ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የወረዳ አስተዳዳሪን ጨምሮ 19 ሰዎች ተገደሉ
በቤኒሻንጉል ክልል፣ በካማሺ ዞን በምትገኘው ምዥጋ ወረዳ በክልሉ ልዩ ኃይሎችና በታጣቂዎች መካከል በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ ሳቢያ 19 ሰዎች መሞታቸውን የክልሉ የፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ሀሩን ኡመር ለቢቢሲ ገለጹ።
ባለፈው ሳምንት መጋቢት 24 ቀን 2014 ዓ. ም. የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ታጣቂዎች ጥቃት ሰንዝረው፣ በምላሹ ከልዩ ኃይል ጋር በተደረገው የተኩስ ልውውጥ የምዥጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ መሞታቸውንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ከዋና አስተዳዳሪው ውጪ የሞቱት ሰዎች ተኩስ የከፈተው የታጣቂው ቡድን አባላት እንደሆኑም አቶ ሀሩን ገልጸዋል።
ጥቃቱ በክልሉ በልዩ ኃይል አባላት ላይ መከፈቱን የተናገሩት ኮሚሽነሩ፣ በተደረገው የተኩስ ልውውጥም በርካታ የታጣቂው ቡድን አባላት መገደላቸውን አመልክተዋል።
በክስተቱ ከልዩ ኃይሉ የሞተ የለም ያሉት ኮሚሽነሩ “ታጣቂዎቹ የሚጠቀሙበት መሣሪያ” በቤታቸው የተገኘ የተባሉ ባለሀብትም እንደሞቱ ተናግረዋል።
ግለሰቡ ቤት ውስጥ “ዲሽቃ ጥይቶች፣ 5 ክላሽና ሌላም በርካታ ታጣቂዎች የሚጠቀሙባቸው ሌሎች ነገሮች" መገኘታቸውን ኮሚሽነሩ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በግለሰቡ ቤት የተገኘውን “ለታጣቂዎች የተዘጋጀ መሣሪያ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
የምዥጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ በአጋጣሚ በስፍራው እንደነበር የተናገሩት ኮሚሽነር ሀሩን በተኩስ ልውውጡ ሕይወታቸው እንዳለፈ አመልክተዋል።
የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) በአካባቢው የሚንቀሳቀስ ታጣቂ ቡድን ሲሆን፣ ከክልሉ መንግሥት ጋር ዕርቅ ለመፈፀም ስምምነት ላይ ደርሰው እንደነበር ይታወሳል።
ሆኖም ግን በታጣቂዎቹ እና በክልሉ መንግሥት መካከል በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት መሪዎች አማካይነት ዘላቂ ዕርቅ ለማስፈን የተደረገው ጥረት በተደጋጋሚ መሰናክሎች ሲገጥሙት ተስተውሏል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥትና ታጣቂው ቡድን ከዚህ ቀደም የመግባቢያ ስምምነት ሲፈራረሙ፣ የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ አመራር “ስምምነቱ የንጹህንን ሞት ለመቀነስ ያለመ ነው” ብለው ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
እጃቸውን በሰላም ከሰጡ ታጣቂዎች ጋር የተደረሰው ስምምነት፣ ታጣቂዎቹ ትጥቅ እንዲፈቱ ሲጠይቅ፣ በምላሹ ታጣቂዎቹ የመልካም አስተዳደር እጦት የፈጠራቸው ችግሮች እንዲቀረፉላቸው መጠየቃቸው አይዘነጋም።
“መድልዎ ተፈጽሞብናል” የሚሉት ታጣቂዎቹ፣ በክልሉ የፖለቲካ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን የምጣኔ ሀብት እና ማኅበረሰባዊ ተጠቃሚነታቸውም እንዲረጋገጥ ይጠይቃሉ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ሦስት ዓመታት በተደጋጋሚ በታጣቂዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለመፈናቀል ተዳርገዋል።
ይህንን የታጣቂዎች ጥቃት ለመቆጣጠርም በአብዛኛው የክልሉ አካባቢ ላይ በፌደራል መንግሥት እና በክልሉ ጥምረት የሚመራ ኮማንድ ፖስት ከተቋቋመ የቆየ ቢሆንም አስካሁን በታጣቂዎቹ የሚፈጸመው ጥቃት አልቆመም።