ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሜታ ፌስቡክና ኢንስታግራም ላይ የፍልስጤም መረጃዎችን መገደቡን ምርመራ አጋለጠ
በእስራኤልና ጋዛ ጦርነት ወቅት የፍልስጤም መገናኛ ብዙኃን የሚያቀርቧቸው ዜናዎች አንባቢዎችና ተመልካቾች ጋር እንዳይደርሱ ፌስቡክ ከፍተኛ ገደብ እንደጣለ የቢቢሲ ምርመራ ይጠቁማል።
በፌስቡክን መረጃ ላይ በተደገረው የዳሰሳ ጥናት መሠረት እአአ ከጥቅምት 2023 ጀምሮ በጋዛና ዌስት ባንክ ያሉ የፍልስጤም መገናኛ ብዙኃን ላይ ገደብ ተደርጓል።
ሜታ በሚያስተዳድረው ፌስቡክና ኢንስታግራም የመረጃ ተደራሽነታቸው ውስን እንዲሆንም ተደርጓል።
ፍልስጤማውን የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች የሚሰጧቸው አስተያየቶች ላይ ቁጥጥር እንደተደረገም የቢቢሲ ምርመራ ያሳያል።
ሜታ በበኩሉ ሆነ ብሎ ድምጾችን አፍኗል የሚለው ክስ "ፍጹም ሐሰተኛ ነው" ሲል አስተባብሏል።
የእስራኤልና ጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ወደ ጋዛ መግባት የቻሉ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ጥቂት ናቸው። የገቡትም የእስራኤል ወታደሮች በቅርብ ርቀት እየተከታተሏቸው ነው።
ከጋዛ ታሪኮችን መስማት የሚፈልጉ ሰዎች መረጃውን እንዳያገኙ አፈና ተደርጓል።
ፓለስታይን ቲቪ፣ ዋፋ ኒውስ ኤጀንሲ እና ፓሊስቲንያን አል-ዋታን ኒውስ ከዌስት ባንክ ሆነው ስለ ጋዛ መረጃ የሚሰጡ የፌስቡክ ገጾች ናቸው።
ቢቢሲ አረብኛ 20 ታዋቂ የፍልስጤም መገናኛ ብዙኃን መረጃ ሐማስ እስራኤል ላይ ጥቃት ከመሰንዘሩ በፊትና በኋላ ምን ያህል እንደተሰራጨ ምርመራ አድርጓል።
ፌስቡክ ላይ ያለውን የመረጃ ስርጭትና ተደራሽነት በመለካት አንድን ይዘት ምን ያህል ሰዎች እንደተመለከቱት ምርመራ ተደርጓል።
ምን ያህል ሰው መረጃውን እንዳጋራውና ምን ያህል አስተያየት እንደተሰጠም ተፈትሿል።
ፌስቡክና የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን
በጦርነት ወቅት የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የበይነ መረብ ተሳትፎ እንደሚጨምር ቢጠበቅም መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከጥቅምት 7/2023 ወዲህ በ77 በመቶ ቀንሷል።
ፓለስታይን ቲቪ ፌስቡክ ላይ 5.8 ሚሊዮን ተከታዮች አሉት። በገጹ የሚለጠፉ መረጃዎችን የሚመለከቱ ሰዎች ቁጥር 60% መቀነሱን የሚድያው መረጃ ይጠቁማል።
በፓለስታይን ቲቪ የሚሠራው ታሪቅ ዚያድ "የምናወጣውን መረጃ ሰዎች ማየት አቆሙ። የመረጃ ልውውጥም ተገደበ" ይላል።
ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች በበይነ መረብ የሚለቁት መረጃ ባለፈው ዓመት ውስጥ በሜታ "ዕቀባ እየተደረገበት ነው" ማለታቸው አይዘነጋም።
መረጃዎቹን የሚያዩ ሰዎች ቁጥር እንዲገደብ ነው የተደረገው።
ቢቢሲ 20 የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የፌስቡክ ገጾችን ተደራሽነት በመፈተሽ ንጽጽር አድርጓል።
ያዶት አህሮኖት፣ እስራኤል ሃዮም እና ቻናል 13 ይጠቀሳሉ። እነዚህ ገጾች ስለ ጦርነቱ ብዙ መረጃ የሚያወጡ ሲሆን ተደራሽነታቸው በ37% ከፍ ብሏል።
