ትራምፕ በሥራ ቅጥር ወደ አሜሪካ ለሚገቡ ሰዎች ቪዛ 100 ሺህ ዶላር እንዲከፈል አዘዙ

አሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ በሥራ ቅጥር ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ክህሎት ያላቸው የውጭ ሀገር ሠራተኞች በሚሰጣቸው "ኤች-1ቢ" ቪዛ ላይ ተጨማሪ የ100 ሺህ ዶላር ክፍያ የሚጥል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈረሙ።

ይህ የቪዛ ፕሮግራም "አላግባብ ጥቅም ላይ እየዋለ" መሆኑን የሚጠቅሰው በፕሬዝዳንቱ የተፈረመው አዋጅ፤ ክፍያው ሳይፈጸም ወደ አሜሪካ መግባትን ይከለክላል።

የ"ኤች-1ቢ" ቪዛ ተቺዎች ይህ ፕሮግራም የአሜሪካዊ ሠራተኞች ቁጥርን ይቀንሳል በማለት ለረጅም ጊዜ ሲከራከሩ ቆይተዋል።

እንደ ኤሎን መስክ ያሉ አሠራሩን የሚደግፉ ሰዎች በአንጻሩ በዓለም ዙሪያ ያሉ ምርጥ ባለተሰጥኦዎችን ወደ አሜሪካ ለመሳብ ይረዳል ሲሉ ይከራከራሉ።

ትራምፕ ፊርማቸውን ያኖሩበት ሌላኛው ትዕዛዝ ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር ጀምሮ ክፍያ የሚፈጽሙ የተወሰኑ ስደተኞች በተፋጠነ መንገድ "ጎልድ ካርድ" የተሰኘ የቪዛ ዓይነት እንዲያገኙ የሚፈቅድ ነው።

አርብ ዕለት በጽህፈት ቤታቸው (ኦቫል ኦፊስ) ትዕዛዙ ሲፈረም የተገኙት አሜሪካ የንግድ ሚኒስትር ሃዋርድ ሉትኒክ፤ "ለኤች-1ቢ ቪዛ በዓመት 100 ሺህ ዶላር [ይከፈላል]፤ ሁሉም ግዙፍ ኩባንያዎች ተስማምተውበታል" ብለዋል። ከኩባንያዎቹ ጋር ንግግር መደረጉንም ጠቅሰዋል።

"የሆነን ሰው ልታሠለጥን ከሆነ፤ በመላ ሀገራችን ከሚገኙ ትላልቅ ዩኒቨርሲዎች ከወጡት አዲስ ተመራቂዎች አንዱን ታሠለጥናለህ። አሜሪካውያንን አሠልጥኑ፤ ሥራዎቻችንን የሚነጥቁንን ሰዎች ማምጣት አቁሙ" በማለትም ተናግረዋል።

ከአውሮፓውያኑ 2004 ጀምሮ በኤች-1ቢ ቪዛ አማካኝነት ወደ አሜሪካ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በዓመት ከ85,000 ሺህ እንዳይበልጥ ገደብ ተጥሎበታል።

እስካሁን በነበረው አሠራር ኤች-1ቢ ቪዛ ለማግኘት የሚከፈሉት የተለያዩ አስተዳደራዊ ወጪዎች ድምር 1,500 ዶላር ገደማ ነበር።

የአሜሪካ የዜግነት እና ኢሚግሬሽን አግልግሎት መሥሪያ ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው በቀጣዩ በጀት ዓመት ይህንን ቪዛ ለማግኘት የቀረበው ማመልከቻ ብዛት 359,000 ነው። ይህ ቁጥር ባለፉት አራት ዓመታት ከቀረበው የማመልከቻ ብዛት አንጻር ዝቅተኛ ነው።

ባለፈው በጀት ዓመት ከዚህ ፕሮግራም በብዙ የተጠቀመው የቴክኖሎጂ ኩባንያው አማዞን ሲሆን፣ እንደ ታታ፣ ማይክሮሶፍት፣ ሜታ፣ አፕል እና ጎግል ያሉ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት በተከታይነት እንደሚቀመጡ የአሜሪካ መንግሥት መረጃ ያመለክታል።

ኩባንያዎች ይህንን አሠራር ተጠቅመው ሠራተኞችን ከሌሎች ሀገራት ሲያስመጡ የነበረው አንዳንድ ሥራ መደቦችን የሚፈልጉት ክህሎት እና እውቀት ያለው ሰው መሙላት ስላልቻሉ እንደነበር ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አሁን ኤች-1ቢ ቪዛ ላይ 100 ሺህ ብር ክፍያ መጣሉ አንዳንድ ኩባንያዎች ሥራቸውን ከአሜሪካ ውጪ እንዲያደርጉ ሊገፋቸው እንደሚችልም ይገልጻሉ።

ኤች-1ቢ ቪዛን በተመለከተ የሚደረገው ክርክር ከዚህ ቀደም የትራምፕን ቡድን እና ደጋፊዎች ለሁለት ከፍሏቸው ነበር።

ትራምፕ ጥር ወር ላይ በዋይት ሐውስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ኤች-1ቢ ን በተመለከተ የሚቀርቡትን "የሁለት ወገኖች መከራከሪያዎችን" እንደሚረዱ ተናግረው ነበር።

ከዓመት በፊት ለምርጫ ዘመቻቸው ከቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪው ድጋፍ ለማግኘት በተንቀሳቀሱበት በወቅት ደግሞ ባለተሰጥኦዎችን ለመሳብ የሚኖረውን ሂደት ቀላል እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው ነበር። ለኮሌጅ ተመራቂዎች ግሪን ካርድ የመስጠት ዕቅድን እስከ ማቅረብም ደርሰው ነበር።