አንድ የሩሲያ ጄነራል ዩክሬን ውስጥ መገደላቸው ተዘገበ

የአንድ ከፍተኛ የሩሲያ ጄነራል ዶምባስ በተባለው አካባቢ በተካሄደ ከባድ ውጊያ መሞታቸውን የአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን አስታወቀ።

ሮሲያ 1 የተባለው የሩሲያ መንግሥት ቴሌቪዥን እንደዘገበው ሜጀር ጄነራል ሮማን ኩቱዞቭ ዩክሬን ውስጥ ሠራዊታቸው ጥቃት እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው የተገደሉት።

ጄነራል ኩትዞቭ እራሷን ከዩክሬን በመገንጠል ዶኔትስክ ሕዝቦች ሪፐብሊክ በማለት ባወጀችው ግዛት ውስጥ ሆነው ሠራዊታቸው የሚያካሂደውን ውጊያ እየመሩ ሳለ መገደላቸው ተነግሯል።

የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ግን ስለጀነራሉ መገደል በወጣው ሪፖርት ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠም።

የዩክሬን ሠራዊት ግን የሩሲያውን ጄነራል መገደል ያረጋገጠ ሲሆን፣ ስለተገደሉበት ሁኔታ ምንም ዓይነት ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።

የጄነራል ኩቱሶቭ መገደል ዜና የተሰማው ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የሩሲያ 29ኛ ሠራዊት አዛዥ የሆኑት ሌትናንት ጄነራል ሮማን ቤርዲኒኮቭ ተገድለዋል የሚል ወሬ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መሰራጨቱን ተከትሎ ነው።

ነገር ግን ቢቢሲ ስለተሰራጨው ወሬ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

የሩሲያ ከፍተኛ የጦር አዛዦች ወደፊት ወደጦር ግንባር በመግባት ሠራዊታቸውን ለመምራት በመገደዳቸው ለጥቃት መጋለጣቸው ይነገራል።

እስካሁን ሩሲያ ሦስት ከፍተኛ ጄነራሎቿ በጦርነቱ መሞታቸውን አረጋግጣለች።

ዩክሬን ግን በጦርነቱ 12 የሩሲያ ጄነራሎችን እንደገደለች ስትገልጽ፣ ምዕራባውያን የስለላ ተቋማት ደግሞ ቢያንስ ሰባት የሩሲያ ከፍተኛ የጦር አዛዦች ተገድለዋል ይላሉ።

ነገር ግን በጦርነቱ ተገደሉ የተባሉትን በርካታ የሩሲያ ጄነራሎችን በተመለከተ ግራ መጋባቶች አሉ። የዩክሬን ኃይሎች ገድለናቸዋል ካሏቸው ጄነራሎች መካከል ሦስቱ በሕይወት እንዳሉ ተዘግቧል።

ባለፈው መጋቢት ወር የዩክሬን ኃይሎች ሜጀር ጄነራል ቪታሊ ጌራሲሞቭ ከአገሪቱ ሁለተኛ ከተማ ኻርኪቭ ወጣ ብሎ መገደላቸውን ገልጸው ነበር። ነገር ግን በግንቦት ወር አጋማሽ ላይ የሩሲያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጄነራሉ ሽልማት እንደተበረከተላቸው በመግለጽ ስለመገደላቸው የወጣውን ሪፖርት ውድቅ አድርጎታል።

በተመሳሳይ ሜጀር ጄነራል ማጎምድ ቱሼቭ በሕይወት እንዳሉ የተነገረ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተሰራጩ ቪዲዮዎች ላይ ታይተዋል።

መጋቢት ወር አጋማሽ ላይ እንዲሁ ዩክሬን ኼርሶን በተባለው አካባቢ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ሌተናንት ጄነራል አንድሬይ ሞርድቪቼቭ ተገድለዋል ብላ ነበር። ነገር ግን በኋላ ላይ ጄነራሉ ከቼቼኑ መሪ ራምዛን ካዲሮቭ ጋር በቪዲዮ በተደረገ ስብሰባ ላይ ታይተዋል።

የቢቢሲ የሩሲያ ቋንቋ አግልግሎትም ጄነራሉ በሕይወት እንዳሉ አረጋግጧል።

የጄነራሎችን ሞት በተመለከተ በሩሲያ ውስጥ ብዙም በይፋ አይነገርም። የሜጀር ጄነራል ቭላድሚር ፍሮሎቭ ሞትን በተመለከተ ምንም ሳይባል ቆይቶ ነው ሚያዝያ ወር ላይ ቀብራቸው ሴንት ፒተርስበርግ ውስጥ ሲፈጸም በሩሲያ መንግሥት ቴሌቪዥን ላይ የተነገረው።

በሰላም ወቅት እንኳን ቢሆን ሩሲያ ወታደራዊ ሞትን በአገር ምስጢርነት ይዛ የምትቆይ ሲሆን፣ በዩክሬን ላይ ወረራ ፈጽማ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ መጋቢት ወር ላይ በጦርነቱ ሞቱብኝ ካለቻቸው 1,351 ወታደሮቿ ውጪ እስካሁን ተጨማሪ መረጃ ይፋ አላደረግችም።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የቅርብ ባለሥልጣን ለአንድ ጋዜጣ እንደተናገሩት የአገራቸው ወታደራዊ የመረጃ መኮንኖች ቡድን የሩሲያ ወታደራዊ መኮንኖች ያሉባቸውን ቦታዎች እንዲለይና ኢላማ እንዲያደርግ መታዘዙን ተናግረው ነበር።

"ከፍተኛ ጄነራሎች፣ ፓይለቶች እና የመድፍ ምድብ አዛዦችን ዋነኛ ትኩረታቸው አድርገዋል” ሲሉ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።

ጨምረውም መኮንኖቹ በአልሞ ተኳሽ ወይም በመድፍ ኢላማ እንደሚደረጉ አስታውቀዋል።