ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጋናዊቷ ሼፍ ያለማቋረጥ ለ227 ሰዓታት ምግብ አበሰለች
ጋናዊቷ ሼፍ ፋይላቱ አብዱል-ራዛቅ ያለማቋረጥ ለ227 ሰዓታት ምግብ በማብሰል የዓለም ክብረ-ወሰን ለመስበር ከጫፍ ደርሳለች።
በሀገሯ ባንዲራ ደምቃ የታየችው ጋናዊቷ ሼፍ ለ227 ሰዓታት ካበሰለች በኋላ ረቡዕ ዕለት ስሜታዊ በሆነ መንገድ ሥራዋን አጠናቃለች።
ይህን ያደረገችው ለሀገሯ ጋና እንደሆነ የምትናገረው ሼፍ ፋይላቱ ወደ ማብሰል ከመግባቷ በፊት “ይህ ሀገራዊ ኃላፊነት” ነው ስትል ተደምጣለች።
በታማሌ ከተማ ካለ አንድ ሆቴል ኩችና ሥራዋን አጠናቃ ስትወጣ ተመልካቾች በጭብጨባ ተቀብለዋታል።
የሼፏ አጋዦች ፋይላቱ የዓለም ክብረ-ወሰን ለሆነ ጊዜ ስታበስል መቆየቷን የሚያሳይ ማስረጃ ለዓለም ድንቃድንቅ መዝጋቢ ድርጅት [ጊነስ ዎርልድ ሬከርድስ] እንደሚልኩ ገልጠዋል።
የወቅቱ ክብረ-ወሰን ባለቤት አየርላንዳዊው አለን ፊሸር ሲሆን ለ119 ሰዓታት ከ57 ደቂቃ በማብሰል ስሙን አስመዝግቧል።
ሼፍ ፋይላቱ እንደምትለው ማንኛውም የሷን ክብረ ወሰን ለመስበር የሚሞክር ሰው “ከባድ” ሊሆንበት ይችላል።
የጋና ምክትል ፕሬዝደንትን ጨምሮ የተለያዩ ፖለቲከኞች እና የሀገሪቱ ጦር ሠራዊት ለሼፏ ያላቸውን አድናቆት ገልጠውላታል።
አልፎም በርካታ ጋናዊያን ለሀገራቸው ልጅ ያላቸውን አድናቆትና ክብር በተለያየ መንገድ እየገለጡ ነው።
ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ናይጄሪያዊቷ ሂልዳ ባቺ ለረዥም ሰዓታት በማብሰል ክብረ-ወሰን ሰብራ ነበር።
ነገር ግን የባቺ ክብረ-ወሰን በአየርላንዳዊው ፊሸር ሊሰበር ችሏል።
ባለፈው ታኅሣሥ ሌላኛዋ ታዋቂ ጋናዊት አፉዋ አሳንቴዋ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሙዚቃ በመጫወት ብዙዎችን አጀብ አሰኝታለች።
በአውሮፓውያኑ የገና በዓል አከባበር ወቅት ለ5 ተከታታይ ቀናት የሞዘቀችው ጋናዊት ከጊነስ ዎርልድ ሬኮርድስ ሽልማት የማግኘት ሕልም አላት።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርካታ ናይጄሪያዊያን በየሞያቸው የዓለም ክብረ-ወሰን ለመስበር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል።
ከሂልዳ ባቺ ለረዥም ሰዓታት የማብሰል ሙከራ ጀምሮ የሁለተኛ ደረጃ አስተማሪ የሆነው ጆን ኦቦት ለረዥም ሰዓታት ድምፁን ከፍ አድርጎ እስከማንበብ ክብረ-ወሰን ለመስበር የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው።