በኬንያ እና በደቡብ አፍሪካ ተቃዋሚዎች በጠሩት የተቃውሞ ሰልፍ ምክንያት ውጥረት ነግሷል

በኬንያ እና በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተቃዋሚዎች በጠሯቸው ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች ምክንያት ዛሬ ሰኞ ከተሞች ውስጥ ከባድ ውጥረት ነግሷል።

በዚህም ሳቢያ በተቃዋሚዎች እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት ሊከሰት ይችላል በሚል ነዋሪዎች እና ተቋማት በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ከተለመደ እንቅስቃሴያቸው ተቆጥበው የሚከሰተውን ለማወቅ እየተጠባበቁ ነው።

የኬንያ እና የደቡብ አፍሪካ የፀጥታ ኃይሎችም ማንኛውንም ሕገወጥ የተቃዋሚዎችን እንቅስቃሴ እንደማይታገሱ ያስጠነቀቁ ሲሆን፣ በኬንያ ፖሊስ የተፈቀደ ሰልፍ የለም ብሏል።

ኬንያ ውስጥም በኑሮ መወደድ እና በሌሎች ፖለቲካዊ ምክንያቶች ባለፈው ዓመት በምርጫ የተሸነፉት ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ደጋፊዎቻቸው አደባባይ እንዲወጡ እና መንግሥትን እንዲቃወሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ዛሬ ሰኞ ይደረጋል በተባለው ተቃወሞ ምክንያት ከማለዳው ጀምሮ ግርግር የሚበዛባቸው የናይሮቢ ጎዳናዎች ጭርብ ብለው የሚታዩ ሲሆን፣ በርካቶችም ከእንቅስቃሴያቸው ተቆጥበዋል።

የኬንያ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ እንዳለው በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በተለይ በቁልፍ የመንግሥት ተቋማት አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፀጥታ ኃይሎች ተሰማርተው ይገኛሉ።

የኬንያ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ባለፉት ቀናት በመላው አገሪቱ በፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና በመንግሥታቸው ላይ ሕዝባዊ ተቃውሞ እንዲደረግ ጥሪ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ኦዲንጋ ዛሬ ሰኞ እንዲደረግ ለጠሩት የተቃውሞ ሰልፍ ምክንያቱ በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ የሆነው የኑሮ ውድነት እና በሕገወጥ መንገድ ሥልጣን ይዘዋል ያሏቸውን ፕሬዝዳንት ለመቃወም ነው።

የተቃዋሚ ሰልፍኞቹ ወደ ፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት በመሄድ ተቃወሞ ያሰማሉ የተባለ ሲሆን፣ ፖሊስ ግን እሁድ ዕለት እንዳስጠነቀቀው የተፈቀደ ሰልፍ እንደሌለ እና ወደ የትኞቹ የተከለከሉ አካባቢዎች የሚደረጉ ሰልፎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

በናይሮቢ ያሉ የንግድ ተቋማት ደግሞ በተቃዋሚዎች የተጠራው ሰልፍ ሥራችንን ያስተጓጉላል በሚል ሌላ የተቃውሞ ሰልፍ ጠርተው የነበረ ቢሆንም፣ ፖሊስ የትኛውም አይነት ሰልፍ እንዲካሄድ ይፋዊ ፈቃድ እንዳልተሰጠ ገልጾ ከልክሏል።

ሊካሄድ በታሰበው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ግጭት ይከሰታል ተብሎ የተሰጋ ሲሆን፣ የኬንያ ፖሊስም የአገሪቱን ሰላም ለማናጋት በሚሞክር በየትኛው አካል ላይ ከባድ እርምጃ እንደሚወስ አስጠንቅቋል።

ከስድስት ወራት በፊት ሥልጣን የተረከቡት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶም በአሁኑ ወቅት የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ የሚያበቃ ምንም ምክንያት እንደሌለ ተናግረው፣ ተቀናቃኛቸው ራይላ ኦዲንጋን በአገሪቱ ግጭት እና ብጥብጥ ለመፍጠር ይፈልጋሉ ሲሉ ከሰዋቸዋል።

ኦዲንጋ ደጋፊዎቻቸው የሚያደርጉት የተቃውሞ ሰልፍ ሰላማዊ እንደሚሆኑ ቢገልጹም፣ ነገር ግን ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ውስጥ የተቃውሞ ሰልፎች ሲካሄዱ ግጭቶች ሲያጋጥሙ እንደነበር አይዘነጋም።

በደቡብ አፍሪካም ዛሬ ለማካሄድ በተቀደው የተቃዋሚዎች ሰልፍ ወቅት ቁልፍ የመሠረተ ልማት ተቋማትን ለመጠበቅ በመላዋ አገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች መሰማራታቸው ተዘግቧል።

አክራሪው ተቃዋሚ ፓርቲው የኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ ፓርቲ የአገሪቱ ዜጎች ለተቃውሞ ቤታቸው ውስጥ በመዋል አገሪቱ ከእንቅስቃሴ ውጪ እንድትሆን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

ፓርቲው ተቃውሞውን የጠራው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ምጣኔ ሀብቱን የያዙበት መንገድ ችግርን አስከትሏል በማለት ሥልጣናቸውን እንዲለቁ እየጠየቀ ነው።

በአሁኑ ወቅት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ባለው ምጣኔ ሀብታዊ ሁኔታ፣ በሥራ አጥነት፣ በሙስና እና በተደጋጋሚ በሚቋረጠው የኤሌክትሪክ ኃይል ምክንያት በሕዝቡ ውስጥ ከፍተኛ ቅሬታ እንዳለ ይዘገባል።

ነገር ግን ተቃዋሚው ፓርቲ ደቡብ አፍሪካን ሙሉ ለሙሉ ከእንቅስቃሴ ውጪ ለማድረግ በጠራው የዛሬው የተቃውሞ ሰልፍ ምን ያህሉ የአገሪቱ ሕዝብ በመሳተፍ ድጋፉን ያሳያል የሚለው እስካሁን ግልጽ አይደለም።

በኬንያ እና በደቡብ አፍሪካ ዛሬ ሰኞ መጋቢት 11/2015 ዓ.ም. ይካሄዳል በተባለው የተቃውሞ ሰልፍ ምክንያት በዋና ዋና ከተሞች የሚካሄዱ የተለመዱ እንቅስቃሴዎች የተገቱ ሲሆን፣ ትልልቅ ተቋማት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ተዘግተዋል።

የኬንያ አየር መንገድም ለሠራተኞቹ እና ለደንበኞቹ ደኅንነት ሲል በሁለቱ አገራት ያሉ የትኬት መሸጫ ቢሮዎቹ ሰልፉ በሚካሄድበት ዕለት ዝግ እንደሚሆኑ አሳውቋል።