ሜሰን ማውንት ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ፤ ማዲሰን ወደ አርሰናል?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ማንቸስተር ዩናይትድ ለቼልሲው አማካይ ሜሰን ማውንት 55 ሚሊዮን ፓውንድ ለመክፈል መስማማቱን ሜይል የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል።
እንግሊዛዊው የ24 ዓመት አማካይ በሊቨርፑል እና በአርሰናል ቢፈለግም የእሱ ቀልብ ግን ወደ ኦልድ ትራፈርድ ይመስላል።
ማውንት የወደፊት ዕጣ ፈንታውን በተለመከተ ከቼልሲ ኃላፊዎች ጋር በሚቀጥለው ሳምንት ውይይት እንደሚያደርግ ተሰምቷል።
ቼልሲ ተጫዋቹን ለመሸጥ ከወሰነ ማውንት ከሌሎች ቡድኖች ይልቅ ወደ ማንቸስተር መሄድን ይመርጣል።
ጋሬዝ ሳውዝጌት የዩናይትዱ ሃሪ ማጓየር እና የሲቲው ካልቪን ፊሊፕስ በቂ የጨዋታ ጊዜ አለማግኘታቸው “አሳሳቢ ነው” ብለዋል ሲል ጋርዲያን ጽፏል።
የ30 ዓመቱ ተከላካይ ማጓየር እንዲሁም የ27 ዓመቱ አማካይ ፊሊፕስ ለብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ ተደርጎላቸዋል።
እንግሊዝ በቅርቡ የአውሮፓ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎቿን ታድርጋለች።
ኢንዲፔንደት ደግሞ የሌይስተር ሲቲው የክንፍ ተጫዋች ሃርቪ ባርንስ ወደ አስተን ቪላ ሊያቀና ይችላል የሚል ዜና ይዞ ወጥቷል።
ሌይስተር ሲቲ ከእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የመውደቅ አደጋ ተደግኖበታል።
ሌላው የመውደቅ ስጋት ውስጥ ያለው ሊድስ ዩናይትድ እንግሊዛዊው ጃክ ሃሪሰንን ለዌስትሃም ሊሸጥ እንደሚችል ሰን የተባለው ጋዜጣ ጠቁሞ ዌስትሃም ባርንስን ለማምጣት ዕቅድ እንዳላቸውም ጠቁሟል።
በአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ለፍፃሜ የበቁት ዌስትሃሞች አሠልጣኝ ዴቪድ ሞየስን እንደማያሰናብቱ ጋርዲያን አስነብቧል።
ቡድኑን ለማጠናከር ያሰቡ ሞየስ የፉልሃሙን ፓርቹጋላዊ አማካይ ጃዎ ፓሊንሃን ለማስፈረም ይሻሉ። ይህ የሚሆነው ዴክለን ራይስ ከተሸጠ ነው።
አርሰናል በክረምቱ የዝውውር መስኮት ራሱን ለማጠናከር እስከ 14 ተጫዋቾችን ሸጦ፤ ስምንት ተጫዋቾችን ለማምጣት ማቀዱን የዘገበው ፉትቦል ለንደን ነው።
ይሸጣሉ ከተባሉት ተጫዋቾች መካከል የክለቡ የግዢ ክብረ ወሰን ሰብሮ የመጣው አይቮሪ ኮስታዊው ኒኮላስ ፔፔ ይገኝበታል።
ሚኬል አርቴታ የ22 ዓመቱን እንግሊዛዊ አማካይ ኤሚል ስሚዝ ሮውን አሰናብተው ጄምስ ማዲሰንን ሊገዙ እንዳቀዱ የሚረር ዘገባ አስነብቧል።
አልፎም መድፈኞቹ የቶሪኖውን ፓራጓዊ የፊት መስመር ተጫዋች አንቶኒዮ ሳናብሪያ በ21 ሚሊዮን ፓውንድ ለመግዛት አስበዋል።
ማንቸስተር ዩናይትድ የ24 ዓመቱን ናይጄሪያዊ የናፖሊ አጥቂ ቪክተር ኦሲምሄን ለማስፈረም ከፈለጉ 140 ሚሊዮን ፓውንድ ማውጣት አለባቸው።
ሚረር እንደሚለው ዩናይትድ የናፖሊውን ተከላካይ ደቡብ ኮሪያዊው ኪም ሚን-ጄን ለመግዛት ተስማምተዋል።
ነገር ግን ናፖሊ ተከላካዩ በክለቡ ያለውን ቆይታ እንዲያዝም እየጎተጎቱት መሆኑን 90ሚን ሹክ ብሏል።
ቢሆንም አሁንም የዩናይትድ ቀዳሚ ዒላማ የቶተንሃሙ እንግሊዛዊ አጥቂ ሃሪ ኬንን ማስፈረም ነው። ዩናይትድ የክረምት የዝውውር መስኮት እንደጠባ የ29 ዓመቱን አጥቂ ለማስፈረም ይሽቀዳደማል ተብሏል።
በሌሎች ጭምጭምታዎች አስተን ቪላ የዋትኪንስ እና ጆን ማክጊን ውልን ለማራዘም እየተሯሯጠ መሆኑ ተሰምቷል።
ኢንተር ሚላን ደግሞ ከቼልሲ በውሰት ያመጣውን ሮሜሉ ሉካኩ ለዘላቂው ለማስፈረም ይሻል።
አርሰናል በበኩሉ የ23 ዓመቱ አማካይ ሪስ ኔልሰንን ውል ለማራዘም እየሞከረ ቢሆንም የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፣ የጣሊያንና የስፔን ክለቦች ዓይናቸውን ጥለውበታል።












