ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ያላስማማው የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ጉዳይ መሆኑ ተነገረ
በፌደራሉ መንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ሲካሄድ በነበረው የዛንዚባር ንግግር ሁለቱን አካላት ካላስማሙ ጉዳዮች መካከል አንዱ የጋራ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ መሆኑን ተሳታፊዎች ተናገሩ።
በሰሜናዊ ምሥራቅ ዛንዚባር ሙዪኒ የባሕር ዳርቻ በመንግሥት እና በአማጺው ቡድን መካከል ለመጀሪያ ጊዜ ለዘጠኝ ቀናት ያህል የተካሄደው ውይይት ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 25/ 2015 ዓ.ም ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ሁለቱም ወገኖች አሳውቀዋል።
ተደራዳሪዎቹን ካላስማሟቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የጋራ የሽግግር መንግሥት መቋቋም እንደሆነ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የንግግሩ ተሳታፊዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱትን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን እና ብልጽግናን ጨምሮ ሌሎች ፓለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ የጋራ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መጠየቁን ቢቢሲ ከተሳታፊዎች አረጋግጧል።
የጋራ የሽግግር መንግሥት ምሥረታው በፌደራል መንግሥቱ ተደራዳሪዎች በኩል ተቀባይነት አለማግኘቱንም እነዚህ የቢቢሲ ምንጮች በዛንዚባር ለሚገኙት የቢቢሲ ጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ተሳታፊዎቹ እንደገለጹት የሽግግር መንግሥት በዋነኝነት የሚቋቋመው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መተማመን እንዲኖር እና አገሪቱ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ እንድትችል የማሻገር ኃላፊነትን እንዲወጣ ለማድረግ መሆኑ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ በዛሬው ዕለት በመጀመሪያው ዙር በነበረው ንግግር በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልተቻለ ጠቅሶ፣ ውይይቱ በአመዛኙ ገንቢ መሆኑንም አስታውቋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ውይይቱ መጠናቀቁን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፣ ቁልፍ ብሎ በጠራቸው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መደረስ አለመቻሉን አመልክቷል።
በዚህ በመጀመሪያው ዙር ውይይት ላይ ከተነሱ ሃሳቦች ሌላኛው በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ሊደረስ የሚገባው ስምምነት በዘላቂነት ጦርነት በሚያከትም መልኩ፣ እንዲሁም ሁሉንም የሠራዊቱን ፖለቲካዊ እና የጦር ክንፉን ማካተት አለበት ተብሏል።
ኬንያ እና ኖርዌይ በአሸማጋይነት በተሰየሙበት በዚህ የመጀመሪያ ውይይት ላይ ከደቡብ ኦሮሚያ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት መካከል ሁለት ተወካዮች በዚህ ውይይት እንዲሳተፉ መደረጉንም በዛንዚባር የሚገኙ የቢቢሲ ጋዜጠኞች አረጋግጠዋል።
በዚህ ውይይት ላይ የተገኙት ስድስት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተወካዮች ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ልዑካን ሲሆኑ፣ ሁለቱ የሠራዊቱ አባላት በአሸማጋዮቹ በኩል እንዲሳተፉ መደረጉን እና በአጠቃላይም ቡድኑ በስምንት ተወካዮች መወከሉን ቢቢሲ ሰምቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥትን በመወከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዴዎን ጤሞቴዎስ ተደራዳሪ ሆነው መቅረባቸውንም ቢቢሲ ከምንጮቹ መረጃ አግኝቷል።
ሁለቱ ልዑካን በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተዛምቶ ለበርካቶች እልቂት የሆነውን ጦርነት እልባት ለማግኘት የፌደራሉን መንግሥት ወክለው ከህወሓት ጋር የተደራደሩት ልዑካን አባል መሆናቸው ይታወሳል።
በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኩል ደግሞ የታሪክ ምሁሩና በጆርጂያ ስቴት ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን፣ ከኦነግ መስራቾች አንዱና ለበርካታ ዓመታት አመራር የነበሩት ጣሃ አብዲ እንዲሁም የጦሩ አዛዥ ዋና አማካሪ የሆኑት ጂሬኛ ጉደታ ይገኙበታል።
በኦሮሚያ ክልል ለዓመታት የዘለቀውና ለበርካታ ሰዎች ሞት እና መፈናቀል ምክንያት የሆነውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በፌደራሉ መንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል የመጀመሪያ ዙር ውይይት የተጠናቀቀ ሲሆን ቀጣይ ዙር መቼ ሊካሄድ እንደሚችል አልተገለጸም።
በዚህ የመጀመሪያ ውይይት የተነሱ ጉዳዮች ዝርዝር ባይጠቀሱም፣ ግጭቱን በዘላቂነት እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል የሰላም ውይይቱን መቀጠል አስፈላጊ ስለመሆኑ መግባባት ላይ መደረሱን ተገልጿል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ለግጭቱ ፖለቲካዊ እልባት ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት ገልጿል።
መንግሥት በበኩሉ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እና እስካሁን ሲከተለው በነበሩ መሠረታዊ መርሖች አማካይነት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግሥት የጸና አቋም አለውም ብሏል።
በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል በቀጣይ የሚካሄደው ንግግር የት እና መቼ ሊሆን እንደሚችል አስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
የሁለቱን አካላት ስድስት-ስድስት ልዑካን እና አሸማጋዮችን የያዘው ይህ ውይይት ማክሰኞ ሚያዝያ 17/ 2015 ዓ.ም. በታንዛኒያ ራስ ገዝ አስተዳደር በሆነችው ዛንዚባር ተጀምሮ በሳምንቱ መጨረሻ ይጠናቀቃል የሚል ዕቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን ለተጨማሪ ቀናት ተራዝሞ በዛሬው ዕለት ተጠናቋል።
ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ተለይቶ የወጣው እና መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ባለፉት ዓመታት በአራቱ የወለጋ ዞኖች፣ በምዕራብ ሸዋ እና ደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተቀዳሚው ዓላማ የኦሮሞ ሕዝብ የራሱን መብት በራሱ እንዲወስን እና ዲሞክራሲ፣ ፍትህ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲመለስ እታገለላለሁ የሚል ድርጅት እንደሆነ ይገልጻል።