ቤንዚን በሊትር 11 ብር ጨምሮ 48 ብር ገደማ ሊሸጥ ነው

መንግሥት ለነዳጅ የሚያውለውን ድጎማ ሂደት ለማንሳት በያዘው ዕቅድ መሠረት በመጀመሪያው ዙር የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ክለሳ ከፍተኛ ጭማሪ ተደረገ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከነገ ረቡዕ ሰኔ 29/2014 እስከ ሐምሌ 30/2014 ዓ.ም. ድረስ የሚያገለግል አዲስ የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ዝርዝር ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሠረት በሊትር 36 ብር ከ87 ሳንቲም ሲሸጥ የነበረው ቤንዚን፤ 10 ብር ከ96 ሳንቲም ጨማሪ በማሳየት ከነገ ጀምሮ በሊትር 47 ብር ከ83 ሳንቲም ይሸጣል።

ነጭ ናፍጣ ደግሞ ባለፉት ጥቂት ወራት 14 ብር ገደማ ጭማሪ አሳይቷል። ከሚያዚያ 30/2014 ጀምሮ በሊትር 35.43 ብር ሲሸጥ የነበረው ነጭ ናፍጣ በአንድ ግዜ 13.59 ብር ጨምሮ ከነገ ጀምሮ በሊትር 49.02 ብር ለገበያ ይቀርባል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባወጣው የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ክለሳ አስመልክቶ ማከስኞ ምሽት ባወጣው የዋጋ ዝርዝር መሠረት ከነገ ሰኔ 29/2014 ዓ.ም. ጀምሮ ነጭ ናፍጣ 49.02፣ ኬሮሲን 49.02፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 53.10፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ 52.37 እና የአውሮፕላን ነዳጅ 98.83 በሊትር ዋጋ እንደተቆረጠላቸው አስታውቋል፡፡

በአሁኑ በነዳጅ ምርቶች ላይ የተደረገው ጭማሪ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ጭማሪዎች ሁሉ ከፍተኛው ቢሆንም፣ አሁንም መንግሥት ለነዳጅ ምርቶች ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

ምንም እንኳን መንግሥት ለነዳጅ ምርቶች በአጠቃላይ ድጎማ ሲያደርግ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን የታለመለት የነዳጅ ድጎማ በተባለ ሥርዓት አማካይነት ለሕዝብ የትራንስፖርት መገልገያዎች ድጎማ ይደረጋል ተብሏል።

ባለፉት ጥቂት ወራት የኢትዮጵያ መንግሥት በነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ላይ ተከታታይ ጭማሪን አድርጓል።

ለማሳያም ከሚያዝያ 30/2014 ዓ.ም. ጀምሮ በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ በተደረገው ለውጥ ቤንዚን የ15 በመቶ ጭማሪ በማድረግ ከ31.74 ወደ 36.87 ብር ከፍ እንዲል ተደርጎ ነበር።

ለዚህ ከፍተኛ ጭማሪ የሚነሱት ምክንያቶች ደግሞ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ምርት ዋጋ መጨመር እና መንግሥት ለነዳጅ ምርቶች እያደረገ ባለው ድጎማ ምክንያት በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ወጪ ማድረጉ ጫና እየፈጠረበት በመሆኑ ነው።

የነዳጅና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለስልጣን የነዳጅ ስታንዳርድ ጥናት ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ቱሉ እንደሚሉት መንግሥት ለነዳጅ በሚያደርገው ድጎማ ምክንያት በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወጪ ያደርጋል።

በግንቦትና በሰኔ መካከል ባሉ ሰላሳ ቀናት ውስጥ ብቻ መንግሥት 16 ቢሊዮን ብር ወይም 268 ሚሊዮን ዶላር ነዳጅን ለመደጎም ሲል ወጪ ማድረጉን አቶ ለሜሳ ተናግረዋል።

የነዳጅ ምርቶች ዋጋ ላይ ጭማሪ ሲደረግ እንደሚስተዋለው በሌሎች ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በስከተል የኑሮ ውድነቱን ያባብሰዋል የሚል ስጋት በበርካቶች ዘንድ አስከትሏል።