የጋቦንን መፈንቅለ መንግሥት የመሩት ጄኔራል ማን ናቸው?

በጋቦን የተደረገውን መፈንቅለ መንግሥት የመሩት ጄኔራል የቀድሞው ፕሬዝዳንት ልዩ ጠባቂና ረዳት እንደነበሩ ታወቀ።

ሙሉ ስማቸው ጄኔራል ብጊዝ ኡሊጊ ኡንጉማ ይህን መፈንቅለ መንግሥት የመሩ ሲሆን ትናንት ረቡዕ ዋናዎቹ ጄኔራሎች ባደረጉት ዝግ ስብሰባ የሽግግር መሪ አድርገው ሰይመዋቸዋል።

ጄኔራል ኡንጉማ በጋቦን ዋና ከተማ በወታደሮች ተከበው በድል ስሜት አቀባበል ሲደረግላቸው ታይተዋል።

የጄኔራሉ ዋንኛ ሥራ አሊ ቦንጎን ከዚህ ዓይነቱ መፈንቅለ መንግሥት መጠበቅ የነበረ ሲሆን በተቃራኒው ፕሬዝዳንቱን ራሳቸውን ፈንቅለዋቸዋል።

በቁም እስር ላይ የሚገኙት አሊ ቦንጎ በለቀቁት የይድረሱልኝ ቪዲዮ “ወዳጆቼ በሙሉ፣ ምን እየተካሄደ እንደሆነ አልገባኝም። በዓለም ላይ ያላችሁ ወገኖቼ በሙሉ፣ እባካችሁ ድምጽ አሰሙ-ኡኡ በሉ!” ሲሉ ተማጽነዋል።

ይህን ተከትሎ በዋና ከተማዋ ሊብረቪል ከፍተኛ ድምጽ የተሰማ ሲሆን ድምጹ ግን ‘እንኳንም ከእርስዎ ተገላገልን’ የሚል ሆኗል። የጋቦን ወጣቶች በዋና ከተማና ሌሎች ከተሞች ፈንቅለው በመውጣት በደስታ ሲጨፍሩ አድረዋል።

የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የነበረችው ጋቦን በአፍሪካ በነዳጅ ሃብት ከታደሉ ጥቂት አገራት አንዷ ናት። ይሁንና ሕዝቡ በከፍተኛ ድህነት ሲንከላወስ ነው የኖረው።

ጋቦን በምዕራብ አፍሪካ የምትገኝ ሲሆን ጠቅላላ የሕዝብ ብዛቷ 2.4 ሚሊዮን ብቻ ነው።

ጋቦንን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የመራት አንድ ቤተሰብ ሲሆን ይህም የቦንጎ ሥርወ መንግሥት እየተባለ ይጠራል።

መፈንቅለ መንግሥቱን የመሩት ወታደሮች በቦንጎ ቤተሰብ መኖርያ ቤት ባደረጉት ፍተሻ በበርካታ ሻንጣዎች የታጨቀ ዶላርና ዩሮ ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል።

የቦንጎን ወንድ ልጅ በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውንም ወታደሮቹ ተናግረዋል።

መፈንቅለ መንግሥቱ ስኬታማ መሆኑን የተናገሩት ጄኔራሎች ዝግ ስብሰባ በማድረግ አገሪቱን ሊያሸጋግሩ ይችላሉ ያሏቸውን ጄኔራል ኡንጉማን በሙሉ ድምጽ መርጠዋል።

ጄኔራል ኡንጉማ ቀድሞ የፕሬዝዳንቱ ልዩ ጥበቃ ኃላፊ ነበሩ።

አገሪቱን ለ41 ዓመታት የመሩት የአሊ ቦንጎ አባት፣ ለኦማር ቦንጎ የቅርብ ረዳታቸው ሆነው ሠርተዋል።

ጄኔራል ኡንጉማ 48 ዓመታቸው ሲሆን ከዚህ ቀደም የአሊ ቦንጎ አባት ሞትን ተከትሎ በተሞከረው ያልተሳካ መፈንቅለ መንግሥት ተሳትፎ ነበራቸው በሚል ተጠርጥረው ወደ ሴኔጋል ገሸሽ ተደርገው ነበር።

በኋላም ወደ ሞሮኮ ተልከው በወታደራዊ አታሼነት አገልግለዋል።

በፈረንጆቹ 2018 ደግሞ በሪፐብሊካን ጋርድ የደኅንነት ኃላፊ ሆነው የተሾሙ ሲሆን ይህ ኃላፊነት የተሰጣቸው የአሊ ቦንጎ ወንድም ፍሬድሪክ ቦንጎ ተነስተው ነው። ከዚያ በኋላ ነበር ጉንጉማ የጄኔራልነት ማዕረግ ያገኙት።

ጄኔራሉ መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ በቴሌቪዥን በተነበበው መግለጫ ከሚታዩት ጄኔራሎች መካከል አልነበሩም።

በአፍሪካ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መፈንቅለ መንግሥቶች የተበራከቱ ሲሆን ባለፈው ዓመት በቡርኪናፋሶ ሁለት ጊዜ፣ በቅርብ ጊዜ ደግሞ በኒጀር፣ በ2021 ደግሞ በጊኒ እንዲሁም በማሊ ተመሳሳይ መፈንቅለ መንግሥቶች ነበሩ።

ሁሉም መፈንቅለ መንግሥቶች የሚያመሳስላቸው 'ፍራንክፎን አገሮች' በሚባሉ የምዕራብና መካከለኛ አፍሪካ አገሮች መሆናቸው ነው።

ፈረንሳይ በነዚህ አገሮች ከፍተኛ የከበሩ ማዕድናትና ሌሎች ጥሬ ዕቃዎች ፍላጎት ያላት ሲሆን የአገራቱ ሕዝቦች ደግሞ የፈረንሳይ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት በቃን በማለት አደባባይ ሲወጡ ታይተዋል።

በኒጀር የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪዎች የፈንሳይ አምባሳደር ከአገር እንዲወጡ ቢጠይቁም አምባሳደሩ አልወጣም ማለታቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ለኤምባሲው የኤሌክትሪክና የዉሃ መስመሮች ተቆርጠው ነበር።

በጋቦን የተደረገውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ በፈረንሳይ የሚኖሩ ጋቦናዊያን ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

የቦንጎ ቤተሰብ በፈረንሳይ ውድ ሪልስቴቶች ባለቤት እንደሆኑ ይነገራል።

በጋቦን የተደረገውን መፈንቅለ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታትና የአውሮፓ ኅብረት አውግዘውታል።