ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመስከረም 11 ጥቃት 'ዋነኛ አቀናባሪን' የጥፋተኝነት ምስክርነት አሜሪካ ለምን ማስቆም ፈለገች?
በሃያ ዓመታት በፊት በአሜሪካ የተፈጸመው የመስከረም 11 የሽብር ጥቃት ዋነኛ አቀናባሪ የተባለው ግለሰብ ባለፈው አርብ ጥር 2/2017 ዓ.ም. የጥፋተኝነት ምስክርነት ለመስጠት የተያዘው ቀጠሮ እንዲራዘም ተደርጓል።
ካሊድ ሼክ መሐመድ ባለፈው ዓመት የደረሰውን ስምምነት ተከትሎ በጥፋተኝነት ሊመሰክር የነበረ ቢሆንም የአሜሪካ መንግሥት ለፌደራል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት አቤቱታውን ማስገባቱን ተከትሎ እግድ ተጥሏል።
ካሊድ ሼክ መሐመድ እና ሌሎች ሁለት ተከሳሾች የሞት እንዳይፈረድባቸው በምትኩ የተከሰሱባቸውን ወንጀሎች በሙሉ አምነው ለመቀበል ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።
ካሊድ ሼክ መሐመድ ወይም በቅጽል ስሙ ኬኤስኤም በኩባ በሚገኘው የአሜሪካ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር ጓንታኖሞ ቤይ የጦር ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ምስክርነቱን ሊሰጥ ነበር። ካሊድ በጓንታናሞ ቤይ በሚገኘው ወታደራዊ እስር ቤት ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል እየማቀቀ ይገኛል።
ነገር ግን የፌደራል ይግባኝ ሰሚ ችሎት ከመንግሥት የቀረበለትን አቤቱታ በመቀበል የመሐመድን እና የሁለት ተከሳሾች የፍርድ ሂደት እንዲቋረጥ ውሳኔ አስተላልፏል።
የአሜሪካ መንግሥት የተከሳሾቹ የጥፋተኝነት ምስክርነታቸው ተቀባይነት ካገኘ መንግሥትም ሆነ የአሜሪካ ሕዝብ ሊጠገን የማይችል ጉዳት እንደሚደርስባቸው በመከራከር ነው ችሎቱ እንዲቋረጥ የጠየቀው።
በሦስት ዳኞች የሚመራው ችሎት መዘግየት "በምንም መልኩ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ተደርጎ መወሰድ የለበትም" ሲሉ አሳስበው፤ ጉዳዩን ለማጤን እና በተፋጠነ ሁኔታ ክርክሮችን ለፍርድ ቤቱ ለማስማት ጊዜ ይሰጠዋል በሚል ውሳኔያቸውን አስተላልፈዋል።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ መዘግየት ማለት ሥልጣኑን ከቀናት በኋላ በሚረከበው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወቅት የሚታይ ይሆናል ማለት ነው።
ያለፈው ሳምንት ችሎት ውሳኔ ምን ነበር?
አርብ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት በነበረው ችሎት ላይ መሐመድ በአውሮፓውያኑ መስከረም 11/2001 ለተፈጸመው የሽብር ጥቃት የጥፋተኝነት ምስክርነቱን ሊሰጥ ነበር።
ጥቃት አድራሾች የጠለፏቸው የመንገደኞች አውሮፕላኖች በኒው ዮርክ የዓለም የንግድ ማዕከል እና ከዋሺንግተን ወጣ ብሎ በሚገኘው ፔንታገን ላይ ተከስክሰው 3 ሺህ ያህል ሰዎች ሞተዋል። ሌላኛው አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ መንገደኞች ከጠላፊዎቹ ጋር በመታገላቸው በፔንስልቫንያ ሜዳ ላይ ተከስክሷል። መሐመድ 2,976 ተጎጂዎችን በመግደል እና በማሴር ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል።
ከዚህ ቀደም የ9/11ን ዘመቻ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ያቀናበረው እሱ እንደነበር ተናግሮ ነበር። አብራሪዎች የንግድ አውሮፕላኖችን ከህንጻዎች ጋር እንዲያጋጩ የማሠልጠን ሃሳብን ጨምሮ ዕቅዶቹን በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ አል ቃኢዳን ይመራ ለነበረው ኦሳማ ቢን ላደን ማቅረቡን ገልጿል።
ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ችሎት ሊሰየም የነበረው በጓንታናሞ ቤይ በሚገኝ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ነበር።
የፍርድ ሂደቱ ከ23 ዓመታት በኋላ ለምን ይካሄዳል?
