በማያጨሱ ሰዎች ላይ የሳንባ ካንሰር የጨመረበት ምክንያት ምንድን ነው?

አጭሰው በማያውቁ ሰዎች ላይ የሳንባ ካንሰር ክስተት ቁጥር እየጨመረ ነው።

በሽታው በማጨስ ምክንያት ከሚመጣው የሳንባ ካንሰር የተለየ ነው፤ ስለዚህ መንስዔው ምንድን ነው?

ማርታ ሳሏ ሲቀየር እና በመተንፈሻ መስመሯ ውስጥ ያለው አክታ እየጨመረ ሲሄድ የሆነ ችግር እንዳለ ተገነዘበች።

ሐኪሞቿ ሳንባዎቿ ሥር የሰደደ በሽታ እንዲይዙ ያደረጋት ያልተለመደ መታወክ ነው ብለው አሰቡ። "አትጨነቂ፣ እሱ መሆን አለበት" ተብላለች።

በመጨረሻ ራጅ ስትነሳ ሳንባዋ ላይ የጠቆረ ነገር ተገኘ።

"ይህ የነገሩ መጀመሪያ ሆነ" ስትል የ59 ዓመቷ ማርታ ታስታውሳለች። "በመጀመሪያ የሲቲ ስካን ምርመራ ተደረገ፣ ከዚያም ብሮንኮስኮፒ (ረጅም ቱቦን በመጠቀም በሰዎች ሳንባ ውስጥ ያሉትን የአየር መተላለፊያ መንገዶች ለመመርመር የሚደረግ ሂደት) የኅብረ ሕዋስ ናሙናዎችን ተወሰደ።

"እብጠቱ ከተወገደ በኋላ፣ ምልክቶቹን ለመጀመሪያ ጊዜ ለጠቅላላ ሐኪሟ ካሳወቀች ከአራት ወራት በኋላ፣ የምርመራውን ውጤት አገኘች። ደረጃ ሦስት የሳንባ ካንሰር ነበር።

እብጠቱ በዙሪያው ባሉት የብሽሽት (ሊምፍ) ዕጢዎች ውስጥ ሰርጎ ገብቷል፤ ነገር ግን እስካሁን ወደ ሌሎች የአካል ክፍሎች አልተስፋፋም።

ማርታ ሁኔታውን "ፍጹም አስደንጋጭ ነበር" ብላለች። አልፎ አልፎ ሲጋራ ብታጨስም ራሷን እንደ አጫሽ ቆጥራ አታውቅም።

የሳንባ ካንሰር በዓለም ላይ በጣም የተለመደ ካንሰር ሲሆን፣ በካንሰር ምክንያት ለሚከሰቱ ሞቶች ዋነኛው መንስኤ ነው።

እ.ኤ.አ. በ2022 ወደ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲያዙ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሞተዋል።

ምንም እንኳን ከትንባሆ ጋር የተያያዙ የሳንባ ካንሰሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ አብዛኛው የምርመራ ውጤት ቢመዘገቡም፤ ለበርካታ አስርት ዓመታት የሲጋራ ማጨስ መጠን እየቀነሰ ነው።

በብዙ የዓለም አገራት የአጫሾች ቁጥር መቀነሱን ሲቀጥል፣ ሲጋራ አጭሰው በማያውቁ ሰዎች ላይ የሚከሰተው የሳንባ ካንሰር መጠን እየጨመረ ነው።

ከ10 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑት የሳንባ ካንሰር ምርመራዎች አሁን ሲጋራ በማያጨሱ ግለሰቦች ላይ ተደርገዋል።

"በጭራሽ በማያጨሱ ሰዎች ላይ ያለው የሳንባ ካንሰር ልዩ ሞለኪውላዊ ባህሪያት ያለው የተለየ በሽታ ሆኖ ብቅ እያለ ነው። ይህም በሕክምና ውሳኔዎች እና ውጤቶችን በቀጥታ ይነካል" ሲሉ በስዊትዘርላንድ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የካንሰር ሐኪም የሆኑት አንድሪያስ ዊኪ ይናገራሉ።

