ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከ25 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያስወጣው አዲሱ የአሜሪካ የሚሳዔል መከላከያ
አሜሪካ "ጎልደን ዶም" ስትል የሰየመችው እና የወደፊቱ የሚሳዔል መቃወሚያ የተባለውን ዲዛይን ይፋ ማድረጓን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም የሥልጣን ዘመናቸው ከማብቃቱ በፊት አገልግሎት ላይ እንደሚውል ተናግረዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ሁለተኛውን የሥልጣን ዘመናቸውን እንደጀመሩ፣ ይህንን አሜሪካ ላይ የሚቃጣን የአየር ጥቃት፣ ባለስቲክ እና ክሩዝ ሚሳዔሎች ጨምሮ የሚከላከል አዲስ የሚሳዔል መከላከያ "ቀጣዩን ትውልድ " ለመከላከል በሚል ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተናግረው ነበር።
የሚሳዔል መቃወሚያውን ወደ ሥራ ለማስገባት 25 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል የተባለ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ተጨማሪ ወጪዎችን እንደሚጠይቅ ተገልጿል።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት አሜሪካ ያላት የሚሳዔል መከላከያዎች እየዘመኑ እና እየተራቀቁ የመጡ የጦር መሳሪያዎችን ለመመከት የሚሆኑ አይደሉም ሲሉ እያስጠነቀቁ ነበር።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአሁኑ ጊዜ በሕዋ ኃይል ውስጥ የሕዋ ዘመቻ ምክትል ኃላፊ የሆኑትን ጄነራል ማይክል ጉትሊን ፕሮጀክቱን በበላይነት እንደሚመሩት ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣናቸውን በተረከቡ በሰባተኛው ቀን የመከላከያ ሚኒስትራቸው የአየር ጥቃቶችን ለመከላከል እና ለመመከት የሚያስችል ሥርዓት ላይ ዕቅዳቸውን እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።
በወቅቱ ዋይት ሐውስ አሜሪካ ፊት ለፊቷ የተጋፈጠችው "በጣም አስከፊ ስጋት" ሲል ገልጾት ነበር።
ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት በጽህፈት ቤታቸው (ኦቫል ኦፊስ) ውስጥ ንግግር ሲያደርጉ የሚሳዔል የመከላከያ ሥርዓቱ ከመሬት፣ ከባሕር እና ከሕዋ ላይ የሚነሱ ጥቃቶችን መመከት የሚያስችል "የቀጣይ ትውልድ" ቴክኖሎጂዎችን ያቀፈ ነው ብለዋል።
አክለውም በሕዋ ላይ የሚቀመጡ ጠቋሚዎችን (ሴንሰሮችን) እና ማምከን የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን እንደሚያካትት ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ካናዳ የሥርዓቱ አካል ለመሆን ጥያቄ ማቅረቧንም ተናግረዋል።
የካናዳው የመከላከያ ሚኒስትር ቢል ብሌየር በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ዋሽንግተንን በጎበኙበት ወቅት ካናዳ በዶም ፕሮጀክት ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት የገለጹ ሲሆን "ትርጉም ያለው" እና የአገሪቱን "ብሔራዊ ጥቅም" የሚያስጠብቅ ፕሮጀክት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም "ካናዳ በአካባቢው ምን እየተካሄደ እንዳለ ማወቅ አለባት" እና የሚመጡ ስጋቶችን፣ በአርክቲክ ውስጥ ጨምር በማወቅ መጠንቀቅ ትፈልጋለች።
ትራምፕ አክለውም ሥርዓቱ ከሌላኛው የዓለም ክፍል እንዲሁም ከጠፈር የሚወነጨፉ ሚሳኤሎችን የማምከን አቅም ይኖረዋል ብለዋል።
ሥርዓቱ እስራኤል ከ2011 ጀምሮ አገሪቱ ሮኬቶችን እና ሚሳዔሎችን ለማምከን እየተጠቀመችበት ያለውን አይረን ዶም በከፊል መነሻ የሚያደርግ ነው።
ጎልደን ዶም፣ ከአይረን ዶም በብዙ እጥፍ ይለያል የተባለ ሲሆን፣ ከድምጽ ፍጥነት በላይ የሚምዘገዘጉ ሃይፐርሶኒክ ጦር መሳሪያዎችን እና ፎብስ (FOBS ) በመባል የሚታወቀውን እና ወደ ዒላማው ለመወንጨፍ ዝቅተኛ የምድር ምህዋርን የሚጠቀመውን የጦር መሣርያ ሥርዓት ጨምሮ የተለያዩ ስጋቶችን ለመመከት የተነደፈ መሆኑ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ የሚሳዔል አረርን ከጠፈር ሊልክ የሚችል አቅም እንደሚኖረው ተገልጿል።
ትራምፕ "ሁሉም ከአየር ላይ ይመታሉ" ካሉ በኋላ "የውጤታማነት መጠኑ ለመቶ ፐርሰንት እጅግ በጣም ቅርብ ነው" ብለዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ቀደም ሲል እንደተናገሩት ጎልደን ዶም ዩናይትድ ስቴትስ ሚሳዔሎችን በተወነጨፉበት የተለያዩ ደረጃዎች ላይ፣ ከመወንጨፋቸው በፊት ሆነ ገና በአየር ላይ እያሉ እንዲመክኑ የማድረግ አቅም ይሰጣታል።
የሥርዓቱ በርካታ ገፅታዎችን በአንድ ያማከለ ዕዝ ስር እንደሚሆን የአሜሪካ መከላከያ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት እንዳስታወቁት ፕሮግራሙ ለመጀመሪያ ጊዜ የ25 ቢሊዮን ዶላር መነሻ ኢንቨስትመንት የሚያስፈልገው ሲሆን በጊዜ ሂደት እስከ 175 ቢሊዮን ዶላር ያስወጣል።
የኮንግረሱ በጀት ቢሮ ግን መንግሥት ከ20 ዓመታት በላይ ለሚዘልቅ ጊዜ እስከ 542 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ተጨማሪ ወጪን በሕዋ ላይ በተመሠረቱ የሥርዓቱ ክፍሎች ላይ ብቻ እንደሚያወጣ ገምቷል።
የፔንታጎን ባለሥልጣናት ነባር ሥርዓቶች በሩሲያ እና በቻይና ከተነደፉት አዲስ የሚሳዔል ቴክኖሎጂዎች ጋር አብረው እንደማይሄዱ ለረጅም ጊዜ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።
ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት በኦቫል ኦፊስ "በእርግጥ አሁን ያለው ሥርዓት የለም" ብለዋል።
"የተወሰኑ ሚሳዔል መከላከያዎች አሉን፤ ነገር ግን ምንም ዓይነት ሥርዓት የለም . . . እንደዚህ ያለ ነገር አልነበረም።"
በመከላከያ የስለላ ኤጀንሲ በቅርቡ የተለቀቀው ሰነድ እንደሚያሳየው ቻይና እና ሩሲያ በአሜሪካ መከላከያ ውስጥ ያሉትን "ክፍተቶች ለመጠቀም" በንቃት አዳዲስ ሥርዓቶችን እየነደፉ ነው።
የሚሳዔል ፉክክሩም "በመጠንም ሆነ በቴክኖሎጂ እየሰፋ ይሄዳል" ብለዋል።