በባሕር ኃይሉ የጦር ሰፈር ወታደራዊ ፍርድ ቤት የተካሄዱ ቅድመ ችሎቶች ለአስር ዓመት ያህል ቆይተዋል። በዚህ ወቅትም ሦስቱ ግለሰቦች ጥፋተኛ ነን ብለው ያመኑት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በሲአይኤ ለረጅም ጊዜ ከተፈጸመባቸው የከፋ ማሰቃየት በኋላ ነው የሚሉ ክርክሮች ተሰምተዋል።
በአውሮፓውያኑ 2003 በፓኪስታን በቁጥጥር ስር የዋለው መሐመድ 'ብላክ ሳይትስ' በሚሰኙት ምሥጢራዊ የሲአይኤ እስር ቤቶች ለሦስት ዓመታት ያህል ቆይቷል።
በዚህም ወቅት 183 ጊዜ ያህል በውሃ እንዲሰጥም እና እንዲታፈን የማድረግ ስቃይ ተፈጽሞበታል። እሱን ጨምሮ ሌሎች ደግሞ እርቃናቸውን ማጋለጥ ጨምሮ፣ እንቅልፍ ማሳጣት እንዲሁም ሌሎች "የረቀቁ የምርመራ ዘዴዎች" ተፈጽሞባቸዋል ተብሏል።
የጓንታናሞን አሰቃቂነት The Least Worst Place: How Guantanamo Became the World's Most Notorious Prison በሚል መጽሐፍ ያሳተሙት ካረን ግሪንበርግ በታሳሪዎቹ ላይ በተፈጸመው ማሰቃየት ምክንያት "እነዚህን ጉዳዮች የአሜሪካን የሕግ የበላይነት ባከበረ መልኩ ለፍርድ ለማቅረብ ፈጽሞ የማይቻል አድርጓቸዋል" ይላሉ።
"በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በማሰቃየት የተገኙ ማስረጃዎችን ሳይጠቀሙ መረጃዎችን ማቅረብ አልተቻለም። ከዚህም በላይ እነዚህ ግለሰቦች መሰቃየታቸው ክሱን ውስብስብ ያደርገዋል" ሲሉ ያስረዳሉ።
በተጨማሪም ጉዳዩ በወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ስር የሚወድቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከተለመደው የአሜሪካ ወንጀል ፍትህ ሥርዓት ለየት ባለ ሁኔታ ሂደቱን አዘግይቶታል።
መሐመድ ጥፋተኝነቱን ለማመን ስምምነት ላይ የደረሰው ባለፈው ዓመት ሲሆን፣ ይህም የሁለት ዓመት ድርድርን ተከትሎ ነው።
ስምምነቱ ምንን አካቷል?
ከመሐመድ እና ከሁለቱ ተከሳሾች ጋር የተደረሰው ስምምነት ዝርዝር መረጃዎች ይፋ አልሆኑም።
ነገር ግን ተከሳሾቹ ጥፋተኝነታቸውን ሲያምኑ በምትኩ የሞት ፍርድ ይቀርላቸዋል።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በዋለው ችሎት የመሐመድ የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ደንበኛቸው በሁሉም ክሶች ጥፋተኝነቱን ለማመን መስማማቱን አረጋግጠዋል። ስምምነቱ ከጸና እና የመሐመድ የጥፋተኝነት ምስክርነት በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት ካገኘ የሚቀጥለው እርምጃ ውሳኔ ለማስተላለፍ ወታደራዊ ዳኞችን (ሚሊታሪ ጁሪ) መሾም ነበር።
ይህ ሕዝባዊ ችሎት ዓይነት እንደሆነ በጠበቆች በተገለጸው በዚህ ችሎት ቤተሰቦቻቸውን በጥቃቱ ያጡ ግለሰቦች እና የተረፉ ጉዳተኞች ምስክርነታቸውን እንደሚሰጡም ተነግሮ ነበር።
በስምምነቱ መሠረት እነዚህ ቤተሰቦች ለመሐመድ ጥያቄያቸውን ማቅረብ ይችላሉ። መሐመድም ለእነዚህ ጥያቄዎች "በሙሉ እና እውነት በተሞላበት መልኩ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባውም" ጠበቆች ተናግረው ነበር።
ሌላኛው የስምምነቱ ማዕከል የነበረው ጉዳይ ተከሳሹ በጥቃቱ ላይ የነበረውን ተሳትፎ ዝርዝር መረጃዎች ለመስጠት መስመማቱ እንደሆነ ዐቃቤ ሕግ ክሌይተን ጂ ትሪቬት ጁኒየር ረቡዕ ዕለት በነበረው ችሎት ላይ ተናግረው ነበር።
ምንም እንኳን የመሐመድ የጥፋተኝነት ምስክርነቱን ለችሎቱ ሰጥቶ የነበረ ቢሆን እንኳን የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በርካታ ወራት ሊፈጅ ይችል ነበር።
የአሜሪካ መንግሥት ለምን ስምምነቱን ማገድ ፈለገ?
