የዘንድሮው ፕሪሚዬር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታዎች ግምት - ማን ሊጉን ይሰናበታል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኤቨርተን፣ ሊድስ እና ሌይስተር ከሊጉ ላለመውረድ የሚታገሉበት ቀን። ከሦስቱ ሁለቱ ሊጉን ‘ቻው ቻው’ ማለት ግድ ይሆንባቸዋል።
የቢቢሲ ስፖርት ተንታኝ ክሪስ ሱቶን “የእሑድ ጨዋታዎች በጣም አጓጊ ናቸው” ይላል።
ሌይስተር ዌስትሃምን ካሸነፈ፤ የኤቨርተንን ውጤት ይጠብቃል። ኤቨርተን ደግሞ ቦርንመዝን መርታት ይጠበቅበታል። ሊድስም ቢሆን የመትረፍ ዕድል አለው።
ሱቶን፤ ዘንድሮ 380 የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎችን ገምቷል። እነሆ የ2022/23 የመጨረሻ ግምቱን እንዲህ አስቀምጧል። ሁሉም ጨዋታዎች እሑድ በተመሳሳይ ሰዓት በ12፡30 ይደረጋሉ።
አርሰናል ከ ዎልቭስ
ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች ይህን ያህል አስፈላጊ የሚባል አይደለም። ነገር ግን አርሰናል የዘንድሮውን የውድድር ዘመን በደጋፊዎቹ ፊት በድል መጨረስ ይሻል።
በመጨረሻዎቹ ሳምንታት የዋንጫ ተስፋው የጨለመው አርሰናል ዓመቱን ቢያንስ በሦስት ነጥብ ማጠናቀቅ ይሻል።
ሱቶን አርሰናል ይህን ጨዋታ ይረታል ብሎ ይገምታል።
በዎልቭስ በኩል ባለፈው ኅዳር ተሹመው ቡድኑን ከመውረድ ስጋት ያዳኑ አሠልጣኝ ጁሌን ሎፔቴጉ ከመንበራቸው እንዳይነሱ ፍራቻ አለ።
ግምት፡ 2 - 0
አስተን ቪላ ከ ብራይተን
ብራይተን ረቡዕ በሜዳው ከማንቸስተር ሲቲ አቻ መውጣቱ በሚቀጥለው ዓመት በአውሮፓ ሊግ ተሳታፊ እንዲሆን አድርጎታል።
ነገር ግን አስተን ቪላ በአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ለመጫወት ከቶተንሃም በላይ ሆኖ መገኘት አለበት።
ቪላ ከዓለም ዋንጫ በፊት ብራይተንን መርታት ችሏል። ኡናይ ኤሜሪ የቪላ አሠልጣኝ ከሆኑ በኋላ ቡድኑን ለውጠውታል።
ነገር ግን በዚህኛው ጨዋታ የሮቤርቶ ዲ ዘርቢን ቡድን ይረታሉ ብዬ አልገምትም ይላል ሱቶን።
ግምት፡ 1 - 1
ብሬንትፈርድ ከ ማንቸስተር ሲቲ
ብሬንትፈርድ በጣም ድንቅ የሚባል የውድድር ዘመን ነው ያሳለፈው። ባለፈው ኅዳር በኤቲሃድ ሲቲን የረቱት ንቦቹ ይህን ድል ለመድገም ይፋለማሉ።
ወደ ፕሪሚዬር ሊግ ከመጡ ገና ሁለት ዓመት የሆናቸው ንቦቹ ለማንም የሚበገሩ አይደሉም።
ይህ ጨዋታ ለቻምፒዮኖቹ ቀላል ይሆናል ተብሎ አይገመተም። በሳምንቱ አጋማሽ በብራይተን የተፈተኑት የፔፕ ልጆች አሁን ሌላ ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል።
ምንም እንኳ ሲቲ በቀጣይ ሳምንታት የኤፍ ኤ እና የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ፍፃሜዎች ቢኖርበትም ከብሬንትፈርድ ጋር የሚኖረውን ጨዋታ በድል እንደሚወጣ ሱቶን ይገምታል።
ግምት፡ 1 - 2

ቼልሲ ከ ኒውካስል
ኒውካስሎች ለቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ማለፋቸውን ተከትሎ ፌሽታ ላይ ናቸው። የዚህ ጨዋታ ውጤት በኒውካስል ተጫዋቾች ተነሳሽነት ላይ ይወሰናል።
ነገር ግን ቼልሲ አሁን ያለበት አቋም እጅግ የወረደ መሆኑን ውጤቱ የኒውካስል ሊሆን እንደሚችል ያሳያል።
በዘንድሮው ፕሪሚዬር ሊግ ከቼልሲ የወረደ ውጤት ያመጡት ከሊጉ ግርጌ የተቀመጡት አራት ቡድኖች ናቸው።
ግምት፡ 0 - 2
ክሪስታል ፓላስ ከ ኖቲንግሃም ፎረስት
