ቦሪስ ጆንሰን ከምርጫ ራሳቸውን በማግለላቸው በተፎካካሪያቸው ተሞገሱ

ሪሺ ሱናክ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰንን በይፋ አሞገሱ። 

ሙገሳው የመጣው ጆንሰን ለጠቅላይ ሚንስትርነት በድጋሚ እንደማይወዳደሩ ካስታወቁ በኋላ ነው። 

“ቦሪስ ጆንሰን ብሬግዚት እና የክትባት ስርጭት ላይ ስኬታማ ነበሩ” ሲሉ ሪሺ ሱናክ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። 

“ፈታኝ ከሆኑ ጊዜያቶች በአንዱ አገራችንን መርተዋል። ፑቲን በዩክሬን የጀመሩት አረመኔያዊ ጦርነት ወቅትም ነበሩ። ለዚህም ሁሌም እናመሰግናቸዋለን።"

በቀጣይ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ለመሆን የተሻለ ዕድል አላቸው የተባሉት ሪሺ ሱናክ “በድጋሚ ጠቅላይ ሚንስትር ለመሆን ፍላጎት ባይኖረውም በአገር ውስጥ እና በውጭ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አምናለሁ” ብለዋል። 

በተሾሙ በ45 ቀናት ስልጣን በቃኝ ያሉትን የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስን ለመተካት የሚደረገው ውድድር ቀነ ገደብ ተቃርቧል።

ሪሺ ሱናክ የቀድሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አጋሮችን ጨምሮ ከፓርቲያቸው 128 የፓርላማ አባላትን ድጋፍ በመሰብሰብ ውድድሩን እየመሩ ይገኛሉ ተብሎ ነበር።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በ53 የድምጽ ድጋፍ ሁለተኛ ሆነው እየተከተሉ ስለመሆናቸው ቢቢሲ መረጃ አግኝቷል።

ሆኖም ደጋፊዎቻቸው ወደ ውድድሩ ለመግባት የሚያስፈልገው የድምፅ ድጋፍ እንዳላቸው በመጥቀስ 100 የፖርላማ አባላት የድጋፍ ድምጽ እንዳገኙ ይከራከራሉ።

ቦሪስ ጆንሰን የህዝብ እንደራሴዎች ድጋፍ ቢኖረኝም “አሁን ይህንን የማድረጊያው ትክክለኛ ጊዜ አይደለም። በፓርላማ ውስጥ የተዋሃደ ፓርቲ ሳይኖር ማስተዳደር ይከብዳል” ብለዋል። 

እስከ 102 የሚደርሱ የሕዝብ እንደራሴዎች ድጋፍ እንዳላቸውም አስታውቀዋል። 

ቢቢሲ 57 የሕዝብ እንደራሴዎች እንደሚደግፏቸው በይፋ ቢያረጋግጡም የቀሪዎቹን ለማረጋገጥ አልቻለም። 

ፔኒ ሞርዳውንት ውድድሩ መቀላቀላቸውን በይፋ ያሳወቁ ብቸኛ እጩ ናቸው ነገር ግን በ23 የፓርላማ አባላት ድጋፍ ወደ ኋላ ቀርተዋል።

የቢቢሲዋ ላውራ ኩንስስበርግ ቦሪስ ጆንሰን እና ሪሺ ሱናክ ቅዳሜ አመሻሹ ላይ ተገናኝተው እንደነበር ገልጻ ነገር ግን በውይይታቸው ላይ መግለጫ ይወጣ እንደሆነ እርግጠኛ አልነበረችም።

ቢቢሲ ድጋፍ የሰጡ የፓርላማ አባላትን መረጃ ሲሰበስብ ቆይቷል።

ከ357 ወግ አጥባቂ የፓርላማ አባላት መካከል የ204ቱ የመምረጥ ፍላጎታቸው የሚታወቅ እና በቢቢሲ የተረጋገጠ ሲሆን የበርካቶች ፍላጎት ግን እስካሁን ግልጽ አልሆነም።

ለውድድሩ በቂ ድጋፍ ለማግኘት እስከ ፊታችን ሰኞ 8 ሰዓት ድረስ ጊዜ አላቸው።

በዚህም ለሚቀጥለው የውድድር ደረጃ ብቁ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ።

የፓርቲው የፓርላማ አባላት አንድ እጩን ብቻ የሚደግፉ ከሆነ ሰኞ ከሰዓት በኋላ ዩናይትድ ኪንግደም አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊኖራት ይችላል።

ካልሆነ ግን የወግ አጥባቂ ፓርቲ አባላት ምርጫ በኦንላይን የሚያካሂዱ ሲሆን ውጤቱም በመጪው ሳምንት አርብ ይፋ ይሆናል።

የምርጫ አስተያየቶች እንደሚያሳዩት በዚህ ኦንላይን ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከምርጫው ራሳቸውን ባያገሉ ኖሮ የአባላቱን ድምጽ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ተገምቶ ነበር።