በምርመራው ላይ ያለው አማካይ ዕድሜ ከማጨስ ጋር ከተያያዙ የሳንባ ካንሰር ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም፣ የሳንባ ካንሰር ያለባቸው ወጣት ታካሚዎች በጭራሽ አላጨሱም።

"የ30 እና 35 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የሳንባ ካንሰር ያለባቸውን ስናይ አብዛኛውን ጊዜ አጫሾች አይደሉም" ይላሉ።

ሌላው ልዩነት በሕክምና የተለየው የካንሰር ዓይነት ነው።

እስከ 1950ዎቹ እና 1960ዎቹ ድረስ፣ በጣም የተለመደው የሳንባ ካንሰር ስኩዌመስ ሴል ካርሲኖማ ነበር።

ይህ ዓይነቱ ካንሰር በሳንባ ውስጥ ካሉት ሕዋሳት ይጀምራል።

በአንጻሩ በማያጨሱ ሰዎች ላይ ያለው የሳንባ ካንሰር ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል አድኖካርሲኖማ (adenocarcinoma) ነው። ይህ ዓይነቱ አክታ በሚያመነጩ ሕዋሳት ውስጥ ይጀምራል።

በአሁኑ ጊዜ በአጫሾች እና በጭራሽ በማያጨሱ ሰዎች ውስጥ በጣም የተለመደ የሳንባ ካንሰር ነው።

ልክ እንደ ሌሎች የሳንባ ካንሰር ዓይነቶች፣ አድኖካርሲኖማ ብዙውን ጊዜ የሚለየው በከፍተኛ ደረጃ ከተስፋፋ በኋላ ነው።

"በሳንባዎ ውስጥ አንድ ቦታ ላይ የተደበቀ 1 ሴሜ (0.4 ኢንች) ዕጢ ካለ፣ እርስዎ አያስተውሉትም" ይላሉ ዊኪ።

የማያቋርጥ ሳል፣ የደረት ሕመም፣ የትንፋሽ ማጠር ወይም ማቃሰትን የሚያጠቃልሉት የመጀመሪያዎቹ ምልክቶች የሚታዩት እብጠቱ ሲበዛ ወይም ሲሠራጭ ብቻ ነው።

በተጨማሪም፣ በሲጋራ እና በሳንባ ካንሰር መካከል ያለው ታሪካዊ ጠንካራ ትስስር አጫሾች ያልሆኑትን ሳያውቁ ምልክቶችን ከሌሎች ምክንያቶች ጋር እንዲያስተሳስሩት ሊያደርጋቸው ይችላል ይላሉ ዊኪ።

"አጭሰው በማያውቁ ሰዎች ላይ የሚከሰቱት አብዛኞቹ ጉዳዮች በሦስተኛ ወይም በአራተኛ ደረጃ ላይ ብቻ ነው የሚመረመሩት።"

በጭራሽ በማያጨሱ ሰዎች ላይ የሚከሰተው የሳንባ ካንሰር በሴቶች ላይም የተለመደ ነው።

አጭሰው የማያውቁ ሴቶች በሳንባ ካንሰር የመጠቃት ዕድላቸው ከወንዶች ፈጽሞ ከማያጨሱ ሁለት እጥፍ ይበልጣል።

ከሳንባ አፈጣጠር እና ከአካባቢያዊ ተጋላጭነት በተጨማሪ ቢያንስ የመልሱ ክፍል በሴቶች ላይ በተለይም በእስያ ሴቶች ላይ በብዛት በሚታዩ የዘረ መል ለውጦች ላይ ሊሆን ይችላል።