ስምምነቱን የፈረሙትን ከፍተኛ ባለሥልጣን የሾሙት የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ናቸው። ነገር ግን ስምምነቱ በተደረሰበት ወቅት ጉዞ ላይ ስለነበሩ እንዳስደነገጣቸው ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
ከቀናት በኋላ ሎይድ "እንዲህ ያለው ውሳኔ እንደ የበላይ ባለሥልጣነቴ በእኔ ሊፈጸም ይገባል" ሲሉ ስምምነቱን ለመሻር ሞከሩ።
ነገር ግን ሁለቱም ወታደራዊ ዳኞች እና የወታደራዊ ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ስምምነቱ ትክክለኛ እንደሆነ እና ሚኒስትሩ የወሰዱት እርምጃ የዘገየ ነው ሲሉ ወስነዋል።
በተጨማሪም መንግሥት ስምምነቱን ለማገድ የፌደራል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቋል።
መንግሥት ለፍርድ ቤቱ ባስገባው አቤቱታ መሠረት መሐመድ እና ሌሎቹ ሁለት ግለሰቦች "በዘመናዊ የአሜሪካ ታሪክ እጅግ ዘግናኝ የሆነ የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል" በማለት ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ መንግሥትን እና የአሜሪካንን ሕዝባዊ ችሎት የሚነጥቅ እንዲሁም የሞት ቅጣትን የሚያስቀር ነው ብሏል።
የተጎጂ ቤተሰቦች ምን አሉ?
በ9/11 ጥቃት ቤተሰቦቻቸውን ያጡ አንዳንድ ግለሰቦች ስምምነቱን ለጥቃት አድራሾቹ ምህረትን ያሳየ ወይም ግልጽነት የጎደለው ነው ሲሉ የተቹት አልታጡም።
ባለቤቷ በዚህ ጥቃት የተገደላበት ቴሪ ስትራዳ የተባለች ግለሰብ ስምምነቱን "በጓንታናሞ ቤይ ለታሰሩ ሰዎች የፈለጉትን የሚሰጥ ነው" ብላዋለች።
በተጨማሪም "ይህ ድል የካሊድ ሼክ መሐመድ እና የሁለቱ ተከሳሾች ነው። ለእነሱ ድል ነው" ስትል ተናግራለች።
ሌሎች ደግሞ ውስብስብ እና ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረውን የፍርድ ሂደት መቋጫ አድርገው ቆጥረው በአሁኑ ወቅት መንግሥት ጣልቃ በመግባቱ አሳዝኗቸዋል።
ታናሽ ወንድሙ በጥቃቱ የተገደለበት እና በጓንታናሞ ቤይ የፍርድ ሂደቱን ሊከታተል አቅንቶ የነበረው ስቴፈን ዤራርድት "የባይደን አስተዳደር የመጨረሻ ግብ ምንድን ነው? እዚያው እስር ቤቱ ቆይተው ጉዳዩን ወደ ቀጣዩ አስተዳደር ማንከባለል? እስከ መቼ ድረስ? ለምን ይህንን ሂደት ማራዘም አስፈለገ?" ሲል ይጠይቃል።
ስምምነቱ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ ተጎጂዎች "ድል" ሳይሆን ለረጅም ጊዜ የቆየውን የፍርድ ሂደት ለመቋጨት እና በተከሳሾቹም ላይ የፍርድ ሂደትን የሚሰጥ ነው ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።
የችሎቱን መራዘም በጓንታናሞ ቤይ ሆነው የሰሙ ቤተሰቦች "የመዳን ወቅት ሊሆን ይገባ ነበር። አሁን አውሮፕላን የምንሳፈረው በከፍተኛ ህመም ውስጥ ሆነን ነው። ምንም መቋጫ የሌለው ጉዳይ ነው" ሲል አንደኛው ተደምጧል።
የፍርድ ሂደቱ በጓንታናሞ ቤይ ለምን ይታያል?
መሃመድ በጓንታናሞ ቤይ እስር ቤት ከአውሮፓውያኑ 2006 ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል።
እስር ቤቱ የተጀመረው ከ9/11 ጥቃት ከአንድ ዓመት በኋላ፣ ከ23 ዓመታት በፊት አሜሪካ "በሽብር ላይ ጦርነት" ያለችውን ዘመቻ ተከትሎ ነው። በዚህም የሽብር ተጠርጣሪዎች ታስረው ይገኛሉ።
እዚህ ከታሰሩት አብዛኛዎቹ ክስ ያልተመሰረተባቸው ሲሆን ግለሰቦቹም በደረሰባቸው እንግልት እና መሰቃየትን አስመልክቶ የተባበሩት መንግሥታት እና የመብት ድርጅቶች ትችታቸውን ሰንዝረዋል።
በርካታዎቹ በአሁኑ ወቅት ወደ አገራቸው ተመልሰዋል ወይም በሌሎች አገራት ሰፍረዋል።
በአሁኑ ወቅት በታሪኩ ውስጥ ትንሹ የሆነውን 15 እስረኞችን ይዟል። ከስድስቱ በስተቀር ሁሉም በጦር ወንጀሎች የተከሰሱ ወይም የተፈረደባቸው ናቸው።