ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ልብሳችን ወልቆ ተፈትሸናል ሲሉ ኳታር አየር መንገድን የከሰሱ ሴቶች መዝገብ ውድቅ ሆነ
የኳታር አየር መንገድ ልብሳችንን አውልቆ ጥብቅ ፍተሻ አድርጎብናል ሲሉ የከሰሱ የአምስት አውስትራሊያውያን ሴቶች ክስ ውድቅ ሆነ።
በአውሮፓውያኑ 2020 ሐማድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ ሕፃን ልጅ ያለጠባቂ መገኘቱን ተከትሎ ነበር አየር መንገዱ ክስ ያቀረቡትን እና የሌሎች ሴት መንገደኞችን ልብስ አስወልቆ የፈተሸው።
ኳታር አየር መንገድ ሴቶቹ ወልደው እንደሆን ለመፈተሽ ያደረገው መኩራ ከበርካታ አገራት ወቀሳ እንዲገጥመው አድርጎ ነበር።
የአውስትራሊያ ፍርድ ቤት የኳታር መንግሥት ንብረት የሆነው አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ጉዞ ሕግ መሠረት በዚህ ድርጊቱ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም ብሏል።
አምስቱ ሴቶች ለአውስትራሊያ ፌዴራል ፍርድ ቤት በ2021 ያቀረቡት የክስ መዝገብ “ያለፈቃዳችን ሰውነታችን ተነክቷል”፤ እንዲሁም ያለጥፋታችን በቁጥጥር ሥር ውለናል ይህ ደግሞ የአእምሮ ጤናችን ላይ ጉዳት አምጥቷል ይላል።
ከዩናይትድ ኪንግደ እና ከኒው ዚላንድ የመጡ ተጓዦች ላይም ፍተሻ ቢደረግባቸውም ክስ አላቀረቡም።
ረቡዕ ዕለት ዳኛ ጆን ሆሊ በሰጡት ውሳኔ በሞነትሪያል ኮንቬንሽን መሠረት የኳታር አየር መንገድ በዚህ ድርጊቱ ክስ ሊቀርብበት አይገባም ብለዋል።
የሞንትሪያል ስምምነት መንገደኛ ላይ ሞት ቢደርስ አሊያም ጉዳት ቢያጋጥም አንድ አየር መንገድ ላይከሰስ እንደሚችል የሚያትት ነው።
ዳኛው አክለው የኳታር ፖሊስ መንገደኞቹን ከአውሮፕላን አውርዶ እንዲፈትሽ እንዲሁም ነርሶቹ ምርመራ እንዲያደርጉ የኳታር አየር መንገድ ሠራተኞች የፈጠሩት ጫና የለም ብለዋል።
በተጨማሪ ሴቶቹ በኳታር አቪዬሽን ተቆጣጣሪ ላይ ያቀረቡት ክስ፣ ተቆጣጣሪው ከአገር ውጭ ሊከሰስ ስለማይችል ውድቅ ሆኗል።
ነገር ግን ዳኛው እንዳሉት ሴቶቹ በኳታር አየር መንገድ ተቀጥሮ ሐማድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን የሚያስተዳድረው ማታር የተሰኘውን ድርጅት መክሰስ ይችላሉ።
ሴቶቹ ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ በሰጡት ቃል ለፍተሻ ፈቃደኛ እንዳልነበሩ እና ምን እየሆነ እንዳለ መረጃ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።
ሙሉ ስሟን ከመናገር የተቆጠበችው ማንዲ “እየተደፈርኩ እንዳለሁ ነው የተሰማኝ” ስትል ተናግራ ነበር።
አንዲት ሌላ ተሳፋሪ ደግሞ ታፍና እየተወሰደች እንዳለ አምና እንደነበር ትናገራለች።
በወቅቱ የኳታር ባለሥልጣናት ተጥሎ የተገኘው ጨቅላ እንክብካቤ እየተደረገለት እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኻሊድ ቢን ኻሊፋ ቢን አብዱላዚዝ አል ታኒ ደግሞ “ሴቶች መንገደኞች ላይ የደረሰው ነገር አሳዝኖናል. . . የሆነው ነገር የኳታርን እሴት የሚወክል አይደለም” ሲሉ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
ጠበቃ ዳሚያን ስቱርዛከር ሴቶቹ ከኳታር ይፋዊ ይቅርታ ይፈልጋሉ፤ አየር ማረፊያው ደግሞ መሰል ድርጊት ድጋሚ እንዳይፈጽም ይሻሉ ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ወጥተን መናገር የፈለግነው ሌሎች ሴቶች እንዲህ ዓይነት ሞራል የሚነካ አስነዋሪ ድርጊት እንዳይደርስባቸው ነው” ስትል ከሴቶቹ አንዷ ለቢቢሲ ተናግራለች።