በጣም ከተስፋፋው አንዱ ኢጂኤፍአር (EGFR) በመባል የሚታወቀው የዘረ መል ለውጥ (mutation) ነው።

የዘረ መል ለውጥ እየተባለ የሚጠራው ሲጋራ ማጨስ በማያውቁ ሰዎች ውስጥ ያሉት የሳንባ ካንሰር ህዋሶች አብዛኛውን ጊዜ ለካንሰር መንስኤ የሚሆኑ ብዙ ለውጥ ይኖራቸዋል ሲሉ ዊኪ ያብራራሉ።

እነዚህ የዘረመል ለውጦች የዕጢ ዕድገትን ያመጣሉ፣ ለምሳሌ ኢጂኤፍአር (EGFR) ጂን በሴሎች ወለል ላይ ላለ ፕሮቲን ኮድ እና ኤፒደርማል ዕድገት ውጤት ተቀባይ ተብሎ ይጠራል።

እነዚህ የዘረ መል ለውጦች በሴት ታካሚዎች ላይ በተለይም የእስያ ዝርያ ባላቸው ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰትባቸው ምክንያቶች ሙሉ በሙሉ አልተረዱም።

በምሥራቅ እስያ ውስጥ የኢስትሮጂንን ሜታቦሊዝምን የሚነኩ አንዳንድ የዘረመል ልዩነቶች የሴቶች ሆርሞኖች ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ መረጃዎች አሉ።

ምንም እንኳን መረጃው ብዙ የተፈተሸ ባይሆንም ይህ በእስያ ሴቶች ላይ የሚከሰተውን ሳንባ ካንሰር ከፍ ያለ ክስተትን ሊያብራራ ይችላል።

በማይጨሱ ሰዎች ላይ ወደ ሳንባ ካንሰር ሊያመራ የሚችል የዘረ መል ለውጥ መገኘቱን ተከትሎ የመድኃኒት ኢንዱስትሪው የእነዚያን ፕሮቲኖች እንቅስቃሴ የሚገድቡ መድኃኒቶችን ማዘጋጀት ጀመሯል።

ይሁን እንጂ ሕክምናው ብዙውን ጊዜ የመቋቋም ችሎታ ያለው የካንሰር ሕዋሳት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

በዚህም ምክንያት ዕጢው እንደገና ማገገምን ያስከትላል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ብዙ ጥረት ሲደረግ የቆየ ሲሆን፣ አዳዲስ የመድኃኒት ዓይነቶች አሁን ወደ ገበያ ገብተዋል።

በዚህ የተነሳ ለታካሚዎች ትንበያ በየጊዜው ተሻሽሏል።

"እንዲህ ዓይነት የዘረ መል ለውጥ የሚሸከሙ ታካሚዎች አማካይ የመዳን መጠን አሁን በርካታ ዓመታት ሆኗል" ሲሉ ዊኪ ያስረዳሉ።

"ከ10 ዓመታት በላይ በታለመለት ሕክምና ላይ የቆዩ ታካሚዎች አሉን። ይህ ከ20 ዓመታት በፊት አማካይ የመዳን መጠን ከ12 ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መሆኑ ሲታሰብ ይህ ትልቅ እርምጃ ነው።"

በማያጨሱ ሰዎች ላይ ያለው የሳንባ ካንሰር መጠን እየጨመረ በሄደ ቁጥር የመከላከያ ስልቶችን ማዘጋጀት ወሳኝ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሬዶን እና የእጅ አዙር አጫሽ መሆን የሳንባ ካንሰርን አደጋ ከፍ ሊያደርግ ይችላል። በተጨማሪም ለማብሰያ ጭስ ወይም በደንብ ባልተሸፈኑ ክፍሎች ውስጥ እንጨት ወይም የድንጋይ ከሰል ለሚጠቀሙ ምድጃዎች መጋለጥ ይህንን አደጋ ሊጨምር ይችላል።

ሴቶች በባህላዊ መንገድ ብዙ ጊዜ በቤት ውስጥ ስለሚያሳልፉ በተለይ ለእንደዚህ ዓይነት የቤት ውስጥ የአየር ብክለት የተጋለጡ ናቸው። ይሁን እንጂ ከቤት ውጪ ያለው የአየር ብክለት ለሳንባ ካንሰር ዕድገት የበለጠ ጉልህ ምክንያት ነው።

