ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአፋር ክልል እየጨመረ የመጣው የምግብ ቀውስ አሳሳቢ እንደሆነ ተገለጸ
በአፋር ክልል እየጨመረ የመጣው የምግብ ቀውስ ስጋት እንዳጫረበት ድንበር የለሽ ዶክተሮች (ኤምኤስኤፍ) ገለጸ።
የሕክምና ግብረ ሰናይ ድርጅቱ እንዳስታወቀው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መሠረታዊ የሚባሉ የጤና ማዕከላትን እንዲሁም ንጹህ የመጠጥ ውሃ በማያገኙበት ሁኔታ ነው የሚኖሩት።
በተጨማሪም በርካታ ሕፃናት በከፋ የምግብ እጥረት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የዘንድሮው ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀርም አራት እጥፍ ብልጫ ባለው መልኩ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸውን ሕፃናትንም የቡድኑ አባላት ተመልክተዋል።
ከነዚህም ውስጥ 35 ሕፃናት የሞቱ ሲሆን አብዛኞቹም ወደ ሆስፒታል በገቡ በ48 ሰዓታት ውስጥ ነው ሕይወታቸው ያለፈው።
በክልሉ በምግብ እጥረት ተጎድተው የሚመጡ ሕፃናት ቁጥር በሦስት እጥፍ መጨመሩን ከወራት በፊት የዱብቲ ጀኔራል ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሁሴን አደም ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
በክልሉ ውስጥ ካሉ የጤና ማዕከላት አብዛኞቹ አገልግሎት ላይ እንዳልሆኑ ያስታወቀው ድርጅቱ፣ በሥራ ላይ ያሉት 20 በመቶ ብቻ ናቸው ብሏል።
ሆኖም በአፋር ክልል እየተከሰተ ያለው ቀውስ ከዚህም የከፋ ሊሆን እንደሚችል ጠቁሞ የረድኤት ማኅበረሰቡ አስቸኳይ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ እንደሆነ አሳስቧል።
በጦርነት ክፉኛ የተጎዳችው የትግራይ ክልልን ወደሚያዋስነው የአፋር ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠረውን ግጭት በመፍራት በርካታ ተፈናቃዮች ወደ ክልሉ ጎርፈዋል።
በትግራይ ክልል በተከሰተው ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የተፈናቀሉ ሲሆን የተወሰኑትም ከአንድ ወር በላይ በእግር ተጉዘው አፋር ደርሰዋል።
ተፈናቃዮቹን ጨምሮ በርካታ ነዋሪዎች በአፋር ለከፍተኛ ስቃይ የተጋለጡ ሲሆን ኤምኤስኤፍ አፋጣኝ ምላሽ እንደሚያስፈልግም አሳስቧል።
ከኤምኤስኤፍ በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ በክልሉ የሰብአዊ ሁኔታ አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጿል።
በተለይም ተፈናቃዮች በሚበዙበትና በተጨናነቁ አካቢዎች መሠረታዊ አገልግሎቶች አለመኖራቸው ሁኔታውን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎታል ብሏል።
በአፍዴራ ወረዳ ተፈናቃዮች በተጠለሉበት ሃርሱማ፣ የክልሉ ባለሥልጣናት ተፈናቃዮችን ወደ ሌላ ቦታ ለማዛወር ዕቅድ መያዛቸውን ተከትሎ የእርዳታ ስርጭት ተቋርጧል።
በስፍራው የምግብ እርዳታ ስርጭት የተደረገውም ከአንድ ወር በፊት መሆኑን አጋር ድርጅቶችን ዋቢ አድርጎ ኦቻ አስፍሯል።
በተመሳሳይም በቦታው ያለው የጤና፣ የውሃ እና የንፅህና አጠባበቅ ሁኔታ በቂ ባለመሆኑ የውሃ እጥረት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።
በስፍራው የውሃ ማጓጓዣ አገልግሎት ባለመኖሩ አብዛኞቹ ሕፃናት ባልታወቀ ተላላፊ የቆዳ በሽታ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ የኦቻ መግለጫ ያስረዳል።
ከክልሉ ዞን 2 የሚሰደዱ ተፈናቃዮች በሰመራ አቅራቢያ ወደ ዱብቲ ያለማቋረጥ እየገቡ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በአሁኑም ወቅት ስፍራው መሸከም ከሚችለው በላይ ከ30 ሺህ ተፈናቃዮች በላይ ደርሰዋል።
በዱብቲ ሆስፒታል ያለውም ሁኔታ አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል ያለው ተቋሙ፣ ከሆስፒታሉ አቅም በላይም በርካታ እርዳታ ፈላጊዎች እየደረሱ እንደሆነ ገልጿል።
በሌሎች የጤና ማዕከላት መሰጠት የነበረባቸው መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች በውሃ እጥረት፣ የመኝታ አቅም ውስንነት፣ የሰው ኃይል እና የሕክምና አቅርቦት እጥረት ምክንያት ዱብቲ ሆስፒታልን አጨናንቀውታል ብሏል።
የጤና ማዕከላትን አቅም ለማሳደግ እቅድ ተይዞ እየተሠራ ቢሆንም፣ በአፋር ክልል ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱ እያንዣበበ ያለውን ችግር ለመከላከል ፈጣን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ኤምኤስኤፍ ገልጿል።