የኢትዮጵያውያን አስክሬን መገኘቱን ተከትሎ የማላዊ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

25 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አስክሬን ያለበት የጅምላ መቃብር መገኘቱን ተከትሎ የማላዊ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።

ምዚምባ በተባለ የማላዊ ግዛት የ25 ኢትዮጵያውያን አስክሬን በጥብቅ ደን ውስጥ በጅምላ ተቀብሮ ባለፈው ሳምንት መገኘቱ ይታወሳል።

የአካባቢው ወጣቶች ደኑ ውስጥ የሚያውክ ሽታ እንዳለ መጠቆማቸውን ተከትሎ ነበር አስክሬኖቹ በቁፋሮ የተገኙት።

ይህ የጅምላ መቃብር ከተገኘ በኋላ በቅርብ ርቀት ሌላ የጅምላ መቃብር ተገኝቶ ተጨማሪ አራት አስክሬኖችን ፖሊስ አውጥቷል።

የማላዊ የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር ጃን ሴንዴዝ “በጣም የሚያሳዝን ነው። አስከፍቶናል። መንግሥታችን እንዲህ ያለ ድርጊት በጽኑ ያወግዛል። ትክክል አይደለም። በጎ አይደለም” ሲሉ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።

ፖሊስ ምርመራ እያደረገ እንደሆነና ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ እጃቸው ያለበት ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንደሚውሉ አክለዋል።

ኢትዮጵያውያኑ በምን ምክንያት እንደሞቱ ለማወቅ የአስክሬን ምርመራ ይደረጋል።

የጅምላ መቃብሩ ከተገኘበት ጥበቅ ደን ርቆ በሚገኝ ሌላ ጥብቅ ደን ውስጥ 72 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ተገኝተው በፖሊስ ተይዘዋል።

በጥብቅ ደን ውስጥ ስደተኞቹ እንዳሉ ለፖሊስ ጥቆማ ከደረሰው በኋላ ነው የተያዙት።

ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በማዘዋወር የተጠረጠሩ ዐሥር የማላዊ ዜጎች ታስረዋል። እስከሁን ግን ፍርድ ቤት አልቀረቡም።

ሚኒስትሯ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ መንግሥት ድንበር አቅራቢያና በአውራ ጎዳናዎች ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር አጥብቋል።

በተለይም በሰሜናዊ የማላዊ ግዛት ሰው አዘዋዋሪዎችን ለመያዝ እየተሞከረ ይገኛል።

አብዛኞቹ ማላዊ የሚገቡ ስደተኞች ከምሥራቅ አፍሪካ የሚነሱ ናቸው።

የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም፣ ኢትዮጵያ ከማላዊ መንግሥት ጋር በመተባበር ስለ ክስተቱ ምርመራ እያደረገች ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አምባሳደር መለስ፣ በክስተቱ ሐዘን እንደተሰማቸው ገልጸው፣ የምርመራውን ውጤት ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

የማላዊ የሲቪል ማኅበራት፣ መንግሥት በአፋጣኝ የአስክሬን ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ሴንተር ፎር ሂውማን ራይትስ ሪሀብሊቴሽን እና ሴንተር ፎር ዴሞክራሲ ኤንድ ኢኮኖሚክ ዴቨሎፕመንት ኢኒሼቲቭ የተባሉ ሁለት የማላዊ ሲቪል ማኅበራት እንዳሉት፣ የጅምላ መቃብር መገኘቱ ሕገ ወጥ ስደት መበርታቱን ይጠቁማል።

አገሪቱ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ቀውስ ውስጥ እንደገባችና ቆራጥ እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም አሳስበዋል።

የሲቪል ማኅበር ሊቀ መንበር የሆኑት ሲልቨስተር ናሚዋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ስለ ጅምላ መቃብሮቹ ሲሰማ መላው የማላዊ ዜጎች ተደናግጠዋል።

መንግሥት ምርመራውን ባለሙያዎች እንዲያከናውኑ መፍቀድ እንዳለበትና ሰው አዘዋዋሪዎች ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ሌላው የሲቪል ማኅበር መሪ ማይክል ኬይታሳ “ተጎጂዎች ፍትሕ ይሻሉ” ብለዋል።

ያለፈው ሰኔ የመንግሥታቱ ድርጅት ባወጣው መግለጫ በማላዊ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በርካታ የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙና ብዝበዛ እንደሚደርስባቸውም ማስታወቁ አይዘነጋም።

ድዛሌካ በተሰኘው የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በወንዶች፣ በሴቶች እና በሕጻናት ላይ መጠነ ሰፊ ብዝበዛ እንደሚደርስ ይፋ የተደረገው በተባበሩት መንግሥታት የመድኃኒት እና የወንጀል ጽሕፈት ቤት (ዩኤንኦዲሲ) እና የማላዊ ፖሊስ ባደረጉት የጥምረት ክትትል ነው።

ማላዊ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከሚፈተኑ አገራት አንዷ ናት።

ከኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ሌሎም የአፍሪካ ቀንድ አገራት ወንዶች፣ ሴቶችና ሕጻናትም ጭምር በማላዊ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ አውሮፓ እና አሜሪካ ይሰደዳሉ።

ጉዟቸው ግን በስቃይና በእንግልት የተሞላ ባስ ሲልም ለሞት የሚዳርግ ነው።

ከሁለት ዓመት በፊት የማላዊ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞው የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ኡላዲ ሙሳን ከስደተኞች ዝውውር ጋር በተያያዘ የአምስት ዓመት እስራት ፈርዶበታል።