ለነገሩ ከቤት ውጪ የአየር ብክለት ከማጨስ ቀጥሎ ለሁሉም የሳንባ ካንሰር ክስተቶች ሁለተኛው ዋነኛ መንስኤ ነው።

ጥናቶች እንዳመለከቱት በጣም በተበከለ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ከሌሎች ይልቅ በሳንባ ካንሰር የመሞት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

በዲያሜትር ከ2.5 ማይክሮን ያነሰ (የሰው ፀጉር ወርድ 30ኛ ገደማ) በተለይም በተሽከርካሪ ጭስ እና በተቀጣጣይ ጭስ ውስጥ የሚገኘው ቅንጣት ጉዳይ ወሳኝ ሚና ያለው ይመስላል።

የአየር ብክለት የካንሰር ዘረ መል ለውጥን በሚይዙ አጫሾች ላይ የሳንባ ካንሰርን እንዴት እንደሚያስነሳ በለንደን የፍራንሲስ ክሪክ ኢንስቲትዩት የምርምር ትኩረት ሆኖ ቆይቷል።

በፍራንሲስ ክሪክ ኢንስቲትዩት የካንሰር ዝግመተ ለውጥ እና የዘረመል ጉዳይ ላብራቶሪ የድኅረ-ዶክትሬት ተመራማሪ ዊልያም ሂል "ስለ የአካባቢ ካርሲኖጂንስ ስናስብ በዲኤንኤ ውስጥ ለውጥ እንደሚፈጥሩ እናስባለን" ብለዋል።

ለምሳሌ የሲጋራ ጭስ ዲኤንኤችንን ስለሚጎዳ ለሳንባ ካንሰር ይዳርጋል።

"ነገር ግን የእኛ ጥናት ፒኤም2.5 ዲኤንኤውን በቀጥታ እንደማይለውጥ ይልቁንም በሳንባችን ውስጥ ተቀምጠው የተኙ ልውጥ ሕዋሳትን በማንቃት በሳንባ ካንሰር መጀመሪያ ላይ እንዲጀምሩ ያደርጋል።"

በአየር ብክለት እና በሳንባ ካንሰር መካከል ያለው ግንኙነት አዲስ አይደለም።

እ.ኤ.አ. በ1950 በጭስ እና በሳንባ ካንሰር መካከል ያለውን ግንኙነት በሚያረጋግጥ አንድ አስደናቂ ጥናት ላይ ፀሐፊዎቹ ከቅሪተ አካል ነዳጆች የሚቃጠሉ የውጭ ብክለትን እንደ ምክንያት ጠቁመዋል።

ግን እስካሁን ድረስ ፖሊሲዎች በትምባሆ ቁጥጥር ላይ ብቻ ያተኮሩ ናቸው። ነገር ግን ከ75 ዓመታት በኋላ የአየር ብክለት በመጨረሻ ትኩረት እያገኘ ነው።

ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ በአውሮፓ እና በአሜሪካ የአየር ብክለት ደረጃ ቀንሷል።

ነገር ግን በሳንባ ካንሰር መጠን ላይ የሚደረጉ ለውጦች ተጽእኖ ገና አልታየም። በአሜሪካ ሜሪላንድ ውስጥ ከሚገኘው የናሽናል ካንሰር ተቋም የካንሰር ሐኪም ክሪስቲን በርግ "የተጋላጭነት ለውጦች በሳንባ ካንሰር ላይ ለመንፀባረቅ ከ15 እስከ 20 ዓመታት ሊፈጅ ይችላል ነገር ግን በእርግጠኝነት አናውቅም" ይላሉ።

"የሰደድ እሳት አደጋ እየጨመረ በመምጣቱ የአየር ብክለት እና ፒኤም2.5 ደረጃዎች በአንዳንድ የአሜሪካ ክልሎች እንደገና እያደገ ነው" ይላሉ በርግ።

