በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዢያ አውሮፕላኖች ላይ ስለደረሱ አደጋዎች መረጃ በመደበቁ ቦይንግ ተቀጣ

በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዢያ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ ከደረሱ አደጋዎች በኋላ ለባለሃብቶች የአደጋውን መንስኤ በመደበቁ 200 ሚሊዮን ዶላር ተቀጣ። 

የቦይንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ዴኒስ ሙሌንበርግ አደጋው በምን ምክንያት እንደተፈጠረ እያወቁ ሐቁን ባለመናገራቸው በግል 1 ሚሊዮን ዶላር ተቀጥተዋል።

የአሜሪካ የአክሲዮን ገበያ ተቆጣጣሪ አካል እንደሚለው ይህ አውሮፕላን አምራች ቦይንግ እና ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዴኒስ ሙለንበርግ ሆን ብለው የሚያውቁትን መረጃን ደብቀዋል። 

ይህን ያደረጉትም የቦይንግን ስምና ዝና ለመጠበቅ በሚል ነው። 

ይሁንና ጠቃሚ መረጃን በመደበቃቸው በአክሲዮን ገበያ የተሰማሩ ባለሀብቶችን አሳስተዋል። ባለሃብቶቹ ከአደጋው በኋላም መዋዕለ ነዋያቸውን በድርጅቱ ላይ ማፍሰሳቸውን የቀጠሉት አደጋው የደረሰበትን ዋነኛ ምክንያት የቦይንግ ኃላፊዎች እያወቁ ባለመናገራቸው ነው።

ባለሀብቶቹ በተሳሳተ መረጃ ምክንያት ለደረሰባቸው ኪሳራ ቦይንግን እና ዋና ሥራ አስፈጻሚውን ከሰዋል።

737 ማክስ አውሮፕላኖች አደጋ ከደረሰባቸው በኋላ ለ20 ወራት ያለ ሥራ እንዲቆሙ መደረጋቸው ይታወሳል።

ይህም የሆነው በቴክኒክ ችግር ምክንያት በሁለት አገሮች በሁለት የተለያየ ጊዜ አደጋ ደርሶ በድምሩ 346 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ነው። 

“ችግር በሚከሰት ጊዜ ኩባንያዎች ሙሉ፣ ሚዛናዊና እውነተኛ መረጃን ለገበያውና ለሕዝብ ማሳወቅ ግዴታ አለባቸው፤ ቦይንግ ይህን አላደረገም ብለዋል” ጉዳዩን የተመለከተው አካል። 

“ቦይንግና ሥራ አስፈጻሚው እጅግ ወሳኝ መረጃ በእጃቸው እያለ ለትርፍ ሲሉ ሸሽገው ቆይተዋል” ተብሏል።

ይህ ሳያንስ ቦይንግም ሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አደጋው የደረሰበት ምክንያት በምርመራ ከተደረሰበት በኋላ የምርመራውን ውጤት አልተቀበሉትም እንዲሁም አላስተባበሉም፤ ዝምታን መርጠዋል ብሏል የአክሲዮን ገበያው ተቆጣጣሪ አካል።

“በላየን ኤየር 610 አውሮፕላን እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ 302 በረራ የደረሰውን አደጋ መቼም አንረሳውም፤ ከአደጋዎቹ በኋላ የደኅንነት አሠራራችንን ቀይረናል” ብሏል ቦይንግ ለደረሰበት ክስ በሰጠው ምላሽ። 

ጨምሮም፣ “ከአደጋዎቹ በኋላ የደኅንነት ፍተሻ፣ ጥራት እና ግልጽነት ቅድሚያ የምንሰጣቸው መርሆዎች ሆነዋል” ይላል ቦይንግ። 

ይሁንና ቦይንግ በወቅቱ አውሮፕላኖቹ የደኅነት እክል እያለባቸው ዝምታን በመምረጡና ባለሀብቶቹን ሆነ ብሎ በማሳሳቱ በአክሲዮን ገበያው መዋዕለ ነዋያቸውን ማፍሰስ ቀጥለው ለደረሰባቸው ኪሳራ 200 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ተወስኖበታል።

እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በጥቅምት 29/2018 ላየን አየር መንገድ በረራ ቁጥር 610 ከጃካርታ ሶዌካርኖ ሃታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ከተነሳ ከ13 ደቂቃ በኋላ በጃቫ ባሕር ተከስክሶ 189 ተሳፋሪዎችና የበረራ አስተናጋጆች በሙሉ ሞተዋል።

ይህ እጅግ ዘግናኝ አደጋ በደረሰ 5 ወራት እንኳ ሳያልፍ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 302 ከአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ወደ ናይሮቢ በመጓዝ ላይ የነበረ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በተመሳሳይ በተነሳ በ6 ደቂቃቆች ውስጥ ተከስክሶ ተሳፍረው የነበሩ 157 ሰዎች በሙሉ ሞተዋል።

በኋላ በምርመራ እንደተደረሰበት ከሆነ የሁለቱም አደጋዎች መንስኤ በምርት ወቅት ለአውሮፕላኑ የአቅጣጫ ቁጥጥር እንዲያደርግ የተገጠመለት በምህጻር ኤምካስ የሚባለው አካሉ እክል ስለነበረበት ነው። 

ቦይንግና ዋና ሥራ አስፈጻሚው የመጀመርያው ማክስ 737 አውሮፕላን ከተከሰከሰ በኋላ ሁሉም የቦይንግ ማክስ አውሮፕላኖች ይህ ችግር እንዳለባቸው ያውቁ ነበር ተብሏል።

ሆኖም የቦይንግ ገበያ፣ ስምና ዝና እንዳይጎድፍ ሲባል ብቻ አውሮፕላኖቹ ችግር የለባቸውም በማለታቸው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሌላ አደጋ እንዲከሰት ሆኗል።

 ሁለቱን አደጋዎች ተከትሎ ቦይንግ በድምሩ 20 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሶበታል። ይህም በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች የተከፈለ ካሳን ይጨምራል።

ይህን አሰቃቂ አደጋ ተከትሎ የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አዲስ አውሮፕላኖች ሲመረቱ የደኅንነት ፍተሻን የሚያልፉበትን አሠራር ሙሉ በሙሉ የቀየረ አዲስ መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል።