ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ቪዛ አመልካቾች እስከ 15,000 ዶላር የሚደርስ ገንዘብ እንዲያሲዙ ሊጠየቁ ነው
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ወደ አገሪቱ ለመግባት የቢዝነስ እና የቱሪስት ቪዛ አመልካቾች እስከ 15 ሺህ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ በማስያዣነት ሊጠየቁ እንደሚችሉ አስታወቀ።
ይህ በሁለት ሳምንት ውስጥ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል የተባለው የሙከራ ፕሮግራም ከቪዛ ጊዜያቸው በላይ የሚቆዩ ጎብኚዎችን ለመከላከል ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ያወጣው ይህ ማስታወቂያ በርካታ ሰዎች ወደ አገሪቱ ለመግባት የሚያደርጉትን ሂደት አስቸጋሪ ያደርግባቸዋል ተብሏል።
እንደ የፌደራል መንግሥቱ የምዝገባ ማስታወቂያ ከሆነ ይህ አሠራር በቀጣዮቹ 12 ወራት ውስጥ በሙከራነት በተወሰኑ አገራት ላይ ተግባራዊ ይሆናል።
የሙከራ መርሃ ግብሩ አሜሪካ ውስጥ ከቪዛ ጊዜያቸው በላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ዜጎች ባሏቸው አገራት እና የአገር ውስጥ ሰነዶች ላይ የላላ ቁጥጥር በሚያደርጉ አገራት ላይ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል ተብሏል።
የእነዚህ አገራት ዜጎች ለቪዛ ሲያመለክቱ 5,000, 10,000 ወይም 15,000 ዶላሮችን በማስያዣነት እንዲያቀርቡ ሊጠየቁ እንደሚችሉ ተገልጿል።
ይህ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አሠራር ይፋ የሆነው የትራምፕ አስተዳደር ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚጠየቁ የቪዛ አመልካቾች መስፈርቶችን እያጠናከረ በመጣበት ወቅት ነው።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአገር ማስወጣት እንዲሁም የድንበር ቁጥጥሩን ለማጠናከር በጀት ከፍ የማድረግ እና ወደ አገሪቱ በሕገወጥ የገቡ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋል እርምጃዎችን ሲወስዱ ቆይተዋል።
በሰኔ ወር ከ19 አገራት ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚያመለክቱ ግለሰቦች ላይ ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች የጉዞ እገዳ ጥለዋል።
በትራምፕ የስደተኞች ፖሊሲ ምክንያት የተወሰኑ ጎብኚዎች ወደ አሜሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት እየሰረዙ መሆኑ ይሰማል።
ከነሐሴ 20 ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው ይህ አዲሱ የቪዛ ማስያዣ ገንዘብ ፕሮግራም ለአንድ ዓመት ያህል ይቆያል ተብሎ ተገምቷል።
የቪዛ ጥያቄዎችን የሚመለከቱ ባለሥልጣናት 5,000፣ 10,000 እና 15,000 ዶላር ለማስያዣነት የመጠይቅ ምርጫ የተቀመጠላቸው ቢሆንም፣ በአብዛኛው ግን 10,000 ዶላር በማስያዣነት እንዲጠይቁ መመሪያው ያዛል።
መግለጫው አክሎም ተጓዦች በተሰጣቸው የቪዛ መቆያ ጊዜ መሠረት ወደ አገራቸው የሚመለሱ ከሆነ ያስያዙት ገንዘብ እንደሚመለስላቸው አስቀምጧል።
በትራምፕ የመጀመሪያው የሥልጣን ዘመን ማብቂያ ላይ፣ በኅዳር ወር 2020 ተመሳሳይ አሠራር ተግባራዊ ሆኖ ነበር።
ነገር ግን ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የዓለም አቀፍ ተጓዦች ቁጥር በመቀነሱ የተነሳ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሳይሆን መቅረቱ በመግለጫው ላይ ተገልጿል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ በዚህ መመሪያ ውስጥ የሚካተቱ አገራቱን ዝርዝር እንደሚገለጽ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም "አገራት የሚለዩት ከተፈቀደላቸው ውጪ በአሜሪካ በሚቆዩ ዜጎቻቸው ብዛት፣ የማንነት መለያ ሰነዶች ጉድለቶችን በመለየት እና በማጣራት፣ ያለነዋሪነት መስፈርት ዜግነትን በኢንቨስትመንት ሰበብ ማግኘትን እና የውጭ ፖሊሲን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው" ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ቢሮ በዚህ ውሳኔ ምን ያህል የቪዛ አመልካቾች እንደሚጎዱ ይፋ አላደረገም።
በትራምፕ የጉዞ እገዳ የተጣለባቸው በርካታ አገራት ከቪዛ ቀነ ገደባቸው በላይ የሚቆዩ አገራት ሲሆኑ፣ እነዚህም ኤርትራ፣ ቻድ፣ ሄይቲ፣ ምያንማር እና የመንን ያካትታል።
ከእዚህ በተጨማሪም የትራምፕ አስተዳደር ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚያስችላቸውን የቪዛ የቆይታ ጊዜ ያሳጠረ ሲሆን ለአንድ ጊዜ የሚያገለግል አድርጎታል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ለመምጣት ከሚወዳደሩበት ጊዜ አንስቶ የስደተኞች ጉዳይን ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገው የነበረ ሲሆን፣ ወደ ዋይት ሐውስ እንደተመለሱ ነበር በርካታ ስደተኞችን የሚመለከቱ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት።
ባለፉት ወራት በአሜሪካ ውስጥ ሳይመዘገቡ የሚገኙ ስደተኞች ታድነው እንዲታሰሩ እና እንዲባረሩ የሚያደርግ ዘመቻ እያካሄዱ ነው። በዚህ እርምጃቸው ምክንያት ትችት እና ከባድ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም በውሳኔያቸው ጸንተዋል።
ትራምፕ ከአሜሪካ ስደተኞችን ለማባረር ከሚወስዱት እርምጃ ጎን ለጎን ደግሞ ባለፈው ግንቦት ወር መጨራሻ ላይ ከሰኔ 1/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገ የ12 አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያደርግ ዕገዳ ጥለዋል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤታቸውም ይህንን የተለያዩ አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክለውን ዕገዳ በማስፋት የተጨማሪ 36 አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያደርግ የውሳኔ ሃሳብ ቀርቧል።