"ቢያንስ አንድ ጥናት ለሰደድ እሳት መጋለጥ እና በሳንባ ካንሰር መጨመር መካከል ያለውን ግንኙነት አሳይቷል። ከድንጋይ ከሰል፣ ዘይት እና ጋዝ መሸጋገር የዓለም ሙቀት መጨመርን ለመቀነስ ብቻ ሳይሆን የአየር ጥራትን ለማሻሻል ወሳኝ ነው።"

በሊዮን፣ ፈረንሳይ ውስጥ በዓለም አቀፍ የካንሰር ምርምር ኤጀንሲ (አይኤአርሲ) የድኅረ-ዶክትሬት ተመራማሪ ጋንፌንግ ሉኦ "99 በመቶው የዓለም ሕዝብ የሚኖረው የአየር ብክለት መጠን ከዓለም የጤና ድርጅት መመሪያ ገደብ በላይ በሆነባቸው አካባቢዎች ነው" ይላል።

በቅርቡ በተደረገ ጥናት፣ የዓለም አቀፍ የካንሰር ምርምር ኤጀንሲ ተመራማሪዎች በግምት 194 ሺህ የሚጠጉ የሳንባ ካንሰር ክስተቶች አሳሳቢ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።

"ከፍተኛው የካንሰር ተጋላጭነት በምሥራቅ እስያ በተለይም በቻይና ውስጥ እንደሚኖር ይገመታል" ሲል ሉኦ ተናግሯል።

በዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሠረት በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የአየር ብክለት ደረጃ ባለባቸው እንደ ሕንድ ባሉ አገራት ውስጥ ወደፊት በአየር ብክለት ሳቢያ በሚከሰት የሳንባ ካንሰር ሞት ቁጥር ሊጨምር ይችላል።

በዩናይትድ ኪንግደም በ2022 በአየር ብክለት ምክንያት 1,100 ሰዎች በአድኖካርሲኖማ የሳምባ በሽታ መያዛቸውን የዓለም አቀፍ የካንሰር ምርምር ኤጀንሲ ጥናት አረጋግጧል።

የኤፒዲሚዮሎጂስት እና የጥናቱ ተባባሪ የሆነችው ሃሪየት ራምጋይ "ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ሰዎች በጭራሽ አጫሾች አይደሉም" ብለዋል።

አድኖካርሲኖማ በአጫሾች ውስጥ በተለይም ፊልተር ሲጋራዎችን በሚጠቀሙ ላይ ይከሰታል።

"አሁንም የማናውቀው ብዙ ነገር አለ" ትላለች ራምጋይ። "የተለያዩ ሁኔታዎችን ለመለየት እና ለምሳሌ ለሳንባ ካንሰር ከመጋለጣችን በፊት ምን ያህል ጊዜ ለአየር ብክለት መጋለጥ እንደሚያስፈልግ ለመረዳት ተጨማሪ ምርምር ያስፈልጋል።"

ሕክምናዎች መሻሻላቸውን በሚቀጥሉበት ጊዜ፣ በማያጨሱ ሰዎች ላይ ያለው የሳንባ ካንሰር ገዳይነቱ እየቀነሰ ነው።

ይህ ዓይነቱ የሳንባ ካንሰር አንድ ቀን በታሪክ ከአዋቂ ወንድ አጫሾች ጋር የተገናኘ በጣም የተለመደ በሽታ እንደሚሆን መገመት ይቻላል።

በታዋቂው ባህል ውስጥ ስለ በሽታው ያለንን አመለካከት ይለውጣል። "...እነሱ [ታካሚዎች] ቢያንስ በከፊል ለበሽታቸው ተጠያቂ ናቸው የሚለው አስተሳሰብ እንደ አለመታደል ሆኖ አሁንም ተስፋፍቷል" ይላሉ ዊኪ።