ፈጽመዋል።
አዝሃር 100 ሺህ የሚጠጉ ተመዝጋቢዎች ሰብስታክ ላይ አሉት። ለመጠቀም ነፃ ነው። ሰብስታክ ከደንበኝነት ምዝገባዎች ላይ 10 በመቶ ኮሚሽን ይቀበላል።
ሰብስታክ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በርካታ ህትመቶችን ለማግኘት መመዝገባቸውን ይናገራል። ሰብስታክ ተጠቃሚዎች ማስታወቂያዎችን ማካተት አይፈቀድላቸውም።
የሰብስታክ መስራች ሃሚሽ ማኬንዚ የስኬቱን ሚስጥር "ወጥነት ያስፈልጋል። መታየትህን መቀጠል አለብህ። በአንባቢዎችህ አእምሮ ውስጥ ተፈላጊነትን መፍጠር አስፈላጊ ነው" ሲል ገልጿል።
"ከአንተ ጋር ግንኙነታቸውን ያዳብራሉ። ከማስታወቂያ በተቃራኒ እውነቱን መናገር አለብህ።”
አንድ ቀን በእነሱ ላይ ላሉት ይዘቶች የደንበኝነት ምዝገባ በሚወስዱ በማህበራዊ አውታረመረቦች እና እንደ ሰብስታክ ባሉ የግለሰብ ፈጣሪ ሞዴሎች መካከል “ትልቅ ፉክክር” እንደሚኖር ማኬንዚ ያስባል።
"ተመልካቾች ምርት ከመሆን ይልቅ ደንበኛ ሲሆኑ በጣም የተሻለ ዓለም ይሆናል” ብሏል።