ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠየቀ።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በበኩሉ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት መግታት የሚያስችል እርምጃዎች ለመውሰድ ዳተኛ በመሆናቸው እየተፈጸመ ላለው ጥቃት ተባባሪ ሆነዋል ብሏል።
በምዕራብ ኦሮሚያ በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ተከትሎ ሁለቱ ፓርቲዎች ባወጡት ጠንካራ መግለጫ መንግሥት የሕዝቡን ደኅንነት ማረጋገጥ ተስኖታል ብለዋል።
ኢዜማ ማንነትን መሰረት አድርገው የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለማስቆም መንግሥት ግዴታውን እንዲወጣ በተደጋጋሚ ባሳስብም፣ ጉዳዩን ጆሮ ዳባ ልበስ ተብሎ ማሳሰቢያዎቹን ለመቀበል ምንም አይነት ፍላጎት አላሳየም ብሏል።
ኢዜማ “የሕግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነቱም ከዕለት ዕለት ጥያቄ ውስጥ እየገባ መምጣቱ በብርቱ አስግቶናል” ብሏል።
አብን በበኩሉ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት መግታት የሚያስችል ተግባራዊ እርምጃዎች ለመውሰድ ዳተኛ በመሆን “እየተፈጸመ ላለው ጥቃት ተባባሪ ሆነዋል” ብሏል።
መንግሥት ለጥቃት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ ዜጎችን በማደራጀት፣ በማስታጠቅ እና አመራር በመስጠት ከመሰል ጥቃቶች ራሳቸውን የሚከላከሉበትን አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጥር አብን ጠይቋል።
ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲው፤ ተደጋጋሚ ጥቃት በሚፈጸምባቸው የምሥራቅ፣ የምዕራብ እና የቄለም ወለጋ ዞኖች የሲቪል እና የፖሊስ አስተዳደር አባላት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቋል።
በተጨማሪም አካባቢዎቹ ከፌዴራሉ መንግሥት በሚመደቡ የሲቪል እና የፀጥታ አስተዳደር አካላት እንዲተዳደሩ እና አካባቢዎቹን የማስተዳደር ሥልጣን ላልተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በፌዴራል መንግሥት ስር እንዲውል አሳስቧል።
ከትናንት በስቲያ ሰኔ 27/2014 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ውስጥ መንግሥት ኦነግ ሸኔ ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በዜጎች ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መግለጻቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ “በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል” ብለዋል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥርን በመቶዎች እንደሆነ ቢገልጹም እስካሁን ድረስ የተጎጂዎችን ቁጥር በተመለከተ መንግሥት ያለው ነገር የለም።
ሰኔ 11/2014 ዓ.ም. ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ውስጥ በሚገኘው ቶሌ ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት ከ330 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ማስታወቁ ይታወሳል።
ኢዜማ መንግሥት በተላይ በምዕራብ ኦሮሚያ የፀጥታ ችግሮችን መቆጣጠር ለምን እንደተሳነው ለሕዝብ በግልጽ የማሣወቅ ግዴታ አለበት ብሏል።
“ይህ መፍትሄ የጊዜ ገደብ ወጥቶለት አካባቢውን ከመሠል ጥቃቶች በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ነፃ እንደሚያወጣ በይፋ በመግለጽ መንግሥት ለዜጎች ደኅንነት መጠበቅ ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ እና መንግሥታዊ የማስፈጸም አቅም እንዳለው ሊያሳይ ይገባል" ብሏል።
ነገር ግን መንግሥት ይህን ማድረግ የማይችልና አሁንም "አድበስባሽ ሆኖ መቀጠል ካሰበ አካባቢውን የመቆጣጠር አቅምም ሆነ ፍላጎት እንደሌለው ያሳብቅበታል” ብሏል ኢዜማ ማክሰኞ ሰኔ 28/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ።
በተያያዘ ዜና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 29/2014 ዓ.ም. ባካሄደው ልዩ ስብሰባ በወቅታዊ የፀጥታ እና በንጹሐን ዜጎች ግድያ ላይ ተወያይቶ የውሳኔ ሐሳብ አሳልፏል።
ፓርላማው ከልዩ ስብሰባው በኋላ፤ በምክር ቤቱ የበላይ አመራር የሚሰየም ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን በማጣራት ምክር ቤቱ እና ሕዝቡ በቂ መረጃ እንዲኖረው ለማስቻል፤ እንዲሁም ለቀጣይ እርምጃዎች የሚረዳ ምክረ-ሐሳብ እንዲቀርብ ወስኗል።
ከመንደራቸው እና ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በአስቸኳይ እንዲሰራም ምክር ቤቱ ወስኗል።