ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአማራ ክልል የፀጥታ ተቋማት ባልደረቦች የነበሩትን ጨምሮ በርካቶች መታሰራቸውን የደኅንነት ምክር ቤት አስታወቀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ፣ በአማራ ክልል የፀጥታ ተቋማትን “የከዱ” የተባሉ አባሎችን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ አካላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገለጸ።
ምክር ቤቱ ትላንት ሰኔ 1 ቀን 2014 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ ላይ “ከፀጥታ ተቋማት የከዱ አባላትን የመያዝ፣ በተለያዩ ወንጀሎች የተሳተፉ አካላትን በቁጥጥር ሥር የማዋል” ሥራ መከናወኑ ተገልጿል።
በአማራ ክልል ባለፉት ሳምንታት መንግሥት “የሕግ ማስከበር” በሚል በወሰደው እርምጃ፣ “ተበትነው የፀጥታ ስጋት ሲሆኑ የቆዩ የጦር መሣሪያዎች የመሰብሰብ፣ በሕገ ወጥ ተግባራት ተሰማርተው የነበሩ አክቲቪስቶችን ሥርዓት የማስያዝ” ሥራ መካሄዱንም የደኅንነት ምክር ቤቱ መግለጫ ይጠቁማል።
እነዚህንም “ሕዝቡን ለእፎይታ ያበቁ ተግባሮች” ሲል ምክር ቤቱ ገልጿቸዋል።
የፌደራል መንግሥት እና የአማራ ክልል መንግሥት በአማራ ክልል የጦር መሣሪያን በመመዝገብ የጀመሩት ዘመቻ ኋላ ላይ ከ4000 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉበት እንደሆነ ተገልጿል።
መንግሥት ዘመቻውን “የሕግ ማስከበር” ቢለውም፣ ዘመቻው መንግሥትን የሚተቹ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና ማኅበረሰብ አንቂዎችን እንዲሁም ፋኖ የተባለውን ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ኢላማ ያደረገ ነው ብለው የሚከራከሩም አሉ።
ምክር ቤቱ የፋኖን ታጣቂዎች በስም ባይጠቅስም ከመንግሥት ፀጥታ መዋቅሮች ውጭ ያሉ የታጠቁ አደረጃጀቶች "እንደፈለጉ" ሊሆኑ እንደማይችሉ በመግለጫው አስፍሯል።
“በአገር ውስጥ ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብት ለመንግሥት የተሰጠ መብት ነው። ዜጎች በሰላም ጊዜ አልሚ፣ በጦርነት ጊዜ ተፋላሚ መሆናቸውም ከጥንት የነበረ ነው። ያ ማለት አገር ስትወረር ሁሉም ለአገሩ ተፋላሚ ይሆናል። አገር ሰላም ስትሆን ደግሞ ሁሉም ወደ ሕጋዊ ማዕቀፍ ይገባል ማለት ነው” ብሏል።
ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ ሚያዝያ 14 ቀን 2014 ዓ. ም. ስለ አገር አቀፍ የፀጥታና ደኅንነት ያደረገውን ግምገማ ተከትሎ ባስቀመጠው አቅጣጫ፣ ከአማራ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝም የተወሰዱ እርምጃዎች እንዳሉ በትናንትናው መግለጫ አትቷል።
በመግለጫው መሠረት በኦሮሚያ ክልል “በሺዎች የሚቆጠሩ የሸኔ አባላት ተገድለዋል”።
“የሸኔን ልዩ ልዩ ቡድኖች የመደምሰስ፣ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን የማምከን፣ በጠላት እጅ የነበሩ አካባቢዎችን መልሶ የመቆጣጠር፣ መንግሥታዊ መዋቅሩን የማጥራት” እርምጃዎች እንደተወሰዱ ጠቅሶ፣ እነዚህንም “ውጤታማ” ሲል ገልጿቸዋል።
ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚለው እና መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለው ታጣቂ ቡድን መካከል ውጊያ ሲካሄድ መሰንበቱ አይዘነጋም።
መንግሥት በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ታግዞ በተካሄደው በዚህ ውጊያ ንጹሐን ዜጎች ሰለባ መሆናቸውን የኦሮሚያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ መክሰሳቸው ይታወሳል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ “የታጠቁ ሽፍቶችን ሥርዓት ማስያዝና መደምሰስ” መከናወኑን ጠቅሶ እነዚህን ሥራዎች “አበረታች” ሲል ምክር ቤቱ ገልጿቸዋል።
በክልሉ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያን የመሰብሰብ እንዲሁም ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለሥ ሥራ መሠራቱን አክሏል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ በክልሉ መንግሥትና በተለይም የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) መካከል ዘላቂ ሰላም ለማውረድ የሚደረጉ ጥረቶች በተደጋጋሚ መሰናክል ሲገጥማቸው ቆይቷል።
ከቀናት በፊት በካማሺ ዞን በምትገኘው ምዥጋ ወረዳ በክልሉ ልዩ ኃይሎችና በጉሕዴን ታጣቂዎች መካከል በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ ሳቢያ 19 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
በሌላ በኩል በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች “ሊደረግ ታስቦ የነበረው የአል-ሸባብ እንቅስቃሴ በፀጥታ አካላት ቅንጅት ከሽፏል” ሲል ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ ገልጿል።
በደቡብ እና በጋምቤላ ክልሎች “የታጠቁና የተደራጁ ሽፍቶችን መልክ የማስያዝ እንቅስቃሴ” መከናወኑን ጠቅሶ፣ በተጨማሪም የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመግታትና በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን የመፍታት ሥራ መሠራቱን መግለጫው አትቷል።
ምክር ቤቱ “ዓለም አቀፍ የሚዲያ ትኩረትን ለመሳብ የሚፈልጉ” ያላቸው ቡድኖች በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ የቃጡትን ጥቃት የፀጥታና ደኅንነት መዋቅሩ ማክሸፉን አያይዞ ገልጿል።
መንግሥት በአማራ ክልልና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በተመለከተ ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበር የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም የአገርን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ብቸኛው መፍትሄ ነው ማለቱ ይታወሳል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን ሕገ ወጥነትና የሰላም መደፍረስን መንግሥት እንዲቆጣጠር ሕዝቡ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ነበር ያለው መግለጫው፣ ብሔራዊ የፀጥታ ምክር ቤት አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ መወሰኑን አስታውሷል።
በዚህ መግለጫውም በአጠቃላይ የተጀመረው ሰላምና ጸጥታ የማስፈን እንዲሁም ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አፅንኦት ሰጥቷል።