ኦነግ ኦፌኮ ባንዲራዬን አላግባብ እየተጠቀመ ነው ሲል ቅሬታውን ገለጸ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ (ኦፌኮ) አርማውን ወይም ሰንደቅ አላማውን ያላግባብ እየተጠቀመበት ነው ሲል ቅሬታውን ለፓርቲው በደብዳቤ ገለጸ።

ኦፌኮ በተደጋጋሚ የኦነግን ባንዲራ ለፖለቲካዊ ጉዳዮች እየተጠቀመበት እንደሆነ በመግለጽ ከትናንት በስቲያ ግንቦት 29/2014 ዓ.ም. ደብዳቤ የጻፈ ሲሆን ባንዲራውን ከመጠቀም እንዲያቆምም ፓርቲውን ጠይቋል።

ለኦፌኮ የተጻፈው ደብዳቤ የአርማውን (የሰንደቅ አላማውን አጠቃቀም) በተመለከተ ግልጽነት እንዲኖር ለመጠየቅ እንደሆነም የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ደብዳቤው የተጻፈው ለኦፌኮ ሊቀ መንበር መረራ ጉዲና ሲሆን የኦፌኮ አመራር የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድንም በስም ጠቅሶ ባንዲራውን እየተጠቀሙ ነው ብሏል።

አቶ ለሚ እንደሚሉት በዚህም የአንድ ድርጅት አመራር የሌላ ፓርቲ ባንዲራ በምን መልኩ መጠቀም እንደሚችል ግልጽ አይደለም ያሉ ሲሆን ይህም ግልጽ መደረግ አለበት ይላሉ።

"ባንዲራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ርዕዮተ ዓለምን፣ ትግልና ስትራቴጂን የሚያንጸባርቅ ነው" የሚሉት አቶ ለሚ አንድ ድርጅት ሲቋቋምም እነዚህን መሠረታዊ የሆኑ የድርጅታዊ አላማዎችን ከያዙ መገለጫዎችም መካከል አርማና ሰንደቅ አላማ አንዱ ነው ብለዋል።

ሆኖም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በአውሮፓውያኑ 2017 ባካሄደው አራተኛው ጠቅላላ ጉባኤ ባንዲራው የአሮሞ ሕዝብ እንዲጠቀምበት ወስኗል።

ባንዲራው ለኦሮሞ ሕዝብ የተሰጠ ነው ካሉ እንዲሁም ኦፌኮ ለኦሮሞ ሕዝብ የሚታገል ፓርቲ እንደመሆኑ ሃሳቡ አይጣረስም ወይ ስንል አቶ ለሚን የጠየቅናቸው ሲሆን እሳቸውም ቅሬታቸው ችግር እንደሌለበት ተናግረዋል።

“አይጣረስም። አንድ ፓርቲ ሲቋቋም መጀመሪያውኑ የራሱ የሆነ አርማና ባንዲራ አለው። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ባንዲራውን የሰጠው ለፓርቲ አይደለም የሰጠው ለሕዝብ ነው። ሕዝብን አትጠቀሙ አንልም፣ ሊልም አይችልም፤ ብሎም አያውቅም” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በርካቶች የኦሮሞ ነጻነት ትግል አርማነት የሚያዩትን አርማና ባንዲራ መጠቀም የተለመደ ቢሆን ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ የገፋፋቸውም የድርጅቱ አባላት በሚጠይቁት ጥያቄ ምክንያት እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የሌላ ፓርቲ አመራር በምን መልኩ መጠቀም አለበት? ድርጅቱ የባንዲራን አጠቃቀም በግልጽ በሕገ ደንቡ ውስጥ ያስቀመጠ ሲሆን፣ የሌሎች ድርጅቶች አመራር ሲጠቀሙ በየትኛው ሕግ ነው የሚታየው የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው ተናገረዋል።

በተጨማሪም ከአባላቶቻቸው የመጡ ግፊቶችና የሁለቱም ድርጅቶች አንድ ላይ የመስራት ሁኔታ ግልጽ ለማድረግ የተጠየቀ ጥያቄ መሆኑንም አበክረው ገልጸዋል።

የኦፌኮ አመራር የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድ ከእስር ከተፈቱ በኋላ በአውሮፓ የተለያዩ ጉዞዎችን እያደረጉ ነው ምናልባት ይህንን ባንዲራ በእነዚያ ክንውኖች ላይ ይዘው መታየታቸው ለዚህ ደብዳቤ መጻፍ ምክንያት ሆኗል ወይ? ስንል ጥያቄ አቅርበንላቸዋል ።

እሳቸውም በምላሹ “መጀመሪያ አመራር ሳይሆኑ እንደ አንድ የኦሮሞ ልሂቅ ይህንን አርማ ወይም ሰንደቅ አላማ ይጠቀማሉ፣ ማንም የሚከለክላቸውም አልነበረም። ጥያቄው ከጉዞው ጋር የተያያዘ አይደለም። ቃለ መጠይቅ በሚያደርጉበት ወቅት በተለያየ አጋጣሚዎች አርማውን ወይም ሰንደቅ አላማውን ይጠቀማሉ። ይሄ ግልጽ ነው" ብለዋል አቶ ለሚ።

ሆኖም መነሻው ከጉዞውም ጋር የተያያዘ አይደለም በማለት ሁለቱ ፓርቲዎች አብረው ሲሰሩ የነበሩና ለወደፊቱም አብረው የሚሰሩ ፓርቲዎች እንደመሆናቸው መጠን ግልጸኝነትና አጠቃቀምን በተመለከተ የተጠየቁበት ነው ይላሉ።

ባንዲራው በባለቤትነት የኦሮሞ ሕዝብ ቢሆንም አጠቃቀሙን በተመለከተ የት፣ እንዴት በምን ሁኔታ መጠቀም እንዳለበት ለአባላቶች ወይም ባሉት ሕጎች ውስጥ እንደተቀመጠም ያስረዳሉ።

“አቶ ጃዋር የሚመሩት የራሳቸው የሆነ ድርጅት አለ። ድርጅቱም የራሱ የሆነ አርማና ባንዲራ አለው ይሄ ግልጽ መሆን አለበት” ይላሉ።

ኦፌኮም ባንዲራውን አላግባብ እየተጠቀሙበት ነው ለሚለው የኦነግ ቅሬታ በቀጥታ ምላሽ ያልሰጠ ሲሆን፣ ሆኖም ደብዳቤውን መቀበሉን አረጋግጧል።

“ደብዳቤውን ፈርሜ የተቀበልኩት እኔ ነኝ። በእዚህ ጉዳይ ላይ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባ ተቀምጦ ወደፊት ይወያይበታል። አሁን ግን እዚህ ላይ የምንለው ነገር የለም” በማለት የኦፌኮ ዋና ፀሐፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በበኩላቸው “እዚህ ጉዳይ ላይ አልተነጋገርንም ወደፊት የምናየው ይሆናል ትልቅ ጉዳይም አይደለም” ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲ አርማን በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 133 መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሌላውን ድርጅት አርማ አመሳስሎ ከመጠቀም አርማ ወይም የምርጫ ምልክት በማመሳሰል መጠቀም መታቀብ እንዳለባቸው ደንግጓል።