ፍልስጤማውያንና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሜታ በገጹ የሚዘዋወሩ መረጃዎችን በፍትሐዊነት እንደማይቆጣጠር ሲናገሩ ይደመጣሉ።
በ2021 ሜታ ባሠራው ገለልተኛ ሪፖርት ላይ የይዘት ቁጥጥር ሂደቱ ክፍተት ሆነ ተብሎ የተከሰተ ሳይሆን አረብኛ ተናጋሪ የይዘት ተቆጣጣሪዎች ውስን ስለሆኑ ነው ተብሏል።
አወንታዊ የሆኑ ይዘቶች እንደ ነውጠኛ ወይም አስቀያሚ ተደርገው ሲፈረጁ ተስተውሏል።
አልሀምዱሊላህ የሚለው አረብኛ ሀረግ "ፈጣሪ ይመስገን" ከሚለው ትርጉሙ ወጥቶ "ፍልስጤማውያን አሸባሪዎች ለነጻነታቸው እየታገሉ ነው፣ ፈጣሪ ይመስገን" ተብሎ መተርጎሙ አንድ ምሳሌ ነው።
ፌስቡክና የአረብ መገናኛ ብዙኃን
ቢቢሲ ስካይ ኒውስ እና አል-ጀዚራን ጨምሮ 30 ታዋቂ የአረብኛ መገናኛ ብዙኃን መረጃ ተደራሽነትን ቃኝቷል።
እነዚህ ገጸች ተደራሽነታቸው እስከ 100% ጨምሯል።
ሜታ ቢቢሲ የሠራውን ምርመራ በተመለከተ በሰጠው ምላሽ ላይ ከጥቅምት 2023 ወዲህ ምንም ዓይነት "ጊዜያዊ የመገልገያ ወይም የፖሊስ ማሻሻሻያ" በምሥጢር አላደረገም።
ስለ ጦርነቱ ብቻ መረጃ የሚሰጡ ገጾች ተደራሽነታቸው ቀንሶባቸው ሊሆን እንደሚችል ገልጿል።
"ስህተት እንደምሠራ እናምናለን። ሆኖም ግን አንድን ድምጽ ሆነ ብላችሁ አፍናችኋላ የሚለው ፍጹም ሐሰት ነው" ሲሉ የሜታ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
ሾልከው የወጡ የኢንስታግራም ሰነዶች
ቢቢሲ አምስት የቀድሞና የአሁን የሜታ ሠራተኞችን አነጋግሯል።
በፍልስጤማውያን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ላይ የድርጅቱ ፖሊሲ የሚያሳድረውን ጫና ይናገራሉ።
ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አንድ ቢቢሲ ያነጋገረው ባለሙያ በኢንስታግራም አልጎሪዝም ላይ የተደረገውን ለውጥ የሚያሳይ ሰነድ አጋርቷል።
በኢንስታግራም የሚወጡ ይዘቶች ላይ ፍልስጤማውያን የሚሰጡትን አስተያየት ለመገደብ ነው የፖሊሲ ለውጡ የተደረገው።
"ሐማስ ጥቃት በሰነዘረ በሳምንት ውስጥ ፍልስጤማውያን ላይ ጠንካራ እንዲሆን መተግበሪያው ለውጥ ተደረገበት" ይላል ባለሙያው።
በሜታ ውስጥ የተለዋወጧቸው መልዕክቶች እንደሚያሳዩት አንድ መኃንዲስ ለውጡ ላይ ያለውን ቅራኔ አስታውቋል።
ባለሙያው "ፍልስጤማውያን ተጠቃሚዎች ላይ መድልዎ የሚያደርስና የሚጎዳ ለውጥ
ሜታ የፖሊሲ ለውጥ እንዳደረገ አልካደም። ሆኖም ግን ይህን ያደረገው ከፍልስጤም ግዛቶች የሚወጣውን "ብዙ የጥላቻ ንግግር" ለመገደብ እንደሆነ ነው የገለጸው።
ጦርነቱ ሲጀመር የተደረጉ የፖሊሲ ለውጦች ላይ ማሻሻያ መደረጉን ቢገልጽም ማሻሻያው መቼ እንደተደረገ ግን አላሳወቀም።
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ቢያንስ 137 ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች መገደላቸው ተገልጿል።
የተወሰኑ ጋዜጠኞች አደጋው አሁንም ቢኖርም ሥራቸውን ቀጥለዋል።
በሰሜናዊ ጋዛ ከሚሠሩ የፎቶ ጋዜጠኞች አንዱ የሆነው ኦማር ኤል ቃታ "አብዛኛው የምናገኘው መረጃ አሰቃቂ ስለሆነ አይለቀቅም። ለምሳሌ የእስራኤል ጦር ጭፍጨፋ ፈጽሞ ብንቀርጽ ቪድዮው አይሰራጭም" ይላል።
"ፈተናው ቢኖርም፣ አደጋው ቢበዛም፣ ይዘቶች ቢገደቡም ስለ ፍልስጤም መረጃ ማጋራት መቀጠል አለብን" ሲልም ያክላል።