አሜሪካ የፍልስጤም ባለሥልጣናትን ቪዛ ልትከለክል ነው

አሜሪካ በፍልስጤም አስተዳደር ባለሥልጣናት እና ፍልስጤማውያንን በዓለም አቀፍ መድረክ በሚወክለው አካል ላይ ማዕቀብ ልትጥል መሆኗን አስታወቀች።

ማዕቀቡ በኦስሎ የሰላም ስምምነት የተቋቋመውን የፍልስጤማ አስተዳደር (ፒኤ) እና በተመሳሳይ ሂደት ለእስራኤል እውቅና በመስጠት እና አመጽን በመቃወም እውቅና ያገኘውን የፍልስጤም ሕዝብ ይፋዊ ተወካይ የፍልስጤም ነጻነት ድርጅት (ፒኤልኦ) ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለፒኤልኦ አባላት እና ለፒኤ ባለሥልጣናት ቪዛ እንደሚከለክል ይፋ አድርጓል።

መግለጫው የወጣበት ጊዜ እና የተጻፈበት ቋንቋ የሚጠቁመው የትራምፕ አስተዳደር በዚህ ሳምንት በተባበሩት መንግሥታት በፈረንሳይ እና በሳዑዲ መሪነት ለወደፊት የሁለት አገራት ምሥረታን አጀንዳ ለመደገፍ ለተካሄደው ጉባዔ የተሰጠ ምላሽ መሆኑን ነው።

በቅርቡ ሳዑዲ አረቢያ እና ፈረንሳይ ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን ለፍልስጤም-እስራኤል ግጭት እልባት ለማበጀት በሚል የሁለት አገራት ምሥረታን አጀንዳ ያደረገ ከፍተኛ ጉባኤ በተባበሩት መንግሥታት መርተው ነበር። ጉባኤው በዋነኝነት ያለመው የፍልስጤምን አገርነት መሠረት መጣል ላይ ነበር።

ስብሰባው የተካሄደው ፈረንሳይ፣ዩናይትድ ኪንግደም እና ካናዳ ነጻ፣ ከወታደራዊ ኃይል ነፃ ለሆነች ፍልስጤም በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ እውቅና ለመስጠት በአንዳንድ ሁኔታዎች የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጠው ዝግጁ መሆናቸውን ከገለፁ በኋላ ነው።

አሜሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኮንፈረንስ ላይ የተሳተፉትን "ፀረ እስራኤል" መግለጫ ካወጡ ዲፕሎማሲያዊ መዘዝ እንደሚያስከትል በግል በማስጠንቀቅ ጉባዔውን ውድቅ አድርጋለች።

የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በዚህ መግለጫው ላእ የፍልስጤም አስተዳደር (ፒኤ) እና የፍልስጤም ነጻ አውጪ ድርጅት (ፒኤልኦ) "ከእስራኤል ጋር ያለውን ግጭት እንደ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) እና ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት (ICJ) ያሉ ዓለም አቀፍ አካላትን ለማሳተፍ እየሞከሩ ነው" ሲል ይኮንናል።

በተጨማሪም መግለጫው ፒኤልኦ እና ፒኤ "አመፅን ማነሳሳት እና ማሞካሸትን ጨምሮ ሽብርተኝነትን መደገፍን (በተለይም በመማሪያ መጽሐፍት ውስጥ) እና ለፍልስጤም አሸባሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ሽብርተኝነትን በመደገፍ ክፍያዎችን እና ጥቅማ ጥቅሞችን መስጠት ቀጥለዋል" ሲል በአሜሪካ እና በእስራኤል በተከታታይ ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ጠቅሷል።

የትራምፕ አስተዳደር በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ ፍልስጤማውያንን በገደሉ አመፀኛ የእስራኤል ሰፋሪዎች ላይ ጥሎ የነበረውን ማዕቀብ አንስቷል።

አንድ ታዋቂ የፍልስጤም ፖለቲከኛ አሜሪካ ማዕቀቡን የጣለችው ለፍልስጤም እውቅና የሚሰጡ አገራት ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ "በቀል" ነው ብለዋል።

የፍልስጤም አስተዳደር ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ ተመሳሳይ ስሜት አንፀባርቋል።

