በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ሁለተኛ ዙር ንግግር መጀመሩ ተነገረ

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂ ቡድን መካከል በታንዛኒያ የሁለተኛ ዙር የሰላም ንግግር መጀመሩን ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንዳሉት ጥቂት ቀናትን ባስቆጠረው ድርድር ከሁለቱም ወገኖች የተወጣጡ የጦር አባላት ተወካዮች በተገኙበት ንግግር እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም ራስ ገዝ ግዛት በሆነችው ዛንዚባር የተካሄደውን ድርድር የምሥራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ አሜሪካ፣ ኖርዌይ እና ኬንያ አስተባባሪ እና አሸማጋይ ሚና መውሰዳቸው ይታወሳል።

አሁን የተጀመረውን ንግግር ማን እንደሚያደራድር ግልጽ ባይሆንም፣ ኢጋድ ከዚህ ቀደም የነበረውን ሚና ሳያስቀጥል እንዳልቀረ ተጠቅሷል።

እስካሁን ስለንግግሩ ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የተባለ ነገር የለም።

ከስድስት ወራት በፊት በታንዛኒያ ዛንዚባር በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል የተደረገው የመጀመሪያው ዙር ድርድር ያለውጤት መበተኑ ይታወሳል።

በሰሜናዊ ምሥራቅ ዛንዚባር ሲካሄድ የነበረው የመጀመሪያው ዙር ውይይት ሚያዝያ 25/2015 ዓ.ም. ከተጠናቀቀ በኋላ የፌደራሉ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በተናጠል ባወጡት መግለጫ ለቀናት ሲካሄድ የቆየው ንግግር በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልተቻለ ይፋ አድርገው ነበር።

ይሁን እንጂ የመጀመሪያው ዙር ውይይት ጠቃሚ መሆኑን ሁለቱም አካላት በወቅቱ አስታውቀው ነበር።

በተለይ የፌደራሉ መንግሥት ከመጀመሪያው ዙር ንግግር ማብቃት በኋላ ባወጣው መግለጫ ውይይቱ በአመዛኙ ገንቢ መሆኑን ጠቅሶ ነበር።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ውይይቱ መጠናቀቁን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፣ ቁልፍ ብሎ በጠራቸው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መደረስ አለመቻሉን አመልክቶ ነበር።

የመጀሪያው ዙር ንግግር ውጤት አልባ ሆኖ የተበተነበትን ምክንያት ሁለቱም አካላት በይፋ ባይገልጹም፣ ቢቢሲ ከተሳታፊዎቹ መካከል እንደተረዳው ሁለቱን አካላት ካላስማሙ ጉዳዮች መካከል አንዱ የጋራ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ነው።

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱትን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን እና ብልጽግናን ጨምሮ ሌሎች ፓለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ የጋራ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መጠየቁን ቢቢሲ ከተሳታፊዎች አረጋግጦ ነበር።

ይህን የጋራ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ጥያቄ በፌደራል መንግሥቱ ተደራዳሪዎች በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

ኬንያ እና ኖርዌይ በአሸማጋይነት በተሰየሙበት የመጀመሪያ ዙር ውይይት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከኢትዮጵያ ውጭ በሄዱ ስድስት ልዑካን እንዲሁም በደቡብ ኦሮሚያ ከሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሁለት አባላት ተወክሎ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥትን በመወከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዴዎን ጤሞቴዎስ ተደራዳሪ ሆነው መቅረባቸውንም ቢቢሲ ከምንጮቹ መረጃ አግኝቶ ነበር።