ታዋቂው ካርቱኒስት ኔታንያሁን በጋዛ ላይ በሚያሳየው ካርቱን ምክንያት ከሥራው ተባረረ

ስመ ጥሩ የጋርዲያን ጋዜጣ ካርቱኒስት ስቲቭ ቤል በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ዙሪያ በሳለው ካርቱን ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት ከሥራው ተባረረ።

ካርቱኑ ኔታንያሁ ሆዳቸው ላይ ቀዶ ጥገና ሲያከናውኑ ያሳያል። ቀዶ ጥገናውን የሚያደርጉበት ቦታ የጋዛ ሰርጥን ካርታ ይዟል።

ካርቱኒስቱ ለመባረር ምክንያት የሆነው የዊሊያም ሼክስፒር ተወዳጅ ድርሰት ከሆነው የቬኑሱ ነጋዴ ዋነኛ ገጸባህርይ ሻይሎክ ጋር በማገናኘት ሌላ ትርጉም በመሰጠቱ ነው።

ይሁዳዊ የሆነው አራጣ አበዳሪ በተቀመጠው ጊዜ ዕዳውን ያልከፈለ ተበዳሪ “ሙዳ ስጋውን” እንዲከፍልም ይጠይቃል።

ምስሉ የሻይሎክን ‘ፓውንድ ኦፍ ፍሌሽ’ (ሙዳ ስጋ) ስጠኝ የሚለውን ሊያመለክት እንደሚችል ጋዜጣው ከጠቆመ በኋላ ነው።

ካርቱኒስቱ በበኩሉ በ60ዎቹ የተሳለው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሊንደን ቢ ጆንሰን ካርቱን መነሻ እንደሆነው ጠቁሟል።

ካርቱኑን ከሁለት ሳምንት ማስረከቡንና "ከአራት ሰዓት በኋላ ... ከቢሮ እንግዳ የሆነ 'ፓውንድ ኦፍ ፍሌሽ (የሙዳ ስጋ) የሚል ሚስጥራዊ መልዕክት ያዘለ የስልክ ጥሪ ደረሰኝ ሲል ኤክስ ላይ አስፍሯል።

ቤል "ይቅርታ አልገባኝም" በማለት ቢናገረም የተሰጠው ምላሽ "ይሁዳዊ፣ የሙዳ ስጋ፣ ፀረ-ሴማዊ ምሳሌያዊ አነጋገር" የሚል ነበር።

በሼክስፒር የቬኑሱ ነጋዴ ውስጥ ስግብግብ የሆነው የአራጣ አበዳሪው ሻይሎክ በእንግሊዝ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ከታወቁት የተሳሳተ የአይሁዳውያን መገለጫዎች አንዱ እንደሆነ ይታሰባል።

በባርድ ዝነኛ ተውኔት ውስጥ ሻይሎክ የሰጠውን ብድር በሶስት ወር ውስጥ ተበዳሪው ካልመለሰ ሙዳ ስጋውን ከሰውነቱ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ውሉ አልታደሰም

የጋርዲያን ትርጉም ለእሱ ምንም ስሜት እንዳልሰጠው ቤል ለቢቢሲ ገልጿል።

“ምክንያቱም በካርቶኑ ላይ ኔታንያሁ በራሱ ላይ የቀዶ ጥገና ሊያከናውን መዘጋጀቱን ያሳያል። ስለተውኔቱ ምንም የሚጠቅስ ነገር የለም። ኔታንያሁ ቀዶ ጥገናውን ለማከናወን የቦክስ ጓንቶች አጥልቋል። ይህም ገና ያልታዩና የሚያስከትላቸውን አስከፊ መዘዞች የሚያሳዩ ናቸው።”

"ካርቱኑን ለመሳል መነሻ የሆነኝ የታላቁ የዴቪድ ሌቪን የፕሬዚዳንት ሊንደን ጆንሰን (LBJ) ካርቱን ነው። ሌቪን በካርቱኑ የፕሬዝዳንቱ የቀዶ ጥገናን ጠባሳን በቬትናም ካርታ መልክ በመሳል ነው ያሳየው።"

የጋርዲያን ኒውስ እና ሚዲያ ቃል አቀባይ በበኩላቸው "የስቲቭ ቤልን ውል ላለማደስ ውሳኔ ተላልፏል። የስቲቭ ቤል ካርቱኖች ባለፉት 40 ዓመታት ለጋርዲያን በጣም ጠቃሚ ነበሩ። ለዚህም እናመሰግናለን። መልካሙን ሁሉ እንመኝለታለን" ብለዋል።

ጉዳዩ መነጋገሪያ የሆነው በጋዛ ሰርጥ የተፈጠረው ግጭት ከተከሰተ ከቀናት በኋላ በመፈጠሩ ነው።

ሌሎች ካርቱኖች

ቤል ፀረ ሴማዊ ምስሎችን ተጠቅሟል ተብሎ ሲከሰስ የመጀመሪያው አይደለም።

እአአ በ2020 ሰር ኪር ስታርመር የዩናይት ኪንግደም የቀድሞ የሌበር መሪ የነበረውን ጄረሚ ኮርቢን ጭንቅላት በሳህን ላይ እንደያዘ የሚያሳየው ካርቱን ስሎ ነበር።

ይህም የአይሁዱ ንጉሥ ሄሮድስ ሴት ልጅ ለሆነችው ሰሎሜ የቀረበውን የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ ለማመላከት ነው በማለት አንዳንዶች ተርጉመውታል።

በዚያው ዓመት መጀመሪያ ላይ የቢቢሲው ሊቀመንበር ሪቻርድ ሻርፕን የሚያሳየው ካርቱን ፀረ ሴማዊ ነው ተብሎ ከተተቸ በኋላ ጋርዲያን ይቅርታ ጠይቋል።

ሰዓሊው ማርቲን ሮውሰንም ይቅርታ ጠይቋል።