"እነዚህ ዘመቻዎች ተባብሰው የቀጠሉት የፍልስጤም ዲፕሎማሲ ጉልህ እና ተከታታይ ድሎችን ተከትለው ነው" ብሏል።

"በተለይ በቅርቡ ቁልፍ አገራት ለፍልስጤም አገርነት እውቅና ለመስጠት መወሰናቸው፣ በኒውዮርክ የተሳካው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ እና እርሱን ተከትሎ የወጣው ታሪካዊ መግለጫ ናቸው"

የፒኤልኦ አካል የሆነው ፓሊስቲኒያን ናሽናል ኢኒሼቲቭ (PNI) መስራች ሙስጠፋ ባርጋውቲ አሜሪካ ዒላማ ያደረገችው የተሳሳተ ጎራ ነው ብለዋል።

ባርጋውቲ ለቢቢሲ "የትራምፕ አስተዳደር በጋዛ እና ዌስት ባንክ የጦር ወንጀል የሚፈጽሙ ወንጀለኞችን፣ እስራኤልን፣ከመቅጣት ይልቅ… ተጎጂውን ማለትም የፍልስጤም ሕዝብ እየቀጡ ነው" ብለዋል።

እስራኤል ማዕቀቡን ተቀብላ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ስለወሰዱት እርምጃ አመስግናለች።

"ይህ (የፕሬዚዳንት ትራምፕ) እና አስተዳደሩ የወሰዱት ጠቃሚ እርምጃ ለሽብር እና ጠብ አጫሪነት የሚያደርጉት ድጋፍ ላይ ዓይናቸውን ጨፍነው ለፍልስጤም ምናባዊ አገር እውቅና ለመስጠት የተሯሯጡ አንዳንድ አገራት የሞራል መዛባትን ያጋልጣል" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳአር ተናግረዋል።

የፍልስጤም አስተዳደር (ፒኤ) ሁል ጊዜ ለሽብርተኞች "ክፍያ ይፈጽማል" በሚል የሚቀርብበትን ውንጀላ ውድቅ ያደርጋል።

አስተዳደሩ ገንዘብ የሚከፈለው በእስራኤል ወታደራዊ ቁጥጥር ስር ለሚገኙ ፍልስጤማውያን እስረኞች ቤተሰቦች ድጎማ መሆኑን በማከል ብዙዎቹ እነዚህ እስረኞች ምንም ዓይነት የፍትህ ሂደት ያልተጀመረላቸው እና አራተኛውን የጄኔቫ ስምምነትን በመጣስ በቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው ይላል።

ፍልስጤማውያን በእስራኤል በቁጥጥር ስር የዋሉትን እና በወታደራዊ ፍርድ ቤቶቿ ታስረው 99 በመቶ የቅጣት ፍርድ የሚጣልባቸውን ዜጎች የሚመለከቷቸው እንደ የፖለቲካ እስረኛ ነው።

የፈረንሳይ ባለስልጣናት ባለፈው ሳምንት አገራቸው ለፍልስጤም እውቅና ለመስጠት ያላትን ቁርጠኝነት ተከትሎ አስተዳደሩ እነዚህን ክፍያዎች ለማቆም ፈቃደኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ሳምንት በተካሄደው የተመድ ጉባኤ አሜሪካ እስራኤል በጋዛ ላይ ለምታካሄደው ጦርነት የምታደርገውን ድጋፍ በርካታ አገራት ተችተዋል።

ጉባዔው በእስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን መካከል ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት የምትመራው ዋሽንግተን ሚናዋን እየተጫወተች እንዳልሆነ አጋልጧል።

በፍልስጤም ባለስልጣናት ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ ከተሟላ የፋይናንስ ማዕቀብ ጋር ሲነጻጸር ትንሽ እርምጃ ሊሆን ይችላል።

ከዚህ ቀደምም ቢሆን የፒኤ እና ፒኤልኦ ባለስልጣናት ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ሲፈልጉ ቪዛ ለማግኘት ረዥም እና ውስብስብ ሂደትን ማለፍ ይጠበቅባቸው ነበር፤ ይህም ብዙ ጊዜ የማይገኘውን ልዩ ይለፍን ማግኘት ያካትታል።

እርምጃው በኒውዮርክ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፍልስጤም ተልእኮ ውስጥ የሚሰሩትን ባለስልጣናት ይነካ እንደሆነ እስካሁን ግልፅ አይደለም።

በተባበሩት መንግሥታት የወቅቱ የፍልስጤም አምባሳደር እና ምክትላቸው ሁለቱም የአሜሪካ ዜግነት አላቸው።