ትራምፕ በዋሽንግተን ወንጀልን ለመቀነስ የብሔራዊ ዘብ ወታደሮችን አሰማሩ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የብሔራዊ ዘብ ወታደሮችን በዋና ከተማዋ ዋሽንግተን ዲሲ ለማሰማራት እና የከተማዋን ፖሊስ በመቆጣጠር ወንጀልን እና ቤት አልባነትን ለመቆጣጠር ቃል ገቡ።

ትራምፕ ሰኞ ዕለት "የሕዝብ ደኅንነት አደጋ"ን በማወጅ በሳምንቱ መገባደጃ የተመደቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፌደራል ሕጎ አስከባሪዎችን የሚያግዙ 800 የብሔራዊ ዘብ ሠራዊቶችን እንደሚያሰማሩ ገልፀዋል።

"ሁኔታው ሙሉ ለሙሉ ሕግ አልባ እየሆነ ነው" ሲሉ በዋይት ሐውስ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የዋሽንግተን ከተማ ከንቲባ ሙሪል ቦውሰር ፕሬዝዳንቱ ስለ ከተማዋ ወንጀል ያቀረቡትን ክስ ውድቅ አድርገዋል።

እ.አ.አ በ2023 በከተማዋ ወንጀል ከፍ ብሎ የነበረ ቢሆንም መረጃዎች በቀጣይ ዓመታት መቀነሳቸውን ያሳያሉ።

በከተማዋ ከባድ ወንጀሎች በ30 ዓመታት ውስጥ ዝቅተኛው ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

"የአገራችንን መዲና ከወንጀል ነፃ ለማውጣት የምንወስደውን ታሪካዊ እርምጃ እያሳወቅኩ ነው" ሲሉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የተናገሩት ትራምፕ ከተማዋ በፌደራል ቁጥጥር ስር ስትሆን ፖሊስን ከሚመሩት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ፓም ቦንዲ ጋር ነበሩ።

"ይህ ለዲሲ የነፃነት ቀን ነው፤ እናም ዋና ከተማችንን መልሰን እንወስዳለን" ብለዋል።

ትራምፕ ዋሽንግተን ዲሲ "በአመፀኛ ወንበዴዎች እና በደም መጣጭ ወንጀለኞች ተወስዳለች" ከማለት በተጨማሪም "በዕፅ ባበዱ እና ቤት አልባ የሆኑ ሰዎች" ነጥቀዋታል ብለዋል።

ከከተማዋ ፖሊስ በተገኘ መረጃ እ.አ.አ በ2023 እና 2024 ግድያ በ32 በመቶ የቀነሰ ሲሆን ይህም ከ2019 በኋላ ዝቅተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።

በዚህ ዓመት ደግሞ በተጨማሪ ጉልህ የተባለ የ12 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን መረጃው ያመለክታል።

ዲሞክራት የሆኑት ከንቲባ ቦውሰር በ2023 "አስፈሪ" ሲሉ የገለፁት የአገሪቱን ሁኔታ ተከትሎ ወንጀል ከፍ ብሎ እንደነበር በመግለፅ ከተማዋ የወንጀል መናኸሪያ ሆናለች የሚለውን ክስ አስተባብለዋል።

"የወንጀል ጭማሪ እያስተናገድን አይደለም" ሲሉ እሁድ ዕለት ለኤምኤስኤንቢሲ የተናገሩት ከንቲባዋ፤ "ፕሬዝዳንቱ ጥረታችንን ጠንቅቀው ያውቃሉ" ብለዋል።

የዋይት ሐውስ ምክትል ኃላፊ ስቴፈን ሚለር ዋሽንግተን ከባግዳድ የበለጠ ነውጠኛ ከተማ ናትሲሉ ስለሰጡት አስተያየት የተጠየቁት ከንቲባዋ "በጦርነት ከደቀቀ አገር ጋር ማነፃፀር ግነት እና ውሸት ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በከተማዋ ከሚሰማሩት 800 የብሔራዊ ዘብ ሠራዊቶች ውስጥ ከ100 እስከ 200 የሚሆኑት ሕግ አስከባሪዎችን ለመደገፍ በማንኛውም ጊዜ እንደሚሰማሩ የአገሪቱ ጦር በመግለጫው ገልጿል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት ሠራዊቶቹ በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ከተማዋ እንደሚገቡ ተናግረዋል።

ከብሔራዊ ዘብ መሰማራት ባለፈ ትራምፕ የከተማዋን ፖሊስ ክፍል በፕሬዝዳንት ኒክሰን ዘመን ከንቲባ እና የምክር ቤት አባላትን ለመምረጥ በወጣ ሕግ መሠረት በቀጥታ በፌደራል መንግሥት ቁጥጥር ስር እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከ48 ሰዓታት በላይ ፖሊስን መቆጣጠር ከፈለጉ ለኮንግረሱ በጽሑፍ ማሳወቅ የሚኖርባቸው ሲሆን፤ ይህን ፈቃድ ቢያገኙም እንኳ ከ30 ቀናት በላይ ፖሊስን መቆጣጠር አይችሉም።