ባለፈው መጋቢት ቪየራን ተክተው የፓላስ አሠልጣኝ ሆነው የተሾሙት ሮይ ሆጀሰን ሥራቸውን በአግባቡ ከውነዋል።
ሆጅሰን ከፓላስ ጋር ቆዩም፣ አልቆዩ የዘንድሮውን የውድድር ዓመት በአዎንታዊ ውጤት ማጠናቀቅ ይፈልጋሉ።
በተለይ ደግሞ አስገራሚ አቋሙን እያሳየ ያለው ኤቤሬቺ ኤዜ ውጤት ቀያሪ ሊሆን ይችላል።
ፎረስት ዘንድሮ ከሜዳው ውጭ ካደረጋቸው 18 ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ነው ያሸነፈው። የቡድኑ ነጥብ ደግሞ ሰባት ብቻ ነው።
ግምት፡ 2 - 0
ኤቨርተን ከ ቦርንመዝ
ይህ ጨዋታ ለኤቨርተን እግጅ ወሳኝ ነው። ኤቨርተኖች ዕጣ ፈንታቸው በእጃቸው ነው። ነገር ግን ቦርንመዝ ቀላል ይሆናል ማለት ዘበት ነው።
ኤቨርተኖች በጣም ፈጣን ጨዋታ ያደርጋሉ። ነገር ግን የፊት መስመሩን የሚመራው ዶሚኒክ ካልቨርት-ሉዊን ሙሉ በሙሉ አለማገገሙ ስጋት ነው።
ጉዲሰን ፓርክ እሑድ ዕለት በጭንቀት የሚሞላበት ቀን ይሆናል። ቢሆንም ኤቨርተን ጨዋታውን ረትቶ ይቆያል የሚል ግምት አለኝ ይላል ሱቶን።
ግምት፡ 1 - 0
ሊድስ ከ ቶተንሃም
ሦስት ጨዋታዎችን ብቻ ያሠለጠኑት ሳም አላርዳይስ በቡድናቸው የተከላካይ መስመር ስንፈት ተስፋ ሳይቆርጡ አይቀሩም።
ሱቶን፤ ሊድስ ይህን ፍልሚያ ያሸንፋል የሚል እምነት የለው። ሊድስ ወደ ታችኛው ሊግ ይወርዳል ሲል ያምናል።
ቶተንሃምም ቢሆን ይህን ያህል አድናቆት ሊቸረው የሚገባ ቡድን አይደለም። ለዚህ ነው ጨዋታው ወደ አቻ ያደላል የሚል ግምቱን የሚያስቀምጠው።
ግምት፡ 1 - 1

ሌይስተር ከ ቶተንሃም
ሱቶን በመጨረሻዎቹ ሳምንታት የተመዘገቡ አንዳንድ ውጤቶች በጣም እንዳስገረሙት አይደብቅም።
ለምሳሌ ሰኞ ዕለት ሌይስተር ወደ ኒውካስትል ሜዳ አቅንቶ 0 - 0 መለያየቱ እንዳስገረመው ይገልጻል። “ኒውካስትል በጎል ናዳ ይረታል ብዬ ቤቴን የማስይዝበት ፍልሚያ ነበር” ይላል።
የመውረድ ስጋት የተጋረጠባቸው ሌይስተር እና ሊድስ ጎል የማስቆጠር ችግር የለባቸውም። ነገር ግን ሁለቱም የተከላካይ መስመራቸው ስስ ነው።
የአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ፍልሚያ የሚጠብቃቸው የዌስት ሃም አሠልጣኝ ዴቪድ ሞየስ ምናልባት አንዳንድ ተጫዋቾችን ሊያሳርፉ ይችላሉ።
ለዚህ ነው ሌይስተር ይህን ጨዋታ የማሸነፍ ዕድል አለው ሲል ሱቶን ግምቱን የሚያስቀምጠው።
ግምት፡ 2 - 1
ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ፉልሃም
ፉልሃም ባለፈው ጊዜ ወደ ኦልድ ትራፈርድ ለኤፍ ኤ ዋንጫ ሲመጣ አጥቂው በቀይ እስኪወጣበት ድረስ ጥሩ ተፋልሞ ነበር።
ዩናይትድ ቼልሲን 4 ለ 1 ረትቶ ለቻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ማለፉን ቢያረጋግጥም ፉልሃም ሊፈትነው እንደሚችል እሙን ነው።
ቀያይ ሰይጣኖቹ ሜዳቸውን አስፈሪ አድርገውታል። ከ11 ሰዓታት የእግር ኳስ ጨዋታ በኋላ ቼልሲ በኦልድ ትራፈርድ ጎል ያስቆጠረ የመጀመሪያው ቡድን ሆኗል።
ግምት፡ 2 - 1
ሳውዝአምፕተን ከ ሊቨርፑል
ሳውዝአምፕተን ፕሪሚዬር ሊጉን ተሰናብቷል። በዘንድሮው የውድድር ዘመን ሁለት ጊዜ ብቻ ነው በሜዳቸው ድል የቀናቸው።
ሊቨርፑል ደግሞ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ወጥ አቋም ማሳየት ጀምሯል። ቢሆንም ለየርገን ክሎፕ ከባድ የሚባል የውድድር ዘመን ነበር።
ሊቨርፑል በሚቀጥለው የውድድር ዘመን በአውሮፓ ሊግ ይሳተፋል።
ግምት፡